ኢትዮጵያ የህዳሴ ግድቡ ለደኅንነት ሥጋት ባለመሆኑ የፀጥታ ምክር ቤት አጀንዳ እንዳይሆን ጠየቀች


መረጃ ቲቪ አባል በመሆን የሳተላይት ቲቪውን ቀጥታ ስርጭት፣ ወቅታዊ ዜናዎችን እና ትንተናዎችን፣ የመዝናኛ ፕሮግራሞችን፣ ስፖርት እና ሌሎችንም ዝግጅቶቻችንን በፍጥነት እና ጥራት ስልክዎ፣ ኮምፒዩተርዎ ወይም ቲቪዎ ላይ ማየት ይችላሉ። እዚህ ሊንክ ላይ በመጫን አባል ይሁኑ


Reporter Amharic :- ኢትዮጵያ ለተባበሩት መንግሥታት ድርጅት (ተመድ) የፀጥታ ምክር ቤት በላከችው ደብዳቤ፣ ግብፅና ሱዳን በኢትዮጵያ ላይ የጦርነት ነጋሪት ከመጎሰም አልፈው ወታደራዊ ስምምነት መፈራረማቸው እንዲታወቅላት አመለከተች።

ግብፅና ሱዳን ከጦርነት ማስፈራሪያ አልፈው ወታደራዊ ስምምነት መፈራረማቸውን ኢትዮጵያ ለተመድ አመለከተችበምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደመቀ መኰንን ተፈርሞ ከአንድ ሳምንት በፊት ለተመድ የፀጥታ ምክር ቤት የተላከው የኢትዮጵያ ደብዳቤ እንደሚያመለክተው፣ ግብፅና ሱዳን በአፍሪካ ኅብረት አማካይነት ሲደረግ የነበረው ድርድር እንዲስተጓጎል በማድረግ ጉዳዩን ወደ ዓለም አቀፍ የዲፕሎማሲ መድረኮች በመውሰድ፣ በኢትዮጵያ ላይ ጫና ለመፍጠር እየሞከሩ ነው።

ሁለቱ አገሮች ኢትዮጵያ በምትገነባው የህዳሴ ግድብ ላይ ያላቸውን ልዩነት በተጀመረው ድርድር ከመፍታት ይልቅ፣ ጉዳዩን ባለፈው ዓመት ወደ ተመድ የፀጥታ ምክር ቤት አቅርበው የነበረ ቢሆንም፣ ምክር ቤቱ በአፍሪካ ኅብረት በኩል በድርድር እንዲፈታ መወሰኑን ደብዳቤው ያስታውሳል።

በዚህ ውሳኔ መሠረት በአፍሪካ ኅብረት አማካይነት ሲደረግ የነበረውን ድርድር በተለያዩ ተገቢ ያልሆኑ ምክንያቶች እንዲስተጓጎል በማድረግ፣ ጉዳዩን የፀጥታና የደኅንነት ሥጋት አድርገው ከዓውዱ ውጪ በመሳል ጫና ለመፍጠር ጥረት በማድረግ ላይ መሆናቸውንም ይገልጻል።

ኢትዮጵያ በዘንድሮው ዓመት በግድቡ ሁለተኛውን ዙር ውኃ ለመያዝ እየተዘጋጀች ባለችበት በዚህ ወቅት፣ ግብፅና ሱዳን የጦርነት ነጋሪት እየጎሰሙ እንደሚገኙ የሚገልጸው የኢትዮጵያ መንግሥት ደብዳቤ፣ አገሮቹ ከጦርነት ነጋሪት አልፈው በመሄድ የሁለትዮሽ ወታደራዊ ስምምነት በመፈራረም የኢትዮጵያ መንግሥትን ለማስጠንቀቅ እየሞከሩ መሆኑን አስታውቋል።

ይህ የሁለቱ አገሮች አካሄድ የአፍሪካ ችግሮችን በአፍሪካዊ መንፈስ ለመፍታት የአፍሪካ ኅብረት ላስቀመጠው መርህ ክብርና ግድ እንደሌላቸው ግልጽ ማሳያ ብቻ ሳይሆን፣ የዓባይ ወንዝን በኢፍትሐዊነት ለብቻቸው እንዲጠቀሙ ያደረጋቸው የቅኝ ግዛት ስምምነት ከተነካ አካባቢውን በግጭት ለማተራመስ ያላቸውን እኩይ ፍላጎት ጭምር የሚገልጽ እንደሆነ ደብዳቤው ያመለክታል።

ይህ ጠብ አጫሪ አካሄድ ዘላቂ የሆነ ቀጣናዊ ሰላምና ትብብር ለመፍጠር አስፈላጊ የሆነውን የጋራ መግባባትና መተማመን እንዳይመሠረት የሚያደርግ፣ ለማንም ጠቃሚ ያልሆነ ዝንባሌ እንደሆነ ኢትዮጵያ በዚሁ ደብዳቤዋ አስታውቃለች።

በመሆኑም ይህ ያልተገባ አካሄድን ለተመድ የፀጥታው ምክር ቤት ማሳወቅ ተገቢነት በማመን፣ ከህዳሴ ግድቡ አለመግባባት ጋር ተያይዞ መስተዋል የጀመሩ አዳዲስ ክስተቶችን የፀጥታ ምክር ቤቱ እንዳያውቃቸው ማድረግ አስፈላጊ መሆኑን ጠቅሳለች።

ኢትዮጵያ የምትገነባው የህዳሴ ግድብ ገና ያልተጠናቀቀ፣ ውኃ የማይፈጅ የልማት ፕሮጀክት በመሆኑ ፈጽሞ የደኅንነት ሥጋት እንዳልሆነ ገልጻለች።

በመሆኑም ግብፅና ሱዳን ጉዳዩ ዓለም አቀፍ የደኅንነት ሥጋት እንደሆነ አድርገው ለተመድ የፀጥታ ምክር ቤት አቤቱታ ማቅረባቸው ተገቢነት የሌለው መሆኑን በመጥቀስ፣ የፀጥታ ምክር ቤቱ በዚህ የቴክኒክ ጉዳዮችን የተመለከቱ ልዩነቶች ብቻ የሚስተዋሉበት የልማት ፕሮጀክትን አጀንዳ አድርጎ ሊመክርበት እንደማይገባና ይህንንም የማድረግ ሥልጣን እንደሌለው ደብዳቤው ያመለክታል።

ግብፅና ሱዳን ጉዳዩን ወደ ፀጥታው ምክር ቤት ያቀረቡት አንድም የፀጥታ ምክር ቤቱን የሥልጣን ክልል ካለመረዳት፣ አልያም ሆን ብለው ለማደናገር ሊሆን እንደሚችል ጠቁሟል።

Reporter Amharic