ሶማሌው በኦሮሞ፣ ኦሮሞ በሶማሌ ክልሎች ለምን አገር አልባ ይሆናሉ ? (ግርማ ካሳ)


መረጃ ቲቪ አባል በመሆን የሳተላይት ቲቪውን ቀጥታ ስርጭት፣ ወቅታዊ ዜናዎችን እና ትንተናዎችን፣ የመዝናኛ ፕሮግራሞችን፣ ስፖርት እና ሌሎችንም ዝግጅቶቻችንን በፍጥነት እና ጥራት ስልክዎ፣ ኮምፒዩተርዎ ወይም ቲቪዎ ላይ ማየት ይችላሉ። እዚህ ሊንክ ላይ በመጫን አባል ይሁኑ


የሶማሌና የኦሮሞ ክልል ከደቡብ ሞያሌ ጀምሮ እስከ ምስራቅ ሃረር ድረስ በብዙ ርቀት ይዋሰናሉ።

በአገሪቷ ሕገ መንግስት መሰረት ኢትዮጵያ የዜጎቿ ሳትሆን የብሄር ብሄረሰቦች ናት። ከዚያም የተነሳ የአገሪቷ ግዛት በዘር ወይም በብሄር ብሄረሰብ ተሸንሽኖ አንዱ አካባቢ ለአንዱ ዘር፣ ሌላውን አካባቢ ለሌላው ዘር የተሰጠ ነው። የሶማሌ ክልል የሚባለው ተሸንሽኖ ለሶማሌዎች፣ የኦሮሞ ክልል የሚባለው ተሸንሽኖ ለኦሮምዎች ተሰጠ።

ሆኖም ያንን በሚሸነሽኑበት ጊዜ፣ አንዳንድ ኦሮሞዎች የሚኖሩባችው አካባቢዎች ለሶማሌ፣ ሶማሌዎች የሚኖርባቸው አካባቢዎች ለኦሮሞ ክልል ተሰጡ። አንዳንድ ቦታዎች ደግሞ ሁለቱም የሚኖሩባቸው ለኦሮሞ መሰጠት አለበት፣ ለሶማሌ መሰጠት አለበት የሚል ዉዝግቦች ተነሱ።

ለምሳሌ የሞያሌ ከተማን መዉሰድ እንችላለን። ከአስር አመት በፊት በተደረገው የሕዝብ ቆጠራ ዉጤት መሰረት፣ በከተማው የቦረና ኦሮሞዎች 35.94%፣ የጋሪ ሶማሌዎች 23.69%፣ ቡርጂዎች 16.85%፣ አማራዎች 14.42%፣ ወላይታዎች 4.82%፣ ስልጤዎች 4.28% የሚሆኑ ይኖሩባታል። ከተማዋ ሕብረብሄራዊ ከተማ ነበረች። የፍቅር ከተማ። ሆኖም ግን ኦሮሞዎች ሞያሌ የኦርሞ ነው ሲሉ ሶማሌዎች ደግሞ የኦሮሞ አይደለም በሚል ዉዝግብ ከተማዋ ለሁለት ተከፈለች። ክዋናው መንገድ በስተምስራቅ ያለው የሶማሌ ክልል ሲሆን፣ በስተምእራብ ያለው ደግሞ የኦሮሞ ክልል ሆኖ። ከተማዋም በደም መፈሳስ መታወቅ ጀመረች። በዘር ግጭቶች።

ሌላው ምሳሌ ድሪዳዋ ናት። ሁለቱም የኦሮሞ፣ የሶማሌ የሚል ዉዝግ ስላስነሱ፣ ድሬዳዋ ከተማም ለጊዜው የፌዴራል ከተማ ትሁን ተብሎ ፣ የድሬዳዋ ነገር እልባት ሳያገኝ እስካሁን በፌዴራል ስር እንደሆነች ቆየች። በርካታ አንድ የነበሩ ወረዳዎች ለሁለት እንደ አንባሻ ተቆርሰው የሶማሌ፣ የኦሮሞ ተብለው ተከፍለዋል። የጉርሱም፣ የሚኤሶ፣ የባቢሌ ወረዳዎችን መጥቀስ ይቻላል።

ሶማሌውና ኦሮሞው ለዘመናት አብሮ የኖረ ነው። በተለይም በምስራቅና በደቡብ አንድ አይነት ሃይማኖት ያለው ማህበረሰብ ነው። በባሌና በሃረርጌ ያለው ኦሮሞ፣ ወለጋ ካለው ይልቅ በሁሉም ነገር የሚቀርበው ሶማሌውን ነበር። ሆኖም ግን በሰላም ለዘመናት የኖሩ ሰዎችን በዘር እንዲከፋፈሉ በመደረጉ ይኽው ደም መፋሰስን እያየን ነው።

ከዚህ በፊት የሆነውን አሳዛኝ ክስተት ሁላችንም የምናስታወሰው ነው። ዛሬና ባለፈው ጥቂት ቀናት ውስጥ ብቻ በጭናቅሰን 38 በጉርሱም ደግሞ 4 ኦሮሞዎች ፣ በሞያሌ ደግሞ ከ50 በላይ ሶማሌዎች ፣ በሜኤሶ 5 ኦሮሞዎችና 4 ሶማሌዎች እንደተገደሉ እየሰማን ነው። ከሁለቱም ወገኖች የተፈናቀሉም ቁጥራቸው ቀላል አይደለም።

እየሆነ ላለው ነገር የኦሮሞ አክቲቪስቶች አብዲን ይከሳሉ፣ የሶማሌ አክቲቪስቶች ደግሞ አቶ ለማን ይከሳሉ። ሁለቱም የየራሳቸውን ዘር ላይ የሚደርሰውን እየነገሩን ነው። ነገር ግን የችግሩ ምንጭ ምን ላይ እንደሆነ የገባቸው አይመስለም። የችግሩ ምንጭ አቶ አብዲም አቶ ለማም አይደሉም።የችግሩ ምንጭ የዘር ፖለቲካው ነው። የዘር ፌዲራል አወቃቀሩ ነው።

አሁንም ደግመን እንጽፋለን። “ኦሮሞ ፣ ሶማሌ ተባብሎ መናቆር መፍትሄ አያመጣም። ጥላቻ መፍትሄ አያመጣም። የሶማሌ መሬት፣ የኦሮሞ መሬት ሳይባል ፣ ዘር ሳይታይ ሁሉም እኩል የሚታዩበት አስተዳደር ያስፈለጋል” እያልን። ሶማሌው ከሶማሌ ክልል ዉጭ አገር አልባ ለምን ይሆናል ፧ ኦሮሞው በሶማሌ ክልል አገር አልባ ለምን ይሆናል? “የኔ ፣ ያንተ” እየተባባልን ከምንተላለቅ “የኛ” ተባብለን፣ ከዘር የጸዳ ፣ ለአስተዳደር የሚያመች ፣ በእኩልነት ላይ የተመሰረተና ሁሉንም እኩል የሚያያስ አወቃቀር ቢኖረን አይቻልም ወይ ?

በአስቸኳይ ብዙ ብሄረሰቦች የሚኖሩባቸው አካባቢዎች ለአንድ ጎሳ ወይንም ዘር ከተመደበ አስተዳደር ወጥተው ሕብረብሄራዊ በሆነ አስተዳደር ስር መሆን አለባቸው። ምያሌ ከተማና አካባቢዋ ለሁለት መከፈሏ ቀርቶ ፣ ሶማሌው፣ ኦሮሞዉም ሁሉም እኩል የየሁናበት ነገሌ ቦረና በሚል ሕብረ ብሄራዊ አስተዳደር ስር መሆኑ ይበጃቸዋል። ጉርሱም ሜኤሶ፤ ባቢሌ ያሉ ወረዳዎች፣ ከዲሪዳዋና ከሃረር እንዲሁም የሶማሌ ክልል ውስጥ ካለው የሽንሌ ዞን እና በሃረርና በድሬዳዋ መካከል ያሉ የኦሮሞ ክልል ወረዳዎችን ባካተተ፣ ሃረርጌ በሚል ሕብረ ብሄራዊ አስተዳደር ስር መሆናቸው ፍቱን መፍትሄው ነው።