" /> “አስከሬኑን” መንግስት አሽጎ አስቀብሮት፣ በእስር ቤት ተገኘ የተባለው ተስፋሁን ጉዳይ | Mereja.com - Ethiopian Amharic News

“አስከሬኑን” መንግስት አሽጎ አስቀብሮት፣ በእስር ቤት ተገኘ የተባለው ተስፋሁን ጉዳይ

የቀን ጅቦች ጉድ!

~”አስከሬኑን” መንግስት አሽጎ አስቀብሮት፣ በእስር ቤት ተገኘ የተባለው ተስፋሁን ጉዳይ

(ጌታቸው ሺፈራው)

ተስፋሁን የእኔአባት ይባላል። ወታደር ነበር። ከወታደር ቤት ለእረፍት ቤተሰቦቹ ወደሚኖርበት ቤተሰቦቹ ባህርዳር ሲመጣ እናቱ ጥሩአለም መንግስቴ “አትሂድብኝ” ይሉታል። የእናቱን ስጋትና ልመና ሰምቶ ወደወታደር ቤት ሳይመለስ ይቀራል። “ከስራው ቀረ” ያሉ አካላት ያፈላልጉት ስለነበር ቦታ ቀይሮ ተቀመጠ። እንደገና ወደባህርዳር ሲመለስ እንደሚፈለግ አወቀ።

ተስፋሁን የእኔአባት ከጓደኛው ቴዎድሮስ መኮንም ጋር በ1994 ዓም ክረምት ወር ከባህርዳር ወደ ኢዲስ አበባ እየሄደ ነበር። “በሰላም ግቡ” ብሎ የሸኛቸው ቤተሰብ የሰማው አዲስ አበባ በሰላም መግባታቸውን አልነበረም። ቤተሰቦቻቸው በመንግስት ሚዲያ የሰሙት ማመን ያቃታቸውን ዜና ነበር። ወደ አዲስ አበባ የተሳፈሩበት አውሮፕላን ሊጠልፉ እንደነበር በዜና ተነገረ። ከቀናት በኋላ ደግሞ ማሕተም ተደርጎበት የተሻገ አስከሬን መጣላቸው።
የተስፋሁን ቤተሰቦች ሰኔ 2/1997 ዓም አስከሬን ነው ተብሎ የታሸገ ሳጥን ብር ከፍለው ተረከቡ። “ከፍተን እንየው” ሲሉ እንደማይቻል ተነገራቸው። በወቅቱ ቀብሩ ሲፈፀም ደሕንነቶች ቆመው ነበር። እናቱ ጥሩአለም መንግስቴ “የልጄን አስከሬን ካላየሁ” ብለው የደሕንነቶችን ትዕዛዝ አልቀበልም አሉ። ደሕንነቶቹ ደግሞ “ከፍተን እናያለን ካላችሁ” መልሰን እንወስደዋለን አሉ። ለቀስተኛው “ሳይቀበር ከሚቀር” ብሎ እናቱ የደሕንነቶችን ትዕዛዝ እንዲቀበሉ አግባባ።
የተስፋሁን የእኔአባት ቤሰተቦች ለወጣቱ ሀውልት የማቆም ፍላጎት ነበራቸው። አስከሬኑ በሳጥን ሰንብቶ ሀውልት የሚሰራበት አካባቢ እንዲቀበር ፍላጎታቸውን ገለፁ። አስከሬኑን ከፍተው ያዩታል ብለው የሰጉት ደሕንነቶች ግን ይህንም አልተቀበሉም። “ዛሬ እኛ ባለንበት ካልተቀበረ መልሰን እንወስደዋለን” ብለው አቋማቸውን አሳወቁ። በቀብር ስነ ስነ ስርዓት ጣልቃ ገቡ። ቤተሰቡ ደሕንነቶቹ በቆሙበት ምን ይሁን ምን ያልታወቀን ሳጥን ከመቅበር ውጭ አማራጭ አልነበረቀቸውም።

የተስፋሁን የእኔአባት አስከሬንን ይዟል የተባለ የታሸገ ሳጥን ከተቀበረ ከ7 አመት በኋላ የተስፋሁን እህት ደጅይጥኑ የእኔአባት የምታውቀው አንድ ሰው ወንድሟ እስር ቤት ውስጥ እንደሚገኝ ይገልፅላታል። ይህ እስር ቤት ውስጥ የሚሰራ ሰው ወደ እስር ቤት ወስዶ መጠየቅ ባይቻልም ከእርቀት አውሮፕላን ሲጠልፍ ተገድሏል የተባለውን ወንድሟን ያሳያታል።
ሆኖም የወንድማቸው ጉዳይ እጅግ ውስብስብ ሆኗል። መንግስት በቀብር ስነ ስርዓቱ ጣልቃ ገብቷል። ሀውልት እንዳይሰራለት፣ ስለ አሟሟቱና መሰል መረጃዎች እንዳይጠይቁ ተደርገዋል። በመሆኑም የትኛውንም የመንግስት አስተዳደር ቢጠይቁ “ቀበራችሁትኮ” እንደሚባሉ ያውቁታል። በአንድ በኩል በሕይወት መኖሩን ተስፋ አድርገው፣ በሌላ በኩል ደግሞ ቢጠይቁ የሚመጣባቸውን መዘዝና የሚሰጣቸውን መልስ ጠብቀው ኖረዋል።

ተስፋሁን የእኔአባትና ጓደኛው ቴዎድሮስ መኮንን 25 አመት ተፈርዶባቸው በአንድ እስር ቤት ውስጥ ታስረው እንደሚገኙ ቤተሰቦቻቸው መረጃ ቢኖራቸውም፣ የታሸገ ሳጥን አምጥቶ፣ ቆሞ ያስቀበረውን መንግስት ለመጠየቅ አልቻሉም። መልስ እናገኛለን ብለው አልጠበቁም። ከቀበሯቸው ከ7 አመት በኋላ አሉ የተባሉትን ወጣቶች በሕይወት መኖር ተስፋ አድርገው፣ ሌላ ተስፋ ይጠብቃሉ። በግራ መጋባት ውስጥ!


የመረጃ ቲቪ አባል ይሁኑ - JOIN US