ፌስቡክ መቀመጫቸውን ግብጽ አድርገው ‘ኢትዮጵያ ላይ አነጣጥረዋል’ ያላቸውን አካውንቶች ዘጋ


መረጃ ቲቪ አባል በመሆን የሳተላይት ቲቪውን ቀጥታ ስርጭት፣ ወቅታዊ ዜናዎችን እና ትንተናዎችን፣ የመዝናኛ ፕሮግራሞችን፣ ስፖርት እና ሌሎችንም ዝግጅቶቻችንን በፍጥነት እና ጥራት ስልክዎ፣ ኮምፒዩተርዎ ወይም ቲቪዎ ላይ ማየት ይችላሉ። እዚህ ሊንክ ላይ በመጫን አባል ይሁኑ


ፌስቡክ መቀመጫቸውን በግብጽ አድርገው በኢትዮጵያ ላይ ያነጣጠረ መልዕክት የሚያስተላልፉ ገፆችን መዝጋቱን አስታወቀ።

እነዚህ ገጾች እና አካውንቶች ራሳቸውን ለማስተዋወቅ 525 ሺህ ዶላር ወይንም 21 ሚሊዮን የኢትዮጵያ ብር ማውጣታቸው ተገልጿል።

ኩባንያው እነዚህ ገጾች የተዘጉበትን ምክንያት ሲገልፅ የውጭ አገራት ጉዳይ ውስጥ አለመግባት የሚለውን ፖሊሲ በመጣሳቸው እንዲሁም እውነተኛ ያልሆነ ዘመቻ ውስጥ በመሳተፋቸው እንደሆነ ገልጿል።

ፌስቡክ ይፋ ባደረገው ሪፖርት ላይ “ግብጽ ተቀምጠው በኢትዮጵያ፣ በሱዳን እና በቱርክ ላይ ያነጣጠሩ 17 የፌስቡክ አካውንቶችን፣ ስድስት ገጾችን እንዲሁም ሦስት የኢንስታግራም አካውንቶች አጥፍተናል” ብሏል።

ድርጅቱ ይህንን ያስታወቀው፣ በዚህ ዓመት መጋቢት ወር ላይ የተቀናጀ ሐሰተኛ ባህሪያት በሚል ባወጣው ሪፖርት ላይ ነው።

በዚሁ በተገለፀው ወር ውስጥ በ11 አገራት ተቀምጠው “ሐሰተኛ ዘመቻ” ሲያሰራጩ ደርሼባቸዋለሁ ያላቸውን 14 ኔትወርኮችን ማጥፋቱን ገልጿል።

ግብጽ መቀመጫቸውን አድርገው ኢትዮጵያ ላሉ ተከታዮች መልዕክት ከሚያስተላልፉ ገፆች መካከል አንደኛው “በኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ላይ ትችት የሚያቀርብ” እንደነበር ፌስቡክ አስታውቋል።

ፌስቡክ ከእነዚህ ኔትወርኮች ጀርባ ያሉት ግለሰቦች እውነተኛ እንዲሁም ሐሰተኛ አካውንቶችን በማቀላቀል በመጠቀም፣ ስማቸውን ጭምር የሚቀያይሩ ነበሩ ሲል አስታውቋል።

በፈረንጆቹ አቆጣጠር ታኅሣሥ ወር ላይ ድርጅቱ ከ2000 በላይ የሚሆኑ ሐሰተኛ አካውንቶች፣ ገጾች እና ቡድኖችን ማጥፋቱን ቢቢሲ ዘግቧል።