ከህወሓትና ከኦነግ ሸኔ አመራሮች የጥፋት ተልዕኮ የተቀበሉት የጋምቤላው ባለሐብት የክስ መቃወሚያ ውድቅ ተደረገ

  • እነ ሜጀር ጄኔራል ክንፈ ዳኘው ከመርከብ እና ከሆቴል ግዢ ጋር ተያይዞ የመከላከያ ምስክር እንዲያሰሙ ፍርድ ቤቱ ቀጠሮ ሰጥቷል።

በጋምቤላ ክልል በእርሻ ስራ ላይ የተሰማሩት ባለሃብት አቶ አለም ደስታ ሃየሎም ያቀረቡት የክስ መቃወሚያ በሙሉ ውድቅ ሆነ።

የክስ መቃወሚያቸውን ውድቅ ያደረገው የፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምደብ 2ኛ የጸረ ሽብርና ህገመንግስታዊ ጉዳዮች ወንጀል ችሎት ነው።

ተከሳሹ አቶ አለም ደስታ ዐቃቤ ህግ በመሰረተባቸው ህገ መንግስቱና ህገመንግስታዊ ስርዓቱን በሃይል ለማፍረስ ሙከራ ወንጀል ክስ ላይ፤ ከጥር 1 ቀን 2012 ዓ.ም ጀምሮ የኦሮሚያ ክልል እንዳይረጋጋ እና ክልሉ የጦርነት ማዕከል እንዲሆን እንዲሁም የፌደራል መንግስት እንዲፈርስና የመንግስት ስልጣንን ከህገ መንግስት ስርዓት ውጪ በሆነ መንገድ ለመያዝ በማሰብ ሲሰሩ እንደነበር በክሱ ተመላክቶ ነበር።

ሰኔ 19 ቀን 2012 ዓ.ም ደግሞ ከኦነግ ሸኔ ተወካይ ጋር ተገናኝተው በምዕራብ ወለጋ እና ኢሉባቡር ዞኖች በህወኃት ቡድን ስለሚደረገው የገንዘብና የቁሳቁስ ድጋፍ ለመነጋገር ከአምባሳደር አዲስ አለም ባሌማ ጋር በሚሰሩበት መንገድ ትራንስፖርት ሚኒስቴር መስሪያ ቤት የኢትዮጵያ ፖስታ አገልግሎት ድርጅት አምስተኛ ወለል ላይ በሚገኘው ቢሮ መግባታቸውን ዐቃቤ ህግ በክሱ መጥቀሱ ይታወቃል።

በተጨማሪም ተከሳሹ በምዕራብ ወለጋ የሚገኘውን የኦነግ ሸኔ ታጣቂዎችን ጎብኝተው ወደ ጋምቤላ ተመልሰው መሄዳቸው እና ታጣቂዎቹ ከመከላከያ ሰራዊት ጋር ጦርነት ላይ ስለመሆናቸው አስቸኳይ ድጋፍ ለኦነግ ሸኔ እንዲደረግ ከዶክተር ደብረጽዮን ገብረሚካኤል ጋር መነጋገራቸውን ጠቅሶ ነበር።

ተከሳሹ ዐቃቤ ህግ ያቀረበው ክስ ተገቢነት የለውም በማለት መቃወሚያ ያቀረቡ ሲሆን፥ ፍርድቤቱ መቃወሚያቸውን ውድቅ አድርጎታል።

በዛሬው ችሎት ዐቃቤ ህግ ከክሱ ጋር የምስክር ማስረጃ አያይዞ እንዲያቀርብ ለዛሬ የታዘዘ ቢሆንም ማስረጃው ተያይዞ ባለመቅረቡ በቀጣይ ቀጠሮ ማስረጃውን አይይዞ እንዲያቀርብ እና ብይን ለመስጠት ፍርድቤቱ ለሚያዚያ 4 ቀን 2013 ዓ.ም ተለዋጭ ቀጠሮ ሰጥቷል።

– በሌላ በኩል በከፍተኛ ፍርድ ቤት ከግዢ መመሪያ ውጪ የእርሻ ትራክተሮችን በተጋነነ ዋጋ ግዢ በመፈጸም ስልጣንን ያለአግባብ መገልገል የሙስና ወንጀል የተከሰሱት፤ የቀድሞው የሜቴክ ዋና ዳይሬክተር የነበሩት ሜጀር ጄኔራል ክንፈ ዳኘውን ጨምሮ ስምንት ተከሳሾች የመከላከያ ምስክር እንዲያሰሙ ፍርድ ቤቱ ተለዋጭ ቀጠሮ ሰጥቷል።

ተከሳሾቹ ላይ ዐቃቤ ህግ በ2004 ዓ.ም ከ1 ሺህ 120 በላይ በተከናወነ የእርሻ መሳሪያ ትራክተሮች ግዢ የእርሻ ትራከተሮቹ ያለ ጥቅም በመቆየታቸው እና የነዳጅ ማጠራሚያ ታንከራቸው የፈነዳ በመሆኑ በመንግስት ላይ ከ119 ሚሊየን 856 ሺህ ብር በላይ ጉዳት መድረሱ ተጠቅሶ መከሰሳቸው ያታወሳል።

ይህን ክስ ተከትሎ ዐቃቤ ህግ የሰነድና የሰው ምስክር አሰምቶ ያጠናቀቀ ሲሆን የተከሳሾቹን መከላከያ ምስክር ለመስማት ከነገ በስቲያ ለመጋቢት 29 ቀን ተለዋጭ ቀጠሮ ተሰጥቷል። እነ ሜጀር ጄኔራል ክንፈ ዳኘው ከመርከብ እና ከሆቴል ግዢ ጋር ተያይዞ ክስ ተመስርቶባቸው እንደነበር ይታወሳል።