ግንቦት ሰባት በናዝሬት ላደረገው ባርኔጣዬን አንስቻለሁ #ግርማ_ካሳ


መረጃ ቲቪ አባል በመሆን የሳተላይት ቲቪውን ቀጥታ ስርጭት፣ ወቅታዊ ዜናዎችን እና ትንተናዎችን፣ የመዝናኛ ፕሮግራሞችን፣ ስፖርት እና ሌሎችንም ዝግጅቶቻችንን በፍጥነት እና ጥራት ስልክዎ፣ ኮምፒዩተርዎ ወይም ቲቪዎ ላይ ማየት ይችላሉ። እዚህ ሊንክ ላይ በመጫን አባል ይሁኑ


ግንቦት ሰባት በናዝሬት በአስር ሺሆች የሚቆጠሩ ኢትዮጵያዉያን ባሉበት አስደማሚ ሕዝባዊ ትእይንት አድርጓል።

ናዝሬት ሕብረብሄራዊ ከተማ ናት። ዜጎች ኦሮሞ፣አማራ፣ ጉራጌ ሳይባባሉ በሰላም የኖሩባት የተዋለዱባት የፍቅር ምልክት የሆነች ከተማ ናት። ብዙዎቹ ነዋሪዎች ከኦሮሞና ከአማራ፣ ከኦሮሞና ከጉራጐ፣ ከጉራጌና ከአማራ ፣ ከከንባታና ከጉራጌ፣ ከትግሬና ከኦሮሞ ….እያሉ የተዋለዱ ናቸው።

ታዲያ ሕብረብሄራዊ ከተማ በሆነችዋ ናዝሬት አብዛኛው ነዋሪ አማርኛ ተናጋሪ ቢሆንም ፣ ኦሮሞዎች ባለቤት በተደረጉበት፣ የኦሮሞ ብቻ በሆነች ክልል ውስጥ ተካታ ፣ የከተማዋና በከተማዋ ያሉ ቀበሌዎች አስተዳደሮች የሚጠቀሙት የስራ ቋንቋ ኦሮምኛ ብቻ ሆኖ፣ አፓርታይዳዊና ዘረኛ አሰራር ነው አጁንም ድረስ ያለው። በናዝሬት ያሉ ከሰባ፣ ሰማኒያ በመቶ በላይ የሚሆኑ ኦሮሞ ያልሆኑ ወገኖች በአገራቸው እንደ ሁለተኛ ዜጋ ነው የሚቆጠሩት።

በአሁኑ ወቅት የዜግነትና ኢትዮጵያዊነትን ፖለቲካ አራምዳለሁ የሚለው ግንቦት ሰባት በመሆኑ፣ ግንቦት ሰባት የጠራውን ስብሰባ እንደ አጋጣሚ በመጠቀም፣ የናዝሬት ሕዝብ ለዘር ፖለቲካ፣ ለዘር መድልዎ፣ ለዘር ክፍፍል ያለውን ጥላቻና ተቃዉሞ በመገለጽ፣ የኢትዮጵያዊነትን ስሜት በገሃድና በአደባባይ አሳውቋል። የኢትዮጵያና አረንጓዴ ቢጫ ቀይ ሰንደቅን ከፍ አድርጎ በማዉለብለብ።

ከዚህ በፊት ግንቦት ሰባቶችን ቻሌንጅ ስናደረግ ነበር። የኦሮሞ ድርጅቶችን ከማባበልና ከመለማመጥ ቀጠታ ወደ ኦሮሞ ክልል ሄደው ህዝቡን ማነጋገር እንዲጀምሩ ጠይቀናል። ግቦት ሰባቶችም በአዳማ ይሄንኑ ነው ያደረጉት። በዚህ አጋጣሚ ሌላው ቢቀር በኦሮሞ ክልል ዋና ከተማ በናዝሬት ሕዝቡ ስሜቱን የሚገልጽበት መድረክ፣ በማመቻቸታቸው ሊመሰገኑ ይገባል። “ይሄን አላደረጉም” ብለን ስንወቅስ እንደነበረው፣ እንዲያደርጉ ስንጠይቅ የነበረውን፣ ዛሬ በናዝሬት የታየው አይነት እንቅስቃሴ ሲያደርጉ እውቅና መስጠት የግድ ነው። ምክንያታዊ ፖለቲካ ማለት ይሄ ነው።

በአማራና በደቡብ ክልል ያለው ማህበረሰብ ኢትዮጵያዊነትን የሚሰበክ ማህበረሰብ አይደለም። ችግር ያለው የኦሮሞ ክልል ነው። የጸረ-ኢትዮጵያዊነት የጥላቻ ፖለቲካ የተረጨውና ስር የሰደደው በኦሮሞ ክልል ነው። በተለይም በወለጋ፣ በተወሰነ ደረጃ በምእራብ ሸዋ፣ በምእራብ አርሲ፣ በሃረርጌና በባሌ።

በነዚህ ቦታዎች የኦሮሞ ማህበረሰብ የኦሮሞ ድርጅቶች ከሚነግሩትና ከሚሰብኩት የተለየ፣ የሚበጀውና የሚጠቅመው አማራጭ አልቀረበለትም። የኢትዮጵያዊነት ፖለቲካ ለኦሮሞ ማህበረሰብ እንደሚጠቅም ማሳየት አልተቻለም። የጽንፈኛ ኦሮሞነት ፖለቲካ የኦሮሞዉን ማህበረሰብ ከሌላው የለየ፣ መቃቃርን የፈጠረ ፖለቲካ ነው። የኔና የርሱ የሚል ስሜትን የፈጠረ ፖለቲካ ነው። የመቀነስ ፖለቲካ ነው። ይህ ፖለቲካ ምን ያህል እንደጎዳው በመረጃ ላይ ተመርኩዞ የኦሮሞን ማህበረሰብ ማስረዳት አልተቻለም።

ለምሳሌ የወለጋና ምእራብ አርሲ ዞኖችን ብንወስዱ ማን ነው ወደዚያ ለመዝናናት፣ ለመኖር.፣ ለመነገድ፣ ሃብት ለማፍራት፣ ኢንቨስት ለማድረግ የሚሄደው ? አክራሪ የኦነግ ታጣቂዎች ሕዝብን እያሸበሩ፣ በኦሮሞ ስም የሚነገዱ ራሳቸውን ቄሮ የሚሉ፣ የሰው ልጅ ዘቅዝቀው የሚሰቅሉ፣ ከሕግ በላይ የሆኑ ቡድኖች ባሉበት፣ ኦሮምኛ ያልተናገረ መስተንግዶ በማያገኙበት ፣ ጠባቦችና ዘረኞች በሃላፊነት ቦታ ላይ በተቀመጡበት አካባቢ መኖር አስቸጋሪ ነው። እንኳን ሌሎች ለመኖር ወደዚያ ሊያምሩ ቀርቶ ያሉትም አቅም ቢኖራቸው ጥለው ነው የሚሄዱት። ይሄ ደግሞ ከማንም በላይ የሚጎዳው ራሱን የኦሮሞ ማህበረሰብ ነው።

በፍቅርና በአንድነት ውስጥ ከተኮነ ግን፣ የኦሮሞ የሆነን ሌላው የኔ ነው ካለ፣ ኦሮሞ ደግሞ የሌላውን የኔ ነው ካለ ፣ አማራው አምቦን እንደ ደብረ ታቦር፣ ትግሬው ዶዶላን እንደ ዉቅሮ፣ ጉራጌው ነቀምቴን እንደ ወልቂጤ ..ከቆጠረ የኦሮሞ ማህበረሰብ በብዛት የሚኖሩባቸው አካባቢዎች በንግድ በኢንቨስትመንት ተጠቃሚ ይሆናሉ። ሆቴል ቤቶች፣ ምግብ ቤቶች…ቢዝነሳቸው ያድጋል። የኦሮሞ ማህበረስበ በኢኮኖሚ ይጠቀማሉ። በርግጥም የአንድነት፣ የዜግነት ፖለቲካ ከማንም በላይ የኦሮሞን ማህበረሰብ የሚጠቅም ነው የሚሆነው።

የኢትዮጵያዊነት ፖለቲካን አንዳንዶች መጨፍለቅ ነው ይላሉ። ይሄ ዉሸት ነው። ኢትዮጵያዊነት ጸረ-ኦሮሞነት አይደለም። የኢትዮጵያዊነት ፖለቲካ ጸረ-ኦሮምኛ አይደለም። የኢትዮጵያዊነት ፖለቲካ የኦሮሞን ቅርስ ሌሎች እንደ ራሳቸው እንዲወስዱ፣ ኦሮሞኛም ኦሮሞ ብቻ ሳይሆን የኢትዮጵያዊያን ሁሉ ቋንቋ እንዲሆን የሚያደርግ ነው። የኢትዮጵያዊነት ፖለቲካ ኦሮሞነትን የሚያጠፋ ሳይሆን እንደውም የበለጠ የሚያሳድገው ነው።

እስቲ ጥያቄ ላቅርብ። በዘር ፖለቲካውና በላቲኑ ፊደል ምክንያት፣ ሰው ኦሮምኛን ጠልቶ ኦሮምኛ በተወሰኑ የኦሮሞ አካባቢዎች ብቻ ተወስኖ ቢቀር ነው ወይስ ሌላው ማህበረሰብ ኦሮሞኛም የኔ ነው ብሎ፣ ቢማረውና ቢያውቀው ነው ኦሮሞነትን ማሳደግ የሚሆነው ? በኢትዮጵያዊነት ፖለቲካ ምክንያት ኦሮሞኛ የኔ ነው በሚል፣ ኦሮሞኛ ከኦሮሞ ማበረሰብ አልፎ በሌሎች ወገኖች የሚታወቅ የሚነገር እንዲሆን ማድረግ እንዴት ተደረጎ ነው ጸረ-ኦሮሞነት የሚሆነው ?

ያለ ኢትዮጵያዊነት ፖለቲካ ኦሮሞነት የትም አይደርስም። ( የኦሮሞ ብሄረተኞች በጉልበት ስልጣን ይዘው ኦሮሞነትን በሃይል ሌላው ላይ ካልጫኑ በቀር)። በኢትዮጵያዊነት ፖለቲካ ውስጥ ግን ኦሮሞነት ያድጋል!!!!!!

ኦሮሞነት ስል ሐሳቤን እንዳትስቱብኝ፣ ኦሮሚያ ወይንም ከኦሮሚያ ጋር ግንኙነት ያለው ነገር ማለቴ አይደለም። በጭራሽ !!!!!! ኦሮሞነት ስል ላቲኑን ፊደል ማለቴ አይደለም።፡በጭራሽ። ኦሮሚያ በቅርቡ ኦነግና ሕወሃት የፈጠሯት ናት። ከኦሮሞነት ጋር ግንኙነት የላትም። ላቲን ጀርመኖች የፈጠሩትና የግእዝ/ኢትዮጵያ ጠል የሆኑ የነጭ ጥቁሮች በሕዝቡ ላይ የጫኑት ነው። ኦሮሞነት ስል ህዝቡን ባህሉን ቋንቋውንና ቅርሱን ማለቴ ነው።

ኢትዮጵያዊነት ኦሮሞነት፣ አማራነት፣ ትግሬነት፣ ከንባታነት፣ ጋሞነት….በአንድ ላይ ተገምደው የፈጠሩት ማንነት እንደመሆኑ፣ ከተገመደው ኢትዮጵያዊነት ውስጥ ኦሮሞነትም መዘን ማጥፋት አንችልም። ያንን እናድርግ ማለትም ኢትዮጵያዊነት ማጥፋት ማለት ነው።

ግንቦት ሰባቶች በአዳማ ያደረጉትን ህዝባዊ ስብሰባ ድጋፌን እየገለጽኩ፣ በሃረር ሊያደርጉት ያሰቡትን ሌላ ስብሰባም ኢ-ሕገ መንግስታዊ በሆነ መልኩ መከልከላቸው አሳሳቢ ነው። የሃረር ክልል ሃላፊዎች የወሰዱት ውሳኔ ተቀባይነት ሊኖረው አይገባም። ግንቦት ሰባቶች በሃረር ከተማ ህዝባዊ ስብሰባዉን ማድረግ አለባቸው ባይ ነኝ። በቀላሉ ማንም ዘረኛ ባለስልጣን ከልክያለሁ ስላለ መሸሽ ያለባቸው አይመስለኝም።

ከሃረር በተጨማሪ፣ በዝዋይ፣ በመቂ፣ በፍቼ ፣ በደራ፣ በወሊሶ፣ በቢሾፍቱ፣ በሰበታ፣ በቡራዪ፣ በጂማ፣ በአሰላ በመሳሰሉ ቦታዎችም በመንቀሳቀስ ለሕዝቡ አማራጭ ማቅረቡ ላይ ይበርቱ እላለሁ። ይሄን ካደረጉ ያለ ምንም ጥርጥር የግርማ ካሳ ሙሉ ድጋፍ አላቸው !!!!!!!!