ለሁለተኛ ጊዜ ኢትዮጵያ በህዳሴ ግድብ ዙሪያ ያላትን አቋም ለፀጥታው ምክር ቤት ግልጽ አድርጋለች።

(ኤፍ.ቢ.ሲ) ኢትዮጵያ በህዳሴ ግድብ ዙሪያ ያላትን አቋም ለሁለተኛ ጊዜ ለተመድ የፀጥታው ምክር ቤት በደብዳቤ አስታወቀች
ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብን አስመልክቶ ግብፅ ለተባበሩት መንግስታት ድርጅት የፀጥታው ምክር ቤት ጥያቄ ማቅረቧን ተከትሎ ኢትዮጵያ ያላትን አቋም በድጋሚ ለምክር ቤቱ ግልጽ አድርጋለች።
በዚህም ኢትዮጵያ ግድቡ የሰላም እና ፀጥታ ስጋት አለመሆኑን ለምክር ቤቱ አስታውቃለች።
ግብፅ በሦስቱ አገራት መካከል እየተካሄ ያለውን እና ያልተቋጨውን ድርድር ወደጎን በመተው ባለፈው ቅዳሜ ለሁለተኛ ጊዜ ለፀጥታው ምክር ቤት ያቀረበችው ጥያቄም አግባብ እንዳልሆነና ኢትዮጵያ በዚህ ድርጊት ማዘኗን ነው የገለፀችው።
የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አቶ ገዱ አንዳርጋቸው ለፀጥታው ምክር ቤት በላኩት ደብዳቤ÷ ኢትዮጵያ እየገነባች ያለችው ግድብ የታችኛውን ተፋሰስ አገር እንደማይጎዳ እና የሰላም እና ፀጥታ ስጋትም አለመሆኑን በድጋሜ አረጋግጠዋል።
ከዚያም ባለፈ የግብጽ አካሄድ ኢትዮጵያ ላይ ያልተገባ የፖለቲካና እና የዲፕሎማሲ ጫና ለማሳረፍ የመሞከር ነው ብለዋል።
በቅኝ ግዛት ወቅት የዓባይ ወንዝ መነሻ የሆነችውን ኢትዮጵያን ባገለለ መልኩ የተደረገን ስምምነት እንደመደራደሪያ ሀሳብ ማቅረብም አግባብ አይደለምም ነው ያሉት።
ከዚያም ባለፈ አሁን እየተካሄደ ያለው ድርድር በውሀ ክፍፍል ሳይሆን በግድቡ የውሃ አሞላል ሂደት ላይ መሆኑንም በደብዳቤው ላይ ግልፅ አድርገዋል።
ኢትዮጵያ አሁንም በፍትሀዊ ተጠቃሚነት ላይ የምታደርገውን ድርድር የመቀጠል ፍላጎት እንዳላት እና የትኛውንም የተፋሰሱ አገራት ጥቅም በማይጎዳ መልኩ ግድቡን ለማጠናቀቅ ያላትን ቁርጠኝነት ለምክር ቤቱ አረጋግጣለች።
ከግድቡ ጋር በተያያዘ ምንም ዓይነት የሰላምና ፀጥታ ስጋት ካለም ሁልጊዜ የሀይል አማራጭን ለመጠቀም ስታስፈራራ የኖረችው ግብፅ ለዚያ ተጠያቂ እንደምትሆን አስታውቃለች።