በግንባር መሰለፍን ጨምሮ ለሕልውና ዘመቻው የሚጠበቅብኝን ሁሉ ለማድረግ ዝግጁ ነኝ – አትሌት ሻለቃ ኃይሌ ገብረስላሴ

አትሌት ሻለቃ ኃይሌ ገብረስላሴ ፤ በግንባር መሰለፍን ጨምሮ ለሕልውና ዘመቻው የሚጠበቅብኝን ሁሉ ለማድረግ ዝግጁ ነኝ አሉ።

አትሌት ሻለቃ ኃይሌ ገብረስላሴ ይህ ያሉት ለኢዜአ በሰጡት ቃል ነው።

” በኢትዮጵያ የተደቀነው አደጋ አፍሪካን የማንበርከክ ዓላማ ጭምር ያነገበ የእጅ አዙር ቅኝ ግዛት ሙከራ ነው ” ያሉት አትሌት ሻለቃ ኃይሌ ፥ ” ” ኢትዮጵያ የጥቁር ሕዝቦች የነጻነት ምልክት ናት ፤ ኢትዮጵያን በማንበርከክ የጥቁር ሕዝቦችን አኩሪ ታሪክ ለመቀማት የተቀናጀ ዘመቻ በኢትዮጵያ ላይ እየተከናወነ ይገኛል” ብለዋል።

ከዚህ አኳያ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አህመድ ለኢትዮጵያ ክብር ወደ ግንባር መዝመታቸው አገሩን ከሚወድ መሪ የሚጠበቅ ተግባር መሆኑን እና አገር ወዳድ ኢትዮጵያዊ ሁሉ የእርሳቸውን ፈለግ እንዲከተል ጥሪ አቅርበዋል።

መላ አፍሪካዊያን ትግሉ የሁሉም ጥቁር ሕዝቦች መሆኑን በመገንዘብ ከኢትዮጵያ ጎን እንዲቆሙም ጥሪ አቅርበዋል።

አትሌት ኃይሌ ፦ “ኢትዮጵያን ብለን ተሸንፈን አናውቅም፤ ኢትዮጵያ ሁሌም አሸናፊ ናት” ሲሉ ነው የተናገሩት።

በአንድ ወቅት የጎበኟት የቱሪስት መናኸሪያ የነበረችውን የሶሪያዋ አሌፖ ከተማ በምዕራባውያን ጣልቃ ገብነት ምክንያት ወደ ፍርስራሽነት መቀየሯን ጠቅሰዋል።

“በመሆኑም እኛ ኢትዮጵያዊያን በአገራችን ላይ ይህን መፍቀድ የለብንም” ያሉት አትሌት ኃይሌ ፤ ” ከዚህ አንጻር ከደጀንነት ባሻገር በግንባር በመሰለፍ ጭምር አገሬ በምትፈልገኝ ቦታ ለማገልግል ዝግጁ ነኝ ” ብለዋል ለኢዜእ በሰጡት ቃላቸው።