የኖቤል ተሸላሚው ጠቅላይ ሚኒስትር በሚል ኢትዮጵያ ላይ የሚደረግን የማንኳሰስ ስልት ኤርትራ ተቃወመች

ኤርትራ ከአሸባሪው ሕወሓት ጎን በመቆም ‹የኖቤል ተሸላሚው ጠቅላይ ሚኒስትር› በሚል የማንኳሰስ ስልትና ስሁት ትርክት ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ኢትዮጵያን ወደ ጦርነት እንደከተቷት ለማሳመን የሚደረግን ጥረት ተቃወመች፡፡ አገር ከማፍረስ የተናበበ እኩይ ሴራና ከአስፈፃሚው የሽብር ቡድኑ ሕወሓት ጋር በማበር በኢትዮጵያ ላይ የተነሱ መገናኛ ብዙኃን በየዘገባቸው መጀመሪያ ‹የኖቤል ተሸላሚው ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ› ማለትን በተናበበ መልኩ እየተጠቀሙት ይገኛሉ፡፡
ይህን መነሻ በማድረግ መልዕክት ያስተላለፉት የኤርትራው የማስታወቂያ ሚኒስትር የማነ ገብረመስቀል፤ ባራክ ኦባማ የአሜሪካ ፕሬዝዳንት በነበሩበት ወቅት የሆነውን አስታውሰዋል፡፡ ‹‹ኦባማ በአፍጋኒስታን የነበረውን ጦርነትና ዘመቻ ያቀጣጠሉት፣ አሜሪካ በሊቢያ ከኔቶ ጦርነት ጀርባ ሆና ግፋ በለው ስትል የነበረው፣ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሯ ሂላሪ ክሊንተን የሶሪያው ፕሬዝዳንት ‹በሽር አል አሳድ ሕጋዊነቱን አጥቷል› ብለው ያወጁትና አሜሪካ ጥልፍልፉን ሴራ የከወነችው ፕሬዝዳንት ኦባማ የሰላም ኖቤል ሽልማትን ከወሰዱ (ካሸነፉ) በኋላ ነው›› ሲሉ ሚኒስትሩ ለሃብታም አገራት ትክክል እንደኢትዮጵያ ላሉ አዳጊዎች ደግሞ ስህተት የሚደረግበትን የተዛባ የዓለም ሚዛን ተችተዋል፡፡
ዓለም ዐቀፍ መገናኛ ብዙኃን ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ በአፍሪካ ቀንድ ውኅደትን ለመፍጠር በተለይም ደግሞ ከኤርትራ ጋር እርቅ እንዲወርድ በማድረጋቸው የሰላም ኖቤል ተሸላሚ መሆናቸውን እያወቁ አሁን ለያዙት የማንኳሰስና አገር የማፍረስ ሴራ ጉዳዩን ሊያንሻፍፉት እየሞከሩ ነው፡፡
ኢትዮጵያዊያንና ወዳጆቻቸው ግን ጠቅላይ ሚኒስትሩ የኖቤል ተሸላሚ የሆኑት ለሰላም ባላቸው ትጋት እንጂ አገርና ሕዝብን ለወራሪና ባንዳ አሳልፈው እንዲሸጡ ወይም የኢትዮጵያ ሉኣላዊነትና የግዛት አንድነትን አሳልፈው እንዲሰጡ አለመሆኑን በመጥቀስ በቲውተርና ሌሎችም የመሞገቻ መድረኮች እውነት ይዘው እየተፋለሙት ይገኛሉ፡፡