ኤርትራ በማስታወቂያ ሚኒስትሯ በኩል ዝምታዋን ሰብራለች


መረጃ ቲቪ አባል በመሆን የሳተላይት ቲቪውን ቀጥታ ስርጭት፣ ወቅታዊ ዜናዎችን እና ትንተናዎችን፣ የመዝናኛ ፕሮግራሞችን፣ ስፖርት እና ሌሎችንም ዝግጅቶቻችንን በፍጥነት እና ጥራት ስልክዎ፣ ኮምፒዩተርዎ ወይም ቲቪዎ ላይ ማየት ይችላሉ። እዚህ ሊንክ ላይ በመጫን አባል ይሁኑ


በሰሜናዊ ኢትዮጵያ የተከሰተውን ግጭት በተመለከተ ምንም አይነት አስተያየት ሳትሰጥ የቆየችው ኤርትራ በማስታወቂያ ሚኒስትሯ በኩል ዝምታዋን ሰብራለች።

BBC Amharic : በዚህም ኤርትራ በዋና ከተማዋ አሥመራ ላይ የሚሳኤል ጥቃት ከተፈጸመ ከቀናት በኋላ የኢትዮጵያ ሰሜናዊ ግዛት የሆነችውን የትግራይ ክልልን የሚያስተዳድረውን ህወሓትን በ”ክፉ ዓላማና ድርጊት” ወቅሳለች።

በፌደራል መንግሥትና በትግራይ ክልል ኃይሎች መካከል የተቀሰቀሰው ግጭት ወደ ሦስተኛ ሳምንቱ በተሸጋገረበት በአሁኑ ወቅት የኤርትራው የማስታወቂያ ሚኒስትር የማነ ገብረ መስቀል ትናንት ህወሓት ላይ ወቀሳ ሰንዝረዋል።

ሚኒስተሩ በትዊተር ገጻቸው ላይ ያሳፈሩት ጥቅምት 25/ 2013 ዓ.ም መንግሥት በህወሓት የሚመሩት የክልሉ ኃይሎች ላይ ወታደራዊ እርምጃ መውሰድ ከጀመረ በኋላ ስለግጭቱ ከኤርትራ በኩል የተሰማ ይፋዊ አስተያየት ነው።

ሚኒስትር የማነ ጨምረውም ብዙም ግልጽ ባልሆነው ሁኔታ ባሰፈሩት መልዕክት ላይ፤ የህወሓትን “ተገማች የሆነ ነገር ግን ውጤት አልባ የመጨረሻ መፍጨርጨርን ማጉላት አስፈላጊ አይደለም” ብለዋል።

የማስታወቂያ ሚኒስትሩ መልዕክታቸው ላይ ባለፈው ሳምንት ማብቂያ ላይ ከኢትዮጵያ የትግራይ ክልል ወደ አሥመራ ከተማ ስለተተኮሱት ሚሳኤሎችም ሆነ የኢትዮጵያ ሠራዊት እያካሄደ ስላለው ወታደራዊ ዘመቻ ምንም ሳይሉ ቀርተዋል።

የማነ ገብረ መስቀል ኤርትራን በሚመለከት አገራዊና ቀጣናዊ ጉዳዮች ላይ በፍጥነት በትዊተር ገጻቸው ላይ ተደጋጋሚ መልዕክቶችን በማጋራት ይታወቁ የነበረ ቢሆንም፤ በሰሜን ኢትዮጵያ የተከሰተውን ግጭት ተከትሎ የኤርትራ ስም በተደጋጋሚ ቢነሳም ምንም ሳይሉ ቆይተዋል።

በተጨማሪም በኤርትራ ከተማ ላይ የሚሳኤል ጥቃትን ተከትሎ በእሳቸው በኩል ማብራሪያ ይሰጣል ተብሎ በበርካቶች ዘንድ ቢጠበቅም አስከ ትናንት ድረስ ምንም ሳይሉ ቆይተዋል።

ግጭቱ ከተቀሰቀሰበት ጊዜ አንስቶ የትግራይ ባለስልጣናት በተደጋጋሚ ኤርትራ የኢትዮጵያ ሠራዊትን እየደገፈች ነው በማለት ሲከስሱ ቆይተዋል።

የደርግን መንግሥት ለመጣል በተደረገው የትጥቅ ትግል ወቅት አጋር የነበሩት አሁን ኤርትራን የሚያስተዳድረው ህዝባዊ ግንባር ለዴሞክራሲና ለፍትህ (ህግዴፍ) እና ህወሓት ዓመታትን በዘለቀ መቃቃር ውስጥ ቆይተዋል።

ከሃያ ዓመታት በፊት በኢትዮጵያና በኤርትራ መካከል ተካሂዶ ከነበረው ደም አፋሳሽ የድንበር ጦርነት በኋላ በኢትዮጵያ መንግሥት ውስጥ ቁልፍ ሚና የነበረው ህወሓት እና በኤርትራ መንግሥት መካከል የነበረው ቁርሾ አስካሁን ድረስ ዘልቋል።

ትናንት [ረቡዕ] የኤርትራ ባለስልጣናት ወደ ግብጽ ተጉዘው ከግብጽ ከፍተኛ ባለስልጣንት ጋር በነበራቸው ውይይት በአሁኑ ጊዜ ኢትዮጵያ ውስጥ ስላለው ሁኔታ መነጋገራቸው ተገልጿል።

ጥቅምት 24 2013 ዓ.ም የትግራይ ልዩ ኃይል በሰሜን ዕዝ ላይ ጥቃት መሰነዘሩን ተከትሎ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ የመከላከያ ኃይል በክልሉ መንግሥት ላይ እርምጃ እንዲወስድ ማዘዛቸው ይታወሳል።

ሁለት ሳምንታት ያስቆጠረው የፌደራል መንግሥቱና በትግራይ ልዩ ኃይሎች መካከል እየተደረገ ያለው ግጭት ከተቀሰቀሰ ጀምሮ በክልሉ ውስጥ ያለው የግንኙነት መስመር በመቋረጡ ዝርዝር መረጃዎችን ለማግኘት አዳጋች ሆኗል።

ነገር ግን ክልሉን እያስተዳደሩ ያሉት ዶ/ር ደብረፂዮን እንዲሁም መከላከያ በሰጧቸው መግለጫዎች የፌደራል መንግሥቱ ኃይሎች ሽሬን እና ራያን ተቆጣጥረው ወደ አክሱም እያመሩ መሆኑ ተነግሯል።

የፌደራል ፖሊስ ኮሚሽን ደብረፂዮንን (ዶ/ር) ጨምሮ ሌሎች ከፍተኛ የህወሓት ነባር አመራሮችን በቁጥጥር ስር ለማዋል የሚያስችል የፍርድ ቤት የመያዣ ትዕዛዝ በ96 ግለሰቦች ላይ ማውጣቱን አስታወቋል።

በትናንትናው ዕለትም ህዳር 9/2013 ዓ.ም ኮሚሽኑ በድጋሜ 76 ጄኔራሎች፣ ከፍተኛ ወታደራዊ መኮንኖችና የበታች ሹማምንቶች “ከህወሓት ጋር በመተባበር የአገር ክህደትን ፈፅመዋል” በሚል የመያዣ ትዕዛዝ እንደወጣባቸው አስታውቋል።

የተለያዩ የዓለም አቀፍ መንግሥታት የፌደራልና የክልሉ መንግሥታት የገቡበትን ግጭት በንግግር እንዲፈቱ ጥሪ ያቀረቡ ሲሆን ጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ አህመድ ግን ጉዳዩ “ህግ ማስከበር ነው” በሚል ሳይቀበሉት ቀርተዋል።

እንደ የተባበሩት መንግሥታት የስደተኞች ድርጅት መግለጫ ከሆነ በአሁን ሰዓት 30 ሺህ ሰዎች በላይ ግጭቱን በመሸሽ ወደ ሱዳን መሸሻቸውን አስታውቋል።