በጅምላ በግፍ የተገደሉ ወገኖቻችን ሬሳ በግሬደር እየተጋዘ ጉድጓድ ውስጥ መጣሉና መቀበሩ የበለጠ ግፉን አግዝፎታል – አበበ ገላው

Image may contain: 1 person, smiling, sitting, drink, coffee cup, closeup and indoorአበበ ገላው — በቤንሻንጉል ክልል በተለይ በአማራው ላይ እየተፈጸመ ያለው የግፍ ጭፍጨፋ ብዙ ህዝብ እያሳዘነ ያለ ክስተት ነው። ጭፍጨፋውና በግፍ መፈናቀሉ አልቆመም። ለዚህም የክልሉ አስተዳደርም ይሁን የፌዴራል መንግስት በየደረጃው ሃላፊነት መውሰድ ይገባቸዋል።
ከሰሞኑም በጅምላ በግፍ የተገደሉ ወገኖቻችን እሬሳ በጅምላ በግሬደር እየተጋዘ ጉድጓድ ውስጥ መጣሉና መቀበሩ የበለጠ ግፉን አግዝፎታል። በባህላችን እሬሳ ክብር አለው። ለዚህም አጸያፊ ድርጊት ትእዛዝ የሰጡና ያስፈጸሙ ባለስልጣናት ተጠያቂ መሆን ይገባቸዋል። ይሁንና ይሄንን ግፍ ለፖለቲካ ትርፍ ሲባል ብቻ መነጻጸር ከማይገባው ጉዳይ ጋር ማነጻጸር ልዩነትንና ቅራኔን በህዝቦች መካከል የበለጠ ከማስፋት የዘለለ ፋይዳ የለውም።
Image may contain: one or more peopleአጊቱ ጉደታ የታላላቅ አለም አቀፍ ሚድያ ተቋማትን ትኩረት የሳበች ፋና ወጊ የሆነች ለፍቶ አዳሪ ኢትዮጵያዊ ነበረች። በስደት በምትኖርበት ጣልያን በአይነቱ ለየት ያለ የግብርና ህይወት በመምረጥ ፍየል እያረባች የፍየል አይብ ምርት እየሸጠች ከራሷ አልፋ ሌሎች ስደተኞችን እየረዳች የምትኖር አርአያና ታታሪ ሴት ነበረች። ይህቺ ወገናችን በቀድሞ ሰራተኛዋ በአሰቃቂ ሁኔታ ተደፍራ በመዶሻ ተቀጥጣ መገደሏ አለምን ሁሉ ያሳዘነ ጭካኔ መሆኑ በስፋት ተዘግቦበታል። የአጊቱ አስከሬን በክብር ለአገሩ አፈር መብቃቱ ፖለቲካዊ ትርፍን ፍለጋ ማንም ሊጠቀምበት የሚገባ ጉዳይ ነው ብዬ አላምንም። በየትም አገር አንድ ሰው ታዋቂ ሲሆን በህይወት ዘመኑም ይሁን ከሞቱ በሁዋላ የበለጠ ትኩረት መሳቡ በየትም ያለ እውነታ ነው።
የቤንሻንጉሉ ግፍና ጣልያን የተፈጸመው ወንጀል ሁለቱም እኩይ የሆኑ የጭካኔ ድርጊቶች ሲሆኑ የራሳቸው ታሪክና ትርክት ያላቸው ክስተቶች ናቸው። አንዱ ከሌላው ጋር ምንም አይነት ዝምድናና ግንኙነት የለውም።
የግፍ ሰለባ የሆኑ ሁሉ ፍትህ እንዲያገኙ በጋራ መስራትና ድምጽ ማሰማት ቅራኔን ለማስፋትና የፖለቲካ ትርፍ ከማነፍነፍ የተሻለ ሰብአዊነትን ይገልጻል። ቅራኔን በትንሹም በትልቁም ለማስፋት እየተጉ ለጋራ ችግሮች የጋራ መፍትሄ ማፈላለግ ፈጽሞ አይቻልም።
የአገራችን ፖለቲካ ገና ብዙ መጽዳት የሚገባው የዘር፣ የጭፍን ስሜት፣ የሴራና የአጥፍቶ መጥፋት እሳቤ ቅይጥ ቆሻሻ መሆኑን መዘንጋት አይገባም።
ለሁሉም ነፍስ ይማር። አበበ ገላው