በቅርቡ ማለትም በአ. አ. መስከረም ፳፰ ቀን ፳፻፲፰ ዓ. ም. ባይሳ ዋቅ ወያ የተባሉ ደራሲ፣ “በባንዲራና አርማ ዙርያ ያሉ ውዝግቦች” በሚል ርእስ የጻፉትን፣ በየድረገጹ አሰራጭተውት አየሁት። ከጽሑፋቸው መካከል ቀልቤን ይበልጥ የሳበው የሚከተለው ንግግራቸው ነው።
“አገራት ባንዲራዎቻቸውን እንደሚያመቻቸው የማንነታቸው መገለጫ አድርገው ይጠቀሙበታል። የዲሞክራሲ እንደ አንድ የአገዛዝ ሥርዓት ሥራ ላይ ከመዋሉ በፊት በነበሩት ያገዛዝ ሥርዓቶች፣ የገዢው ክፍል (ለምሳሌ ንጉሦች) ያላንዳች የሕዝብ ተሳትፎ ራሳቸው ያሰኛቸውን ቅርጽና ቀለም ያለውን ባንዲራ አሰርተው ያገራቸውና የሕዝባቸው መለያ አድርገው ይጠቀሙበት ነበር። ለምሳሌ በተለምዶ የኢትዮጵያ የምንለው ባለሶስት ቀለማት ባንዲራ ያገራችን ሕዝቦች መለያ እንዲሆን የተወሰነው በሕዝቦች ተሳትፎ ሳይሆን በአጼ ምኒልክ ውሳኔ ነበር። ያኔ በነበረው ያገዛዝ ሥርዓት፣ ንጉሥ “ስዩመ እግዚአብሔር” ስለሆነ ሕዝቡ ከንጉሡ “የተሰጠውን” እንዳለ ተቀብሎ ሥራ ላይ ማዋል እንጂ የሚፈልገውን የመምረጥ መብት ስላልነበረው፣ የራሱ ባንዲራ አድርጎ ሲጥቀምበት ኖሯል። በሌሎች አገራት ግን ዲሞክራሲያዊ የአገዛዝ ሥርዓቶች እየተስፋፉና እየተለመዱ ሲመጡ፣ የባንዲራ ምርጫም ልክ እንደ ሌሎች አገራዊ ጉዳዮች ለሕዝብ ቀርቦና ሕዝብም ተወያይቶበት የሚበጀውን ባብላጫው ድምጽ እንዲወስን ይደረግ ነበር። ዛሬም ብዙ አገራት የሚከተሉት ይህንን ልምድ ነው። ባንዲራና አገርን በተመለከተ ገዢው የዲሞክራሲ መርህ፣ አገር ቋሚ ናት፣ ባንዲራ ግን እንዳስፈላጊነቱ ሊቀየር ይችላል የሚል ነው።
አቶ ባይሳ የሙያቸው መስክ ምን እንደሆነ አላውቅም። ግን የታሪክ ምሁር እንዳልሆኑ ይኸው ጽሑፋቸው ቊልጭ አድርጎ ይመሰክራል። የታሪክ ሰው ሁነው ይኸንን ዐይነት ጽሑፉ ከጻፉ ደግሞ፣ ከታሪክ ምሁራን የሚጠበቅባቸውን መሠረታዊ መስፈርት ቅንጣት እንኳን የሚታክል ሊያሟሉ አልቻሉም የሚል ግምት ያሰጣቸዋል። በአገራችን አለመስክ ገብቶ መፈትፈት የተለመደ መሆኑን የተረዳሁት የዛሬ አራት ዓመት፣ ማለትም በአ. አ. ጥር ፬ ቀን ፳፻፲፬ ዓ. ም. አቶ አበራ ቶላ የተባሉ ጸሓፊ፣ “ስለኦሮሞ መስፋፋትና ስለምኒልክ ማስገበር ጨለማው ጐን በኢትዮጵያ [1]” በሚል ርእስ፣ የኦሮሞን በኢትዮጵያ ገጸምድር መስፋፋት ከአፄ ምኒልክ ማስገበር ጋር በማነፃፀር የጻፉትን ሳነብ ነበር። እንደተረዳሁት፣ አሳባቸው፣ በወቅቱ የኦሮሞ ሕዝብ ነፃ አውጭ እኛ ነን የሚሉ ድርጅቶች የሚያናፍሱትን የተረት ታሪክ ማስተጋባት ስለነበር፣ አቋማቸውንና እንደሰደድ እሳት እየተናኘ የነበረውን የሐሰት ትረካ በመተቸት፣“ምኒልክን ብትወቅሱ ማንነታችሁን ትረሱ” የሚል ረጅም ጽሑፍ እንዳበረክት አስገድደውኛል። ጽሑፌ እስከወጣ ድረስ፣ የድርጅቶቹ የተረት ታሪክ በሰፊው ሕዝብ ዘንድ እንደማይካድ ሐቅ ተወስዶ፣ የአፄ ምኒልክን ስም እጅግ ከማጠልሸቱ የተነሣ፣ አብዛኛው ኢትዮጵያዊ፣ የተማረ ነው የሚባል እንኳን ሳይቀር፣ የዘመናቸው ሕዝብ በፍቅራቸው ተነሽጦ፣ “እምዬ ምኒልክ” እስከማለት የደረሰውን የንጉሠነገሥቱን ስም ማንሣት እስከመፍራት ደርሶ ነበር። አሁን አቶ ባይሳና፣ እሳቸውን የመሳሰሉት እየደገሙ ያሉት፣ ይኸንኑ ዐይነት የሐሰት ትረካ ነው ማለት ይቻላል። ልዩነቱ የአሁኑ ታሪክ ባለቤት አፄው ሳይሆኑ፣ እሳቸው ፈጠሩ እየተባለ የሚወራው ሰንደቅ ዓላማ ነው። በኔ አስተያየት፣ ነፃ አውጪ ነን ባዮቹ፣ አፄ ምኒልክን የሚጠሏቸው ንጉሠነገሥቱ በደል ፈጽመውባቸው አይደለም፤ ታዲያ፣ በነጭ ዘር የጭቈና ቀንበር ሥር ወድቀው እንዳይደፈጠጡና አሁን የሚኰሩበትን ማንነታቸውንና ባህላቸውን እንዳያጡ፣ በጊዜ ደርሰው ስለታደጓቸው ብቻ ነው ማለት ይቻላል። እነዚህና እነሱን የመሰሉ አንጃዎች፣ ለአብዛኛው የጥቊር ዘርና የባርነት ቀንበር ሸክም ለከበደው ለዓለም ሕዝብ፣ የነፃነት ጩራ ሁኖ ያገለገለውን፣ የኢትዮጵያን ሰንደቅ ዓላማንም የሚያንቋሽሹት፣ በስሙ የተሠራ ግፍና በደል ኑሮ ሳይሆን፣ ለምን በባዕድ ዘረኛ እንዳንገዛ ተከላከለን ከሚል ስሜት የመነጨ ነው ብል የተሳሳትሁ አይመስለኝም። በዚህ ጽሑፍ ትኩረቴ በአቶ ባይሳ ጽሑፍና እሳቸውን የመሳሰሉ በሚያናፍሱት የተዛባ ስለሌላው ዓለም ሰንደቅ ዓላማ አመጣጥ ሲሆን፣ ባጭሩ ደግሞ የምኒልክ ‘ባንዲራ’ ብለው የሰየሙትን የኢትዮጵያን ሰንደቅ ዓላማ ይነካካል። ስለኢትዮጵያ ሰንደቅ ዓላማ አመጣጥና ታሪክ በሌላ ቦታ አጠር ባለ መልኩ፣ “የሰንደቅ ዓላማው ወንጀለኛ አርማ”” በሚል ርእስ፣ በቅርቡ ስለጻፍሁ፣ ፍላጎት ካለው እንዲመለከተው አንባቢዬን በትሕትና እጋብዛለሁ። ስለዚህ፣ የዚያን ጽሑፍ አሳብ እዚህ ላይ መድገሙ አስፈላጊ ስላልመሰልኝ፣ እንዲሁም አንባቢዬን ላላሰለች ስል በጉዳዩ ልመለስበት አልፈልግም።
ንግግሬን በጀርመናዊው ፈላስፋ ፍሬድሪኽ ሄገል ልጀምር። ሄገል የሰው ልጅ ታሪክ እንዴት እንደሚተገበር ሲገልጥ፣ በነባርና በፀረ-ነባር አሳቦች መካከል የሚፈጸመው የግጭት ሂደት ውጤት ነው ይላል። ነባር አሳብ፣ በወቅቱ ከፍተኛ ተሰሚነትና ተቀባይነት ያለው ገዢ ርእዮተ ዓለም መሆኑ ነው። የዘመኑን ተቋማት፣ ድርጊቶችና እምነቶች የሚያንቀሳቅስ ሞተር እንደማለት ነው። ፀረ-ነባር ደግሞ፣ ቃሉ እንደሚለው ገዢውን አሳብ የሚቃወምና፣ ጉልበት አግኝቶ ወደጦር ዐውድማ ገብቶ ነባሩን እስካላንበረከከው ድረስ፣ ብዙም ተደማጭነት የሌለው ርእዮተ ዓለም መሆኑ ነው። ይኸንኑ በተግባር እንይ ካልን፣ ለምሳሌ ያህል፣ እስከርስበርስ ጦርነት ድረስ፣ በአሜሪቃ አገር ጥቁሮች ጽዋቸው ባርነት መሆኑን ሁሉም ይጋራ የነበረው አስተሳሰብ ነው። የክርስቲያን ሃይማኖት መሪዎች በቅዱስ መጽሐፍ በመደገፍ፣ የጥበብና የስነልቦና ምሁራንና ተመራማሪዎች ጭምር ሳይቀሩ ሁሉም በየመስኩና በየሙያው፣ ከፍባለ ጥናታቸው ያገኙትን ተጨባጭና የማያጠያይቅ እውነት ነው የሚሉትን ማስረጃ በማቅረብ፣ አሁን የተዛባና እጅግ በጣም የተሳሳተ ነው ብለን የምናየውን፣ የጥቁርን ባርነት የሚያቀነቅነውን ወራዳ ርእዮተ ዓለም፣ በጥብቅ ማመንና ማሳመን ብቻ ሳይሆን፣ ከተራው ሰው ይበልጥ፣ ፀረ-ነባሩን ርእዮተ ዓለም በፊታውራርነት አጥብቀው የሚቃወሙት እነሱ ነበሩ ማለት ይቻላል። አሁንም በአገራችን ኢትዮጵያም ይካሄድ ያለው ሁናቴ ይኸንን የመሰለ ነው ብል የተሳሳተ ግንዛቤ አይመስለኝም። በደርግ ዘመን በማርክስና ሌኒን የተበከለው ትውልድ፣ ሌላው ቀርቶ ሣርና ከብቱ ጭምር በማኅበረሰብኣዊነትና በመደብ ትግል ዙርያ እንዲሰለፍ አድርጎ ነበር። አሁን ያ ሁሉ መና ሁኖ ቀረና፣ ዘመኑ የባለጐሣዎችና የባለክልሎች ሁኗል። ጸሓፊው አቶ ባይሳ እንግዴህ ቃሉን ቅኝ ግዛቱ ሊያደርገን ከፍተኛ ጥፋትና ውድመት ካደረሰብን ከኢጣሊያን ቋንቋ በመበደር “ባንዲራ”፣ ብለው በሚጠሩት፣ በገዛ ቋንቋችን ደግሞ “ሰንደቅ ዓላማ” በምንለው ላይ የሚያነበንቡት የነዚህን የባለጐሣዎችን ልበወለድ ትረካ ነው። የሚገርመው አሳባቸውን ብዙዎች ወደመጋራት ያዘነበሉ ይመስላል። ሌላው ቀርቶ ተራማጅና የለውጥ ፈርቀዳጅ በመባል፣ በብዙዎች ኢትዮጵያውያን ዘንድ እየተደነቁ ያሉት፣ አዲሱ የኢትዮጵያ ሕዝብ አብዮታዊ ዴሞክራሲያዊ ግንባር ሊቀ መንበር ሁነው የተመረጡት ሊቅ (ዶር.) ዐቢይ ራሳቸው፣ በቅርቡ ስለብሔራዊ ሰንደቅ ዓላማ ለአንድ ጋዜጠኛ የሰጡት መግለጫ፣ በአቶ ባይሳ አስተሳሰብ የተበከሉ መሆናቸውን ይጠቁማል እላለሁ። ከሆነ በጣም አሳሳቢ ነው ብዬ እገምታለሁ። ይኸን ካልሁ በኋላ፣ ሐተታ ላለማብዛት ወደአቶ ባይሳ ስሕተቶችና ሐሰቶች ብዬ ወደምገምታቸው አሳቦች ልዝለል።
አንደኛ፣ የአቶ ባይሳ ዋና ስሕተታቸው “ዲሞክራሲያዊ የአገዛዝ ሥርዓቶች እየተስፋፉና እየተለመዱ ሲመጡ፣ የባንዲራ ምርጫም ልክ እንደ ሌሎች አገራዊ ጉዳዮች ለሕዝብ ቀርቦና ሕዝብም ተወያይቶበት የሚበጀውን ባብላጫው ድምጽ እንዲወስን ይደረግ ነበር። ዛሬም ብዙ አገራት የሚከተሉት ይህንን ልምድ ነው። “ የሚለው ንግግራቸው ነው። ሕዝባዊ መንግሥት [ዴሞክራሲ] በሰፈኑበት አገሮች እንኳን ሳይቀር፣ ሕዝብ ተወያይቶ የወሰነ ሰንደቅ ዓላማ በታሪክ እንዳለ እኔ በጥናቴ አልደረስኩበትም። ካለም ጸሓፊው ንግግራቸውን በማስረጃ ማስደገፍ ይገባቸዋል ብቻ ሳይሆን አስፈላጊም ነው። ግን ጠቅላላ ማስታወቂያ ከመንገር ውጭ ያደረጉት ቁም ነገር የለም። እኔ እንደደረስሁበት፣ የሰንደቅ ዓላማዎች ቅርጽና ቀለማት የተወሰኑት በዘፈቀደ ወይንም በሰፊው ሕዝብ ምርጫ ሳይሆን፣ የያንዳንዱን አገር ታሪክንና ባህልን አለበለዚያም ሃይማኖትን መሠረት በማድረግ ነው። ወሳኞቹና መራጮቹ ገዢዎችና የአገሩ መሪዎች እንጂ በጠቅላላ ሕዝብ ሁኖ አያውቅም። እስኪ ታሪክን በአጭሩ እንቃኝ።
የአፍሪቃ ሰንደቅ ዓላማዎች፣ አገራቸው ከአውሮጳውያን ቅኝ ግዛት ሊላቀቁ ሲታገሉ በነበረበት ወቅት፣ ለዚህ ቅዱስ ዓላማ በአንድ ላይ ያሰለፈቻቸውና፣ እንደአብነትና የድላቸው ዋስትና ሁና ያገለገለቻቸው ኢትዮጵያ በመሆኗ፣ ነፃነታቸውን ሲቀዳጁ፣ ከአገራችን ጋር ያላቸውን የታሪክና የሥነምድር (ጂዎግራፊ) ትስስራቸውን ለማሳየት ሲሉ፣ አብዛኞቹ የሰንደቅ ዓላማቸው ቀለማት፣ የኢትዮጵያን ያማከለ እንዲሆን መርጠዋል። በፈረንሳይ ሥር ለነበሩት ዋኖቹ ቀለማት አረንጓዴ፣ብጫ፣ ቀይ ሲሆኑ፣ አቀማመጣቸውን ከላይ ወደታች ቀጥ ያለ አደረጉ። በእንግሊዞች ሥር ለነበሩት ደግሞ፣ አደራደሩ በአግድሞሽ ሁኖ፣ የአብዛኞቹ ምርጫቸው ከአረንጓዴ፣ ሰማያዊ፣ ጥቍርና ነጭ ቀለሞች ዙርያ እንዲሆን ተወሰነ። የሁለተኛዎቹ የቀለማቸው መብዛት ምክንያት የጥቁሮች መብት አቀንቃኝ የነበረው ጃማይካዊው ማርኩስ ጋርቬይ የጥቊር ሕዝብ ሰንደቅ ዓላማ ብሎ ያወጃቸውን ቀለማትን በማካተታቸው ነው። ማርኩስ ጋርቬይ ለጥቊር ሕዝብ ሰንደቅ ዓላማ ምልክት የመረጠው የኢትዮጵያን ቀለማት ቢሆንም፣ በወቅቱ በደረሰለት ስሕተተኛ መረጃ ምክንያት፣ ቀለማቱን ሊያዛባ በቅቷል ይባላል። ዋናው ቁም ነገር፣ እነዚህን ቀለማት የመረጡት የነፃነቱ ትግል መሪዎች እንጂ፣ የአገሩ ሕዝብ መክሮበት አይደለም። ከመሪዎቹ ብዙዎቹ በፈጸሙት ግፍ፣ ወይንም በመባለግ መንግሥታቸው ሲገለበጥ፣ ወይንም እነሱ ከሥልጣን ሲባረሩ፣ በሥራቸው ክፋት ምክንያት ወይንም ያንድ የተወሰነ ጐሣ አባል ስለነበሩና፣ ወገኔንና ክልሌን ስለማይወክሉ፣ ሰንደቅ ዓላማው ይቀየር ያለ አገር፣ ወይንም ሕዝብ እንዳለ፣ እስካሁን አልተሰማም።
ወደአውሮጳ ከመጣን ደግሞ፣ እጅግ ጥንታውያን ናቸው የሚባሉት ሰንደቅ ዓላማት የመስቀል ምልክት ያላቸው ናቸው። እነሱም እጅግ በጣም አጸያፊ የነበረው፣ የመካከለኛው ዘመን የመስቀል ጦርነቶች መሪዎች የነበሩት ይጠቀሙ ከነበሩት የተወረሱ ናቸው። ከነዚህ መኻል፣ የታላቂቷ ብሪታኒያን፣ የእስካንድናቭ አገሮችን (ኖርዌይ፣ እስውድን፣ ፊንላንድ፣ ዴንማርክ)፣ እንዲሁም የግሪክን መጥቀስ ይቻላል። የቤልጁም፣ የሁንጋሪ፣ የሉክሰምቡርግ፣ የሞናኮ፣ የእስጴንና የፖላንድ የመሳሰሉት አገሮች ቀለማት ደግሞ የየአገራቸው ነገሥታት በ፲፪ኛና በ፲፫ኛ ዘመነምሕረታት ይጠቀሙ ከነበሩት ከባለአርማው ጋሻ ጋር የተያያዙ ናቸው። አውስትርያ፣ ሳንማሪኖና ለይቼስቴይን የተባሉት ሁለቱ የመሳፍንት ግዛቶች አሁንም ቢሆን ባለአርማ ጋሻውን ጭምር አልተውትም። እንግዴህ እነዚህን ሰንደቅ ዓላማትና ቀለሞቻቸውን የመረጡት ነገሥታትና መሳፍንት መሆናቸው ግልጽ ነው። ከነዚህ አብዛኞቹ እጅግ በጣም ግፈኞች እንደነበሩ አይካድም። ግን አስተዳደሩ ወደሕዝባዊ መንግሥት ሲቀየር፣ ሕዝቡ ሰንደቅ ዓላማው አይወክለንምና ይቀየር አላለም፤ ስለሰንደቅ ዓላማው ምርጫ ተሰጥቶት የተጠየቀበትም፣ ድምጹን የሰጠበትም ጊዜ አልነበረም።
አሜሪቃም በከዋክብትና በጥለቶች ላጌጠው ሰንደቅ ዓላማዋ የመረጠቻቸው ቀለማት፣ በፊት ጠላቴ ብላ በጽኑ ከተዋጋችው እንግሊዝ ነው። ሁላችንም እንደምናውቀው፣ “ዩኒዮን ጃክ” በመባል የሚታወቀው የእንግሊዝ ሰንደቅ ዓላማ በበኩሉ ያካተተው፣ አንድነቱን የፈጠሩትን የሦስቱን አገሮች ጠባቂዎች የሆኑትን ቅዱሳንን፣ ማለትም የእንግሊዝን ቅዱስ ጊዮርጊስ፣ የእስኮትላንድን ቅዱስ እንድርያስና የአየርላንድን ቅዱስ ፓትሪክ አርማዎችን ነው። ቀለማቱ የተወሰኑት ባላባታዊ ሥርዐት ያራምዱ በነበሩ ነገሥታቱ ሲሆን፣ ሕዝባዊ መንግሥት ከተቋቋመም በኋላ፣ የአቈርቋዥና ጊዜው ያለፈበት ሥርዐት ቅሪት ነው ተብሎ እስካሁን አልተወገደም። እነዚህን ቀለማት ነው እንግዴህ ከጨቋኟ እንግሊዝ በታሪክ ስለሚያተሳሰሯት ብቻ፣ ዛሬ አሜሪቃ ለሰንደቅ ዓላማዋ እየተጠቀመች ያለችው። የጠላት ብቻ ሳይሆን፣ ዘመኑ ያለፈበትን የባላባትን ሥርዐት የሚያንፀባርቅ ነው ብላ ወግድ አልጠቀመውም አላለችም። ይሁንና በውሳኔው ላይ የአሜሪቃ ሕዝብ ድምፁን እንዲሰጥ የተጠየቀበትና የተወያየበት ወቅት እንደነበረ እኔ እስካሁን አልሰማሁም።
ከአውሮጳ ወጣ ስንል፣ አብዛኞቹ የእስልምና እምነት ተከታዮችንም ሆነ፣ ሌሎቹን የእስያን አገሮች ያየን እንደሆነ የምንረዳው ይኸንኑ ሐቅ ነው። በሕዝብ ፍላጎት የተወሰነ ሰንደቅ ዓላማ የለም። ወሳኙ ገዢው ክፍል ነው። ያውም ብዙውን ጊዜ ጨቋኝና አሁን አንገሽጋሽ ሥርዐት ነው ተብሎ የሚታሰበውን ያራምድ የነበረ። የወሰነው ታሪክ፣ ባህልና እምነት በማማከል ነው። የእስልምና እምነት ተከታይ አገሮች ሰንደቅ ዓላማዎች አብዛኞቹ ባለሦስት ቀለማት ሲሆኑ፣ እነሱም የተመረጡት ከእምነታቸው ጋር ተቈራኝተው ከቈዩት ከዐራቱ ቀለማት፣ ማለትም ቀይ፣ ነጭ፣ አረንጓዴና ጥቊር መካከል አንዱን ወይንም አብዛኛውን ለይቶ በመውሰድ ነው። ጥቂቶቹ እንደነቱርክ፣ ቱኒስና አልጄርስ፣ እንዲሁም ማሌዢያና ፓኪስታን የመሳሰሉት፣ የእምነታቸው ምልክት ስለሆኑ፣ ኮከብና ግማሽ ጨረቃ ያካትታሉ። የእስያ አገሮችን በተመለከተ፣ አብዛኞቹ በአውሮጳውያን የተገዙ ናቸው። ግን ከአፍሪቃውያን በተለየ መልኩ፣ ከመገዛታቸው በፊት የየራሳቸው ብሔራዊ መለዮ ምልክቶች ነበሯቸው። የባዕዱን ቀንበር የሰበሩትም ሆኑ፣ ጽዋውን ያልቀመሱት፣ አሁን የሚጠቀሙት፣ ታሪካዊ የሆነውን የጥንቱን መንፈሳዊና ፖለቲካዊ ምልክቶችን በደማቅ ቀለም ላይ ያሰፈረ ሰንደቅ ዓላማ ነው። ስለዚህ፣ እንደታይዋን፣ ነፓልና ጃፓን የመሳሰሉ አገሮች የፀሐይ ምስል፤ ህንድ የመንኰራኲር፣ ብሑታን የዘንዶ፣ ስሪላንካ የሰይፍ አርማ በሰንደቅ ዓላማቸው ላይ ያሰፈሩት በጥንት ታሪክ፣ በሥነምድርና በሃይማኖት ላይ ተመሥርተው ነው። እነዚህም የተመረጡት በነገሥቶቻቸውና ቅኝ ገዢዎቹን በተኩት መሪዎቻቸው ውሳኔ እንጂ በሕዝብ ፍላጎት አይደለም።
የፈረንሳይ አብዮት መሪዎች ሰንደቅ ዓላማቸውንና ቀለሞቹን የተዋሱት የአገራቸው ባላንጣ ከነበረችው ከኔዘርላንድ ነው። አብዛኞቹ የላቲን አሜሪቃዎቹ አገሮች መሪዎች በተራቸው የቀዱት የፈረንሳይ ሰንደቅ ዓላማ ቀለማትን ነው። አንዱ ከሌላው እንዲቀዳ ያደረጋቸው ተመሳሳይ ታሪክ ወይንም የሥነምድር ትስስር ስላላቸው እንጂ በፈረንሳዊነት ስለሚዛመዱ አይደለም። ኔዘርላንድንም ሆነ የላቲን አሜሪቃን አገሮች ለብዙ ዘመናት ትገዛ የነበረችው እስጴን ነበረች። ለብዙ ዓመታት ተዋግታት እስጴንን ሲታሸንፍ፣ ኔዜርላንድ ለፈረንሳይ አብዮት መሪዎች አብነት ሆነችላቸው፤ ልክ ኢትዮጵያ ለአፍሪቃ ተምሳሌት እንደነበረች ማለት ነው። በፈረንሳይ አብዮት ተነሽጠው፣ ከእስጴን ቀንበር የተላቀቁት የላቲን አሜሪቃ መሪዎች ደግሞ፣ የተዋሱት የፈረንሳይን ሰንደቅ ዓላማ ቀለማት ነው። እስጴንን የተዋጉት በፈረንሳይ አብዮትና አሳቦች ተነሣሥተው ስለነበር ማለት ነው።
ያም ሆነ ይህ፣ ዋናው ነገር የሰንደቅ ዓላማ ጉዳይ የተወሰነው አገሮቹ የቈየ ታሪክ ካላቸው በነገሥታቱ፣ ለመንግሥትነት የበቁት በቅርብ ጊዜ ውስጥ ከሆነ በታሪክና በሥነምድር ከሚተሳሰረው አገር በመቅዳት ነው። ወሳኞቹ ነፃ አውጪዎቹ እንጂ፣ ጸሓፊው እንደሚለው፣ “እንደ ሌሎች አገራዊ ጉዳዮች ለሕዝብ ቀርቦና ሕዝብም ተወያይቶበት የሚበጀውን ባብላጫው ድምጽ” የተወሰነ ሰንደቅ ዓላማ ካለ እስካሁን ድረስ አላጋጠመኝም። እውነት ነው ይኸንን ሕግ በቅርቡ ያልተከተሉት የቀድሞው የእንግሊዞች ግዛት የነበሩት ኒውዜላንድና አውስትራሊያ እንዲሁም ካናዳ ሲሆኑ፣ የነዚህም ምክንያታቸው ግልጥ ነው። አንደኛ፣ ነፃ አገሮች ቢሆኑም፣ ከቀድሞ ገዢአቸው ከእንግሊዝ ሙሉ በሙሉ አለመላቀቃቸውና ያገሩ ባለቤት የነበረውን ሕዝብ በግልጥ ካለማካተት በተፈጠረ ውዝግብ መሆኑ መረሳት የለበትም። ሁለተኛ፣ ከነዚህም መካከል ውሳኔውን ለሕዝብ ድምፅ ያቀረበችው ኒውዜላንድ ብቻ ስትሆን፣ ውጤቱም አጥጋቢ ካለመሆኑ የተነሣ፣ ድርጊቱ የብዙ ሚሊዮን ወጪ ዕዳ ባገሯ ላይ ከመጫን ውጪ ምንም ያመጣው ለውጥ የለም። ሰንደቅ ዓላማውም ቢሆን አልተቀየረም። በተጨማሪ፣ የድሮውን ትተው አዲስ ሰንደቅ ዓላማ ከቀየሩት ሊቢያ፣ ቬነዙወላ፣ እንዲሁም የድሮው ቡርማ፣ የዛሬው ማይናማር ሊጠቀሱ ይችላሉ። ግን ወሳኙ ሕዝብ ሳይሆን፣ የየአገሩ መሪ ነው። ይልቅስ አንድ የሚገርም ነገር ቢኖር፣ የሊቢያው መሪ የነበሩት ኮሎኔል ገዳፊ ከዓለም ሰንደቅ ዓላማዎች ሁሉ እጅግ አስቀያሚ የሚል ግምት ያፈራውን የአገራቸውን ሰንደቅ ዓላማ የተኩት፣ በ፱፻፱ና በ፲፩፻፸፩ ሰሜን አፍሪቃን ይገዙ በነበሩት በፋጥሚዶች ሥርወ መንግሥት ሰንደቅ ዓላማ ነው።
ሁለተኛው የአቶ ባይሳ ከፍተኛ ስሕተት፣ የኢትዮጵያን ሰንደቅ ዓላማ እጅግ በጣም በተሳሳተ መልኩ ከአፄ ምኒልክ ጋር ማያያዛቸው ነው። በፍጹም ትክክል አይደለም። የኢትዮጵያ ጥንታዊነት ከማንኛውም በላይ ከተጠቀሱት አገሮች ይበልጣል እንጂ አያንስም። ስለዚህ ረጂም የሰንደቅ ዓላማ ታሪክ ያላት አገር ናት። አፄ ምኒልክ የፈጸሙት ነገር ቢኖር፣ በፊት በተናጠል ይንጠለጠሉ የነበሩትን ሦስቱን የሰንደቅ ዓላማ ቀለማት በአንድ ላይ ማሰፋታቸው ነው። አዲስ ሰንደቅ ዓላማና ቀለማት አልፈጠሩም። ሌላው ያደረጉት ተጨማሪ ነገር ቢኖር፣ በሕግም በመደንገግ የሰንደቅ ዓላማው ባለቤት ኢትዮጵያ መሆኗን ለመላው ዓለም በማስታወቅ የዘመናዊነትን ቅርጽ ሰጡ። እሳቸው በሰጡት ዕውቅናና ዐዋጅ ተነሥተው ነው እንግዴህ፣ በነጭ ዘር የጭቈና ቀንበር ሥር ይማቅቅ የነበረው ጥቊር ሕዝብና ነፃነት የጠማው ሁሉ የኢትዮጵያን ሰንደቅ ዓላማ ቀለማት አሰላለፋቸውን እየቀየሩ የራሳቸው በማድረግ ለአገራችን ውለታቸውን ሊገልጡ የፈለጉት። ቀለማቱ የሚያንጸባርቁት በአካባቢው የነበሩት የተለያዩ ግዛቶች ይጠቀሙ የነበሩትን፣ እንዲሁም ታሪክንና ሥነምድርን (ጂዎግራፊ) በማስደገፍ የተመረጡ እንጂ ከተወሰነ ብሔረሰብ ወይንም አምነትና አካባቢ ጋር የተያያዙ አይደለም። ይኸ ሰንደቅ ዓላማ ከሌሎቹ የሚለየው፣ በጥንታዊነቱ ብቻ ሳይሆን፣ በታሪክነቱም ራሱ አዋሓጅና ደማሪ፣ እንዲሁም የነፃነት አብሳሪ ሁኖ እንጂ ጨቋኝነትን አንፀባርቆ አያውቅም። ስለዚህም ነው የነፃነት ታጋዮች ቀለማቱ የራሳቸው አገር የመለዮ ምልክታቸው እንዲሆን የመረጡት። ከዚህም ጥንታዊነቱና፣ ታሪካዊ መልእክቱ ተነሥተው ነው እንግዴህ የአፋሩ አገር መሪ ክቡር አቶ አሊ ምራሕ “የኢትዮጵያን ሰንደቅ ዓላማ”፣ እኛ የአገሪቷ ዜጎች ቀርተን፣ “ግመሎቻችንም እንኳን ያውቁታል” ሊሉ በቁ የሚባለው።
እውነቱ እንደዚህ ሁኖ ሳለ፣ አሁን ያለውን ሰንደቅ ዓላማ፣ ያለአንዳች ማስረጃ፣ እንደአቶ ባይሳ፣ ከአፄ ምኒልክ ጋር አሳብቦ፣ ወይንም “የንጉሦቹ” ስለሆነ ለሕዝብ ቀርቦና ሕዝብም ተወያይቶበት “ዛሬ ብዙ አገራት እንደሚከተሉት” በአብላጫው ድምፅ ይወሰን የሚሉት፣ እነሱ የሚፈልጉትን ዓላማ ብቻ ለማራመድ መሆኑ ግልጽ ነው። ታዲያ፣ “አያ ጅቦ ሳታመካኝ ብላኝ” ይላል የአገሬ ሰው።
[1] . Abera Tola, “Ethiopia: Dark Side of Oromo Expansions and Menilek Conquests,” Ethiomedia, January 4, 2014.