ከነበረከት ስሞንና አሁን ካሉ የብአዴን አመራሮች ማን ይሻላል ? ግርማ ካሳ


ኢትዮጵያን ካጋጠሟት እጅግ ውስብስብ ችግሮች ለማዳን የተለያዩ ጠቃሚ ሃሳቦችን እና ገንቢ ትችቶችን የሚያቀርቡ ነፃ ሚዲያዎች ወሳኝ ሚና እንደሚጫወቱ ይታወቃል። ስለዚህም ኢትዮ360፣ መረጃ ቲቪ፣ አዲስ ድምጽ፣ ምንሊክ ቲቪ እና ሌሎችም የኢትዮጵያዊነት አጀንዳ የሚያራምዱ ሚዲያዎች በመተባበር ፕሮግራሞቻቸውን በሳተላይት ቲቪ ለኢትዮጵያ ህዝብ በማቅረብ ላይ ይገኛሉ። እነዚህ ሚዲያዎች የፈጠሩት ማህበር የሳተላይት ወጪውን መሸፈን እንዲያስችለው ይህን የጎፈንድሚ ፔጅ ከፍተናል → እዚህ ሊንክ ላይ ይጫኑ። ለትብብርዎ እናመሰግናለን።
ከነበረከት ስሞንና አሁን ካሉ የብአዴን አመራሮች ማን ይሻላል ? ግርማ ካሳ
በቢኔሻንጉል በጉባ ወረዳ ዘር ተለይቶ ሕጻናት ሳይቀሩ በግፍና በጭካኔ ተገድለዋል፡፡ አርሶ አደሮች፣ የእርሻ ሥራቸው በማከናወን ላይ የነበሩ፣ አማራዎች፡፡ እስከነ ልጆቻቸው፡፡
በምክትል ርዕሰ መስተዳድር ማዕረግ የአማራ ክልል ብልጽግና ፓርቲ ጽ/ቤት ኃላፊ አቶ አገኘው ተሻገር ፣ “ጥቃቱን የፈጸመው ኃይል በአካባቢው የብሔር ግጭት የመቀስቀስ ዓላማ በመያዝ ተደጋጋሚ የጥፋት ሙከራ ሲያደርግ የቆየ ነው።
ታጣቂ ኃይሉ በህውሓት የስልጠናና የገንዘብ ድጋፍ የተደረገለት ነው፡፡ ህውሓት ሀገርን ለማተራመስ እያደረገ ያለው እንቅስቃሴ አካል ነው” የሚል አስተያየት ሰጥተዋል፡፡
ብአዴኖች/አዴፓዎች ምን አለ ሕወሃት ላይ ማሳበብ ቢያቆሙ ?????? አሁን አሁንማ ኮሮናን ያመጣው ሕወሃት ነው ሊሉን እንደሚችሉ መጠበቅ አለብን፡፡
ችግሩ ያለው የቤኔሻንጉል ክልል የብልጽግና ፓርቲ አመራርና የክልል መንግስቱ ላይ ነው፡፡ ክልሉ ወደ 45% አካባቢ የሚሆኑት አማራና ኦሮሞ ናቸው፡፡ ከበርታዎች ቀጥሎ ትልቁ ማህበረሰብ አማራው ነው፡፡ ሆኖም አማራዎችና ኦሮሞዎች በክልሉ ሕገ መንግስቱ መሰረት፣ በክልሉ መጤና ሰፋሪ ተደርገው ነው የሚቆጠሩት፡፡”ሌሎች ብሄር ብሄረሰብ ሕዝቦች(አማራውና ኦሮሞዉችን ማለታቸው በዋናነት) በክልሉ እንደሚኖሩ ቢታወቅም፣ የክልሉ ባለቤቶች የሸናሽ፣ ማኦ፣ ኮሞ፣ በርታና ጉምዝ ብሄረሰቦች ናቸው” ነው የሚለው የቤነሻንጉል ክልል ሕገ መንግስት፡፡ ያ ማለት በዚያ የሚኖሩ አማራዎችና ኦሮሞዎች የክልሉ ባለቤቶች አይደሉም፡፡ በክልሉ አመራር ውስጥም አይካተቱም፡፡ በክልሉ ውክልና የላቸውም፡፡
ስለዚህ በክልሉ ያሉ ጽንፈኞች ፣ “የኛ ክልል ነው፣ ሌሎች ወራሪዎች ናቸው” የሚል ስሜት ነው ውስጣቸው ያለው፡፡ “አማራዎችና ኦሮሞዎች የኛ አገር ሰዎች ናቸው”ብለው እንዳያምኑ ነው የዘር ፖለቲካው ያደረጋቸው፡፡ ከዚህም የተነሳና የክልሉ መንግስት ከምር ሕግን የማስከበር ፍላጎት እንደሌለው ስላወቁ ነው በየጊዜው ጥቃት የሚፈጽሙት፡፡
ይሄ ነው ችግሩ፡፡ አከላለሉ ላይ ነው ችግሩ፡፡ የዘር ፖለቲካው ላይ ነው ችግሩ፡፡ ይሄ ሕወሃት ከኦነግ ጋር ሆነው በሕዝብ ላይ የጫኑት ሕገ መንግስትና የጎሳ አወቃቀር ላይ ነው ችግሩ ፡፡ ለዚህም ነው በተለይም አማራው ከአማራ ክልል ውጭ የዘር ማጥፋት ወንጀል የሚፈጽመበት፣ የሚገደለው፡፡
የአማራ ክልል አመራሮች፣ በፌዴራል ደረጃም ያሉ የቀድሞ አዴፓዎች (እነ አቶ ደመቀ መኮንን፣ አቶ ንጉስ ጥላሁን …ያሉ) የጎሳ አወቃቀሩን ተቀብለው እየሄዱ ነው፡፡ ይኸው ሁለት አመት ተኩል ሆናቸው፣ ቃላቸውን አልጠበቁም፡፡ መሰረታዊ ለውጥ እንዲመጣ ሲሰሩ አይታዩም፡፡ ዜጎችን በተለይም አማራውና አማርኛ ተናጋሪዎች በዝምታቸው እያስጨረሱት ነው፡፡
በቤኔሻንጉል ያሉ አማራዎች በአገራቸው አገር አልባና ሁለተኛ ዜጎች መሆናቸው አምነውና ተቀብለው ነው እየሄዱ ያሉት፡፡ ሕወሃት የሰጣቸውን አስቀያሚ ቀይና ቢጫ አርማ እንኳን አልቀየሩም፡፡ አሁንም ያ አርማ የክልሉ አርማ ነው፡፡ የክልሉ ዋና ከከተማ ባህር ዳር አይሮፕላን ማረፊያን አሁንም ግንቦት 20 የሚለውን ስያሜ በማስቀጠል የሕወሃት አዲስ አበባ መግባት እየዘከሩ ነው፡፡ አሁንም በመንፈስ ሕወሃትን እያመለኩ ነው፡፡
እውነታው እንደዚያ ሆኖ ላይ ላዩን ሕወሃትን መርገምና ሁሉንም በሕወሃት ላይ ማሳበብ ግብዝነት ብቻ ሳይሆን ነውረኝነት ነው፡፡
ከዚህ ጋር በተገናኘ አንድ ጥያቄ ላቅርብ፡፡ አሁን በተለይም በአማራው ማሕበረሰብ ላይ እያየን ያለውን ሰቆቃና እልቂት፣ የዘር ማጥፋት ወንጀል፣ በኦሮሞ ክልል በሉ በቤነሻንጉል ። እነ በረከት ስምኦን ቢኖሩ ኖሮ ይፈጸም ነበር ?????
በኔ እይታ የቤኔሻንጉል ክልል መፍረስ ያለበት ክልል ነው፡፡