ያልተጠና ኢላማና ሰብአዊነት የጎደለው አካሄድ ተፅእኖው ከፍተኛ ነው ! – ምንሊክ ሳልሳዊ


መረጃ ቲቪ አባል በመሆን የሳተላይት ቲቪውን ቀጥታ ስርጭት፣ ወቅታዊ ዜናዎችን እና ትንተናዎችን፣ የመዝናኛ ፕሮግራሞችን፣ ስፖርት እና ሌሎችንም ዝግጅቶቻችንን በፍጥነት እና ጥራት ስልክዎ፣ ኮምፒዩተርዎ ወይም ቲቪዎ ላይ ማየት ይችላሉ። እዚህ ሊንክ ላይ በመጫን አባል ይሁኑ


ምንሊክ ሳልሳዊ – በኦሮሚያ ክልል የቀጠለው የሰው ሕይወት የመጥፋትና የሽብር ተግባር እጅግ አሳሳቢ በመሆኑ መንግስት አስቸኳይ መፍትሔ ሊያበጅለት ይገባል። በተለያዩ የኦሮሚያ ክልል ከተሞች በጸጥታ አካላት በተሰነዘረ ጥቃት ሰላማዊ ዜጎች፣ የሃይማኖት ሰዎች አዛውንትና ሕጻናት መሞታቸው እና መቁሰላቸው ተሰምቷል። ሕግ ለማስከበር መንግስት በሚወስደው እርምጃ የሰላማዊ ዜጎችን ደሕንነት የመጠበቅ ግዴታ አለበት።

በክልሉ የሚነሱ ተቃውሞዎች ዜጎች በነጻነት ጥያቄዎቻቸውን እንዲያቀርቡ መከልከል ከሕግ አንጻር ተገቢ አይደለም። ዜጎች ጥያቄዎቻቸውን ሲያቀርቡም መንግስት የሚወስደው የኃይል እርምጃም ሊጤን ይገባዋል። የሞት ጉዳቶቹ የደረሱት የኦሮሞ ተቃዋሚ ፓርቲ ፖለቲከኞች እንዲለቀቁ በተጠሩ የተቃውሞ ሰልፎች እንደሆነም ለማወቅ ተችሏል፡፡

መንግስት በመዋቅሮቹ ውስጥ ያሉትን የግጭት ነጋዴዎችና ግጭቱን የሚመሩ እኩይ አካላትን መንጥሮ በማውጣት ችግሮችን መግታት ይጠበቅበታል። መንግስት የኃይል እርምጃ ከመውሰድ ይልቅ ችግሮች ይከሰታሉ በሚባልባቸው የክልሉ አከባቢዎች የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ በማወጅ በኮማንድ ፖስት በመቆጣጠር ችግሮችን ከስራቸው ለማድረቅ መፍትሔ ሊሆን ይገባል።

በሰላማዊ መንገድ ተቃውሞ የሚያሰሙ ሰዎች የጥቃት ሰለባ እንዳይሆኑ መንግስት ተገቢውን ጥንቃቄ ሁሉ ማድረግ ይኖርበታል። መንግስት አስቸኳይ በሆነ ሁኔታ የደረሱትን ጥፋቶችና የኃይል እርምጃዎች ያስከተሉትን ግድያዎች በተመለከተ በገለልተኛ አካል በማጣራት የዜጎች የመኖር ሕልውና በሕግ የበላይነት እንዲከበር አፋጣኝ እርምጃ መውሰድ አለበት።

በኡስታዝ አቡበከር አሕመድ አባባል ጽሁፌን ስዘጋ እንዲህ ብለዋል ፦ ” …… በየወቅቱ መፍትሄን ሰላማዊ ባልሆነ መልኩ የማምጣት ሙከራዎች በሁሉም በኩል ይታያል። በተለይም ለችግሮች የሚሰጡ መፍትሄዎች ሌላ ችግር እየፈጠሩ ተደጋጋሚ አዙሪቶች ውስጥ ስንገኝ ይታያል። የዚህ አንዱ መነሻ ለሰላማዊ ጥያቄ ንፁሃንን ተጎጂ ማድረግ ሲሆን ሰላምን ለማስከበር ንፁሃንን ኢላማ ማድረግ ደግሞ ሌላው ነው። በተለይ ሰላም ለማስከበር ንፁሃንን፣ ያልተጠና ኢላማ እና ሰብአዊነት የጎደለው አካሄድ ተፅእኖው ከፍተኛ ነው።” –  ምንሊክ ሳልሳዊ