በዱራሜከተማ ደቡብ ኢትዮጵያ ስራ እንዲሰጣቸው በሰላማዊ ሰልፍ የጠየቁ የዩኒቨርስቲ ምሩቃን በፖሊሶች ተደበደቡ

(ኢሳት – ጥቅምት 16 ቀን 2011 ዓ/ም) – በከምባታ ጠምባሮ ዞን ካለፉት 4 ዓመታት ወዲህ በተለያዩ ዩኒቨርስቲዎች ተመርቀው ስራ ያጡ ወጣቶች ወደ ዞን መስተዳደር ምክር ቤት ማምራታቸውን ተከትሎ በፖሊሶች ድብደባ ተፈጽሞባቸዋል።

ተማሪዎቹ ቀደም ብለው ጥያቄያቸውን ለመስተዳድሩ አቅርበው ለዛሬ አርብ ተቀጥረው የነበረ ቢሆንም፣ በቀጠሮአቸው መሰረት ወደ መስተዳድሩ ሲሄዱ ያጋጣማቸው የፖሊስ ዱላ ነው። በጉዳዩ ዙሪያ የከተማውን የአስተዳደር አካላት ለማግኘት ያደረግነው ሙከራ አልተሳካም።

ተጨማሪ ዘገባ ከፌስቡክ ፔጅ ተከታታያችን፦

በከምባታ ጠምባሮ ዞን በተለያዩ ትምህርት መስኮች ካለፉት አራት አመታት ወዲህ ከተለያዩ ዩኒቨርሲቲዎች ተመርቀው ስራ ያጡ ወጣቶች ዛሬ ወደ ዞን መስተዳድር ምክር ቤት አምርተው ነበር። ይሁን እንጂ ቁጥራቸው ወደ300 የሚደርሱት ወጣቶች በምላሹ መደብደባቸውንና መበተናቸውን የደረሱን መረጃዎች ያመለክታሉ።

በከተማው የነበረውን መሯሯጥ እንደተሰማ ሁኔታውን እንደተከታተልኩት ዱላ የያዙ ፖሊሶች ወጣቶቹን እያሯሯጡ ሲደበድቡ ብዙዎች ታዝበዋል። ሮጠው ማምለጥ ያልቻሉ ሴቶችና የፖሊሶችን እርምጃ ለመቋቋም የሞከሩ ወጣቶች ክፉኛ ተደብድበዋል። በሶስት የወታደር ላንድክሩይዘር መኪና የተጫኑት ፖሊሶች በመቶዎች የሚቆጠሩትን ወጣቶች ከመደብደብ በተጨማሪ ቁጥራቸው ባይታወቅም የተወሰኑት ታስረው ሊሆን እንደሚችል ጥርጣሬ ያደረባቸው ብዙዎች ናቸው።

ጥያቄያቸው ምን እንደነበረ ለማወቅ ቀርቤ ያነጋገርኳቸው ተደብዳቢዎች ውስጥ በዱላ የደረሰበትን ድብደባ እያሳየ አንድ ወጣት እንደገለፀልኝ÷ “የዞን መስተዳድር ምክር ቤቱ በክልሉ የሚታወቀው ምንም ስራ አጥ እንደሌለበት በመሆኑ ድምፃችን ታፍኖ ትኩረት ተነፍገናል ስለዚህ ዋናው አስተዳዳሪ በሰጡን ቀጠሮ መሰረት ያነጋግሩን በማለታችን ተደብድበናል። ይህ ቀጠሮ በአስተዳዳሪው ብቻ ሲቀየር ለሦስተኛ ጊዜ ነው÷ ብዙ ወጣቶችም ተጎድተዋል÷ ምናልባትም የታፈሱ ልጆችም ይኖራሉ” በሚል እንባ እየተናነቀው አስረድቶኛል።

ይህ በእንዲህ እንዳለ የዞኑን ፖሊስ ስለተፈጠረው ግርግር የጠየቅኳቸው ኃላፊዎች ከወጣቶቹ በኩል የቀረበውን ጥያቄ ተከትሎ የዞኑ ዋና አስተዳዳሪ ዛሬ ሊያነጋግሩ ባለመቻላቸው ለእሑድ ከየወረዳው የተጠሩትን ሰላሳ ሰላሳ ተመራቂዎችን ጨምሮ ሊያነጋግሩ እንደወሰኑ ቢገለፅላቸውም ፈቃደኛ ባለመሆናቸው ግጭት መከተሉን አምነዋል። አስተዳዳሪው በሰዓቱ የዞኑን የሀይማኖት መሪዎችና አባቶች (300 የሚጠጉ ሰዎች) እያነጋገሩ በመሆናቸው ሁለት ስብሰባ በተመሳሳይ ሰዓት ማስተናገድ እንደማይችሉ መግለፃቸውን ባለስልጣኑ ገልፀውልኛል። ይሁን እንጂ÷ “ድብደባ መፈፀም ተገቢ ነው ወይ?” በሚል ላቀረብኩት ጥያቄ ድርጊቱን እያጣሩ መሆኑንና በተፈጠረው ግጭት ማዘናቸውን÷ እንዲሁም ጥቂት የተጎዱ ወጣቶችን ለህክምና መላካቸውን አስረድተዋል።

መንቾ ከም (ጥቅምት 16/2011 ዓ•ም)