አምባቸው እንደሚገደል ቀደም ብሎ በስልክ ያስጠነቀቀኝ ሰው ነበር፤ የእሱ ሞት ለእኔ አንጀት የሚያሳርር ምንግዜም አዲስ ነው – ወይዘሮ የሹሜ ደምሳሽ


መረጃ ቲቪ አባል በመሆን የሳተላይት ቲቪውን ቀጥታ ስርጭት፣ ወቅታዊ ዜናዎችን እና ትንተናዎችን፣ የመዝናኛ ፕሮግራሞችን፣ ስፖርት እና ሌሎችንም ዝግጅቶቻችንን በፍጥነት እና ጥራት ስልክዎ፣ ኮምፒዩተርዎ ወይም ቲቪዎ ላይ ማየት ይችላሉ። እዚህ ሊንክ ላይ በመጫን አባል ይሁኑ


ቢቢሲ፡ ለመጨረሻ ጊዜ ከዶ/ር አምባቸው ጋር ስለምን አወራችሁ?
ወይዘሮ የሹሜ፡ ብዙም አላስታውሰውም ግን እኔ ነጋ፣ ጠባ ይገድሉሃል እላለሁ። ይገድሉሃል ስል ነበር።
ቢቢሲ፡ ለምን ነበር እንዲዚያ የሚሉት?
ወይዘሮ የሹሜ፡ አንድ ሰው ደውሎ ነገረኝ።
ቢቢሲ፡ ምን ብሎ ነገርዎት?
ወይዘሮ የሹሜ፡ ለአምባቸው የምትነግሪልኝ መልዕክት ብሎ እንደሚገደል ነገረኝ። ከዚያ ደነገጥኩና አንተ ማን ነህ? ስለው ‘ማንነቴ ምን ያደርግልሻል። እሱን ሰውዬ ግን ተጠንቀቅ በይው’ አለኝ። ከዚያም ነገሩ ስላሳሰበኝ .. .. ..
የማይመጣውን አባታቸውን የሚጠብቁት የዶክተር አምባቸው ልጆች –  BBC Amharic

አምባቸው መኮንን (ዶ/ር)ቅዳሜ ሰኔ 15/2011 ዓ.ም። አማራ ክልል ባህር ዳር ከተማ።

ባህር ዳር ዕለቱን እንደተለመደው ደመቅመቅ ብላ ጀመረች። ከሰዓት በኋላ ላይ ግን ተኩስ በየአቅጣጫው ይሰማባት ጀመር።

ከዚያ በኋላ የተፈጠረው ክስተት፤ ቅዳሜ ሰኔ 15 በባህር ዳር ታሪክ ፀሊሟ ቀን የሚል ስያሜ ቢያሰጣት አያስገርምም።

አምባቸው መኮንን (ዶ/ር) እና ወይዘሮ የሹሜ ደምሳሽ በትዳር ለ29 ዓመታት አብረው ኖረዋል። አምስት ልጆችም አፍርተዋል- አራት ሴት አንድ ወንድ።

አምባቸው (ዶ/ር) እንደ አማራ ክልል ፕሬዝዳንትነታቸው የሥራ ቦታቸው ባህር ዳር ነው። ቤተቦቻቸው ደግሞ አዲስ አበባ ነው የከተሙት።

አምባቸው (ዶ/ር) ከባህር ዳር ለሥራ ሲመጡ መሄጃቸውንም ሆነ መመለሻቸውንም አይናገሩም። እንደ ወይዘሮ የሹሜ “በቃ ሲመጣ ምጥት ሲሄድም መሄድ ነው። እንደዚህ ነው የእሱ ጸባይ።”

“አንድንድ ነገር እንኳን አዘጋጅቼ እንድጠብቅህ” በሚል፤ መሄጃ እና መመለሻህን ንገረንም ተብለው ተጠይቀው ያውቃሉ። “እኔ ከእናንተ የተለየ ነገር አልፈልግም ይለኛል” ምላሻቸው ነው።

**

አዲስ አበባ የሚገኘው የአምባቸውን (ዶ/ር) ቤት እንግዳ አያጣውም። ቅዳሜ ሰኔ 15/2012 ዓ.ም ጥየቃ የመጡ ቤተ ዘመዶች ቤቱን ሞልተውታል። ቤቱ በጨዋታ ደምቋል። የቤቱ እማወራ የወይዘሮ የሹሜ የአክስት ልጅ ስልክ እስኪደውል ድረስ ጨዋታው ቀጥሏል።

“ደውሎ ‘ባህር ዳር ተኩስ አለ’ አለኝ። . . . ለአምባቸው ደወልኩኝ። ስልኩ አይሠራም” ይላሉ ወይዘሮ የሹም። መረጃ ለማግኘት የተለያዩ ሰዎች ዘንድ ደወሉ። ምላሽ የለም።

የት እንደሚደውሉና ምን እንደተከሰተ ለማወቅ ቢያወጡ ቢያወርዱ አማራጭ ጠፋ። “እንደ ብርድም፤ እንደ ህመምም፤ እንደ መንቀጥቀጥም [አደረገኝ]። ምንም መቋቋም አልቻልኩም። ሰውነቴ ደረቀ” ይላሉ።

አንዳች ነገር እንደተከሰተ ደመነፍሳቸው የነገራቸው ወ/ሮ የሹም ትንሽ ቆየት ብለው አምባቸው (ዶ/ር) እግራቸውን በጥይት ተመትቶ ለህክምና ወደ አዲስ አባባ ሊመጡ መሆኑን ይሰማሉ።

“‘ተጎድቶም ይትረፍልኝ። ተጎድቶም ለልጆቼ ይኑርልኝ’ አልኩኝ። አዳር አይባልም እንዲሁ ሳለቅስም፣ ስነሳም ስወድቅም ምንም ስል በከፋ ስቃይ ውስጥ ሌሊቱ አለፈ” ሲሉ የመከራውን ሌሊት ያስታውሳሉ።

አይነጋ የለም ሌሊቱ ነጋ። እሑድ ሰኔ 16/2011 ዓ.ም ። ፀሐይ ወጥታ ባለቤታቸው ካሉበት ደርሰው ከጎናቸው ለመቆም ወደየት መሄድ እንዳለባቸው የሚነግሯቸውን ሰዎች ሲጠብቁ የነበሩት ወይዘሮ የሹሜ በማለዳ የአምባቸውን (ዶ/ር) ሞት ከቤተሰብ እና ዘመድ አዝማድ ተረዱ። ቀሪው ታሪክ ነው።

“ትልቅ ሐዘን በጣም፤ ልብ የሚሰብር ሐዘን ደርሶብናል። እንኳን ቤተሰቡን የሌላውንም ልብ ሰብሯል። የአባት ሞት የሁሉንም ኢትዮጵያዊ ልብ ይሰብራል። በጣም መራር የሆነ ሃዘን ነው የወደቀብን።”

“በቃ ቤተሰቡ በአምባቸው ሞት ክፉኛ ነው የተሰበረው። ተጎዳን። . . . የአምባቸውን ሞት እኔ እራሴ እስካሁን መቀበል አልቻልኩም” ሲሉ የሐዘናቸውን ጥልቀት ለቢቢሲ ተናግረዋል።

በተለይ ለሥራ ወጥቶ ስለቀረው አባታቸው ለልጆች መንገርና እንዲቀበሉት ማድረግ ካበድ ነው የሆነባቸው። “ከፍ ከፍ ያሉት ልጆች ጉዳዩን ይረዱታል። ከባዱ ነገር ዘወትር የአባታቸውን መምጣት በር በር እያዩ ለሚጠብቁት ለትንንሾቹ ማስረዳት ነው” ይላሉ።

የቤተሰብ ፎቶ

የቤተሰቡ የመጨረሻ ልጅ አራት ዓመቷ ነው። ሁሌም ትጠይቃለች። “አባቴ አይመጣም ወይ” እያለች።

“‘ሥራ ሂዷል አይመጣም’ ስትባል ጸሎት ቤት ትገባና ‘አባን አምጣልኝ ብዬ ለመንኩት’ ትለኛለች አሁንም ድረስ። ‘አይመጣም እኮ’ ብዬ ነግሬሻለሁ ስላት ምንም አትረዳም። በቃ ምንጊዜም ቢሆን አዲስ ናት። እሷ አሁንም ይመጣል ነው የምትለው።

“. . . ወንዱ ልጅ 13 ዓመቱ ነው። እሱ ብዙ ነገር ስለሚያውቅ አይናገርም። በጣም የተጎዳው እሱ ነው። አይናገርም ዝም ነው የሚለው። ነገር ግን ከፊቱ ላይ ጥበቃውንና ሐዘኑን እረዳለሁ።

“እሱም እኛን ያያል የሆንነውን ይረዳል። የሁሉንም ሰው ዓይን ዓይን እያየ የሚረዳው ነገር አለ” ሲሉ የአባታቸው ከቤተሰቡ መጉደል በተለይ በልጆቻቸው ላይ የፈጠረውን ስሜትና እርማቸውን እንዲያወጡ ለማስረዳት እንዴት እንደከበዳቸው በሐዘን ተሞልተው ይናገራሉ።

እንደ አካላቸው ክፋይ የሕይወት አጋራቸው እሳቸውም “እንኳን አሁን ተለይቶች በህይወት እያለ አምባቸውን ሳላስበው ውዬ አድሬም አላውቅም” የሚሉት ወ/ሮ የሹሜ አምባቸውም (ዶ/ር) ለእርሳቸው ያለቸውን መሳሳትና ትዝታቸው አሁን ድረስ ትኩስ ነው ይላሉ።

የቤተሰብ ሰው የነበሩት አምባቸው (ዶ/ር) ቀልድ እና ጨዋታ አዋቂ እንደነበሩ የሚናገሩት ባለቤታቸው “ማታ እቤት የሚሰራውን ነገር እንኳን ይዞ ቢመጣ ሰዓቱን አጣቦም ቢሆን ቁጭ ብለን የምንጫወተውን ምንጊዜም አስታውሰዋለሁ። ከቁም ነገርኝነቱ ባሻገር ቀልድም ጨዋታም በጣም ይችላል” ሲሉ ብዙ ነገር ቤተሰቡ እንዳጣ ይጠቅሳሉ።

አምባቸው (ዶ/ር) ከመሞታቸው ከጥቂት ቀናት በፊት የተጨዋወቱተን ፈጽሞ አይረሱትም።

“በጨዋታ መሃል ድንገት ‘አንቺ እኮ ጎበዝ ነሽ፤ ልጆችሽን ታሳድጊያለሽ’ አለኝ ሊሞት አንድ ሳምንት ሲቀረው። ‘እኔ እንዲህ ዓይነት ቀልድ አይመቸኝም። ሁለተኛ እንዲህ ዓይነት ነገር እንዳታወራ’ አልኩት።

“እኔም ‘ምን አስቦ ይሆን? ምን ተሰምቶት ይሆን?’ አልኩኝ። ከዚህ ውጪ ሌላ ነገርም ምንም አላለኝም። ይሄንን ነው ያለኝ። ስቆጣ በቀልድ ቀየረው። ረሳነው። ወዲያው ተውነው። ምን እንዳሰበ እና ለምን እንደተሰማው ባላውቅም ይሄንን ብሎኛል” በማለት ጥያቄያቸውን ይዘው በሃሳብ ወደዚያች ቀን ተመለሱ።

በአማራ ክልልና በፌደራል መንግሥት ከፍተኛ የኃላፊነት ቦታዎች ላይ የሰሩት አምባቸው (ዶ/ር) ካላቸው ኃላፊነት አንጻር ከፍተኛ የሥራ ጫናና ከቦታ ቦታ መንቀሳቀስ ነበረባቸው። ቢሆንም ግን ባገኙት ቀዳዳ ሁሉ ከቤተሰባቸው ጋር ጊዜያቸውን ማሳለፍን ይመርጡ እንደነበር ባለቤኣተቸው ይናገራሉ።

ለልጆቻቸው እንደ አባት ፍቅር ለመስጠት፣ ለማስተማርና ለመምከር አንድ ቀንም ወደኋላ የማይሉት አምባቸው (ዶ/ር) ልጆቻቸው ጠንካራና በእራሳቸው የሚተማመኑ እንዲሆኑ አዘውትረው ይመክሩ ነበር።

በተለይ ልጆች በምቾት እንዳይዘናጉ “‘አስለምደዋለሁ እግሬን ካለጫማ፤ ምንግዜም ደህና ቀን አይገኝምና እያለ አባቴ ይነግረኝ ነበር። እናንተም እንደዚህ ብላችሁ ማደግ አለባችሁ። እኔ ቋሚ አይደለሁም'” ይሏቸው እንደነበር ወ/ሮ የሹሜ ያስታውሳሉ።

አሁን የቤተሰቡ ኃላፊነት በወይዘሮ የሹሜ ትከሻ ላይ ሙሉ ለሙሉ ወድቋል። ቢሆንም ግን ልጆቹም ከአባታቸው ፍቅር ሌላ የሚጎድልባቸው የለም ይላሉ። “እነሱ የአባትነትን ፍቅር ማጣቱ፣ እሱን ካጠገባቸው ማጣታቸውና የእሱን መምጣት በመጠበቅ ከሚፈጠርባቸው ጫና ውጪ በሌላው ጉዳይ ልጆቹ ያለምንም ችግር ያድጋሉ” ይላሉ።

በዕለቱ ባህር ዳር ውስጥ ስለተፈጸመው ነገር የተለየ ነገር የሚያውቁትም የሰሙትም ነገር የሌለው ወ/ሮ ሹሜ እሳቸውም “እንደ ኢትዮጵያ ሕዝብ ነው እየሰማሁ ያለሁት” ይላሉ።

“ጀነራሉ ገደለ። እሱም ተገደለ ተባለ። አለቀ። ከዚያ ውጪ ፍትህ እንደማንኛውም ኢትዮጵያዊ ነው የምጠብቀው። እኔ ፍትህ አግኝቻለሁ አልልም። ከእሱ ጀርባ ያለው አሁንም አልጸዳም። እሱ ብቻውን አያደርገውም፤ እሱ ብቻውን አልገደለውም። ከኋላ ቆስቋሹ ማነው? የሚለውን ያወቅኩት ነገር የለኝም” በማለት ጉዳዩ እንዳልተቋጨ ይናገራሉ።

ቢቢሲ፡ ለመጨረሻ ጊዜ ከዶ/ር አምባቸው ጋር ስለምን አወራችሁ?

ወይዘሮ የሹሜ፡ ብዙም አላስታውሰውም ግን እኔ ነጋ፣ ጠባ ይገድሉሃል እላለሁ። ይገድሉሃል ስል ነበር።

ቢቢሲ፡ ለምን ነበር እንዲዚያ የሚሉት?

ወይዘሮ የሹሜ፡ አንድ ሰው ደውሎ ነገረኝ።

ቢቢሲ፡ ምን ብሎ ነገርዎት?

ወይዘሮ የሹሜ፡ ለአምባቸው የምትነግሪልኝ መልዕክት ብሎ እንደሚገደል ነገረኝ። ከዚያ ደነገጥኩና አንተ ማን ነህ? ስለው ‘ማንነቴ ምን ያደርግልሻል። እሱን ሰውዬ ግን ተጠንቀቅ በይው’ አለኝ።

ከዚያም ነገሩ ስላሳሰበኝ እንዲጠነቀቅ ነገርኩት። ስነግረው ‘የሹሜ እንደዚህ እያልሽ አዕምሮሽን እያስጨነቅሽ በሽተኛ እንዳትሆኚ። እኔ ምን አድርጌ ነው የሚገድሉኝ? ምን አጥፍቼ ነው የሚገድሉኝ?’ አለኝ።

ይሄንን አስታውሳለሁ . . . እና በጣም ያሳዝናል። የእሱ ሞት ለእኔ አንጀት የሚያሳርር ምንግዜም አዲስ ነው። እኔ እስከምሞት ድረስ በቃ እንዲሁ ስቃጠል ነው የምኖረው። አሟሟቱ በጣም ነው የሚያሳዝነው።

አገሬን ላለ ሰው፣ ለዚያውም ቢሮ ውስጥ ወረቀትና ስክሪብቶ ብቻ ይዞ መገደል፤ ታይቶም ተሰምቶም አይታወቅም። በኢትዮጵያ ታሪክ ለመጀመሪያ ጊዜ ነው። በጣም ነው የማዝነው።

አምባቸው መኮንን (ዶ/ር)

የሰኔ 15/2011 ዓ.ም በባህር ዳርና በአዲስ አበባ ውስጥ የአማራ ክልል ከፍተኛ ባለስልጣናትና የአገሪቱ ጦር ሠራዊት ከፍተኛ መኮንኖች የተገደሉበት ክስተት ፈጽሞ ከኢትዮጵያም አልፎ ዓለምን ያነጋገረ ነበር።

ክስተቱ በአማራ ክልልም ሆነ በአገሪቱ ፖለቲካ ላይ ትልቅ ጠባሳን የጣለ እንደነበር የሚያምኑት ወ/ሮ የሹሜ ባለቤታቸው ባላቸው አቅም ሁሉ ለዘመድ ወገን ደራሽ ሌብነትን የሚጸየፉ እንደነበሩ ይናገራሉ።

“ምንም ምንም የሌለን እንዲህ አድርጉልን እያልን በልመና ነው የምንኖረው። አምባቸው የመንግሥትን ሰባራ ሳንቲም የማይመኝና የማይነካ ንጹህ ህሊናና ንጹህ እጅ የነበረው ንጹህ ደሃ ነበር፤ ንጹህ። በዚህም ደረቴን ነፍቼ አንገቴን ቀና አድርጌ እንድሄድ አድርጎኛል” በማለት በባለቤታቸው ሥራ እንደሚኮሩ ይገልጻሉ።

“የዶክተር አምባቸው ባለቤት ስባል የሌባ ሚስት እንደማልባል አውቃለሁ” የሚሉት ወ/ሮ የሹሜ፤ በአምባቸው (ዶ/ር) ሞት ከቤተሰቡ በተጨማሪ የአማራ ክልል በአጠቃላይ ደግሞ የኢትዮጵያ ሕዝብ ትልቅ ጉዳት ደርሶበታል ብለው ያምናሉ።

አምባቸው (ዶ/ር) በኃላፊነት በቆዩበት ጊዜ በተለይ አንድ ጉዳይ የበለጠ ያስጨንቃቸውና ይቆጫቸው ነበር የሚሉት ባለቤታቸው የሰዎች መፈናቀል ዋነኛው ነገር ነበር።

“‘በኃላፊነት ላይ ሆኜ ሕዝቡ ከቀየው ተፈናቅሎ እረፍት የለኝም’ ይል ነበር። ይህንንም ለማስተካከል “ችግር ባለባቸው ቦታዎች መረጋጋትን ማምጣት ዋነኛው ትኩረቱ ነበር። የቀን ጭንቀቱ የሌሊት ህልሙ ይህ ነገር ነበረ” ይላሉ።

ከዚህ በተጨማሪም “ፋታ አጥቶ ነበር” ነበር የሚሉት ወ/ሮ የሹሜ በጎን ደግሞ “የእሱን አመራርነት ያለውደዱ ሰዎች በዚያም ተኩስ በዚያም ማፈንዳት በዚያም ማቃጠል ሥራቸው ነበር። ይሄ በጣም ያስጨንቀዋል” በማለት የክልሉ ነገር በፌደራል ኃላፊነት ላይ ሆነው ጭምር ያሳስባቸው እንደነበር ይመሰክራሉ።

ለሕዝቡ ሠላምና መረጋጋትረ ማምጣትና ከድህነት እንዲወጣ ለማድረግ ሌት ከቀን ከመጨነቅ ውጪ በሌላው ነገር ግን “በራስ መተማመንና የንጹህ ህሊና ባለቤት ነበረ። ፍርሃትን የማያውቅ ሙልት ያለ ልበ ሙሉ ጀግና ነበር። ሌላ የሚያስጨንቀው ነገር የለውም።”

ወይዘሮ የሹሜ ከአንድ ዓመት በፊት የተለዩአቸው ባለቤታቸው ስላላቸው መልካምነት ለማወቅ አብረውት ከዋሉና ከሰሩ ሰዎች መካከል ከትንሽ እስከ ትልቁ የሚመሰክሩላቸው ሰው አክበሪነታቸውን እንደሆነ ይናገራሉ።

ይህንንም “አምባቸው የበላዩን የማይፈራ የበታቹን የሚያከብር” ሲሉ ይገልጿቸዋል። ሠላምተኛ፣ ትሁትና ሰው ወዳጅ ነበሩ የሚሏቸው የባለቤታቸው መልካም ባህሪያት መለያቸው እንደነበሩ ይመሰክራሉ።

ባለቤታቸው እንደሚሉት አምባቸው (ዶ/ር) ዘመድ ወዳድም ናቸው። “የእኛ ቤት የባለስልጣን ቤት አይመስልም። ዘመድ ጎረቤት የሚያዘወትረው ነው። እሱም ከሥራ ለምሳ ሲመለስ እንግዳ ይዞ ነው የሚመጣው። ጊዜ ሲያገኝ ከጓደኞቹ ከዘምድ ጋር መሆንን የሚመርጥ ሰው ወዳድ ነበር” ይላሉ።

ከሁለት ዓመት በፊት በመጣው ለውጥ ውስጥ ጉልህ አስተዋጽኦ አበርክተዋል ተብለው ከሚጠቀሱት ሰዎች መካከል አንዱ እንደሆኑ የሚጠቀሱት አምባቸው መኮንን (ዶ/ር) ከተደሰቱባቸው ነገሮች መካከል በለውጡ የተገኘው ውጤት ነው።

በተለይ የጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ አህመድ መሾም ትልቅ ደስታን ፈጥሮላቸው እንደነበር ባለቤታቸው ይጠቅሳሉ። “የዚያን ቀን በህይወቱ በጣም ከተደሰተባቸው ቀናት መካከል አንዱ ነበር። ወደ ቤት ሲመጣ እጅግ ተደስቶ ‘ከየትኛውም ጊዜ በላይ በህይወቴ በጣም የተደሰትኩበት ቀን’ ብሎ ነው ያመሸው።”

ወይዘሮ የሹሜ ከነቤተሰባቸው የሚኖሩት አዲስ አበባ ውስጥ ሲሆን የመንግሥት ሠራተኛ ናቸው። ከባለቤታቸው ሞት በኋላ በሚያገኙት ጡረታ ልጆቻቸውን እያስተዳደሩ ነው። አዲስ አበባ አሁን ያሉበት ቤት የመንግሥት የኪራይ ቤት ነው።

በፊትም ባለቤታቸው በሚያገኙት የመንግሥት ደሞዝ ላይ የተወሰነ ገቢን ይመሩ ስለነበረ ቤተሰባቸው የተቀማጠለ ሕይወት አለመልመዱን የሚናገሩት ወ/ሮ የሹሜ “እኔ ተንቀባርሬ እንደፈለኩ እያወጣሁ ስላልኖርኩ በተለመደው ህይወት ቀጥያለሁ” ይላሉ።

ዋነው ግባቸው ልጆቻቸውን ሳይቸገሩ ማሳደግ እንደሆነ የሚገልጹት ከመንግሥትና ከፓርቲው ድጋፍ እንደተደረገላቸው ጠቅሰው አሁንም ቤተሰቡን ለመደገፍ የሚደረጉ ጥረቶች እንዳሉና በአምባቸው (ዶ/ር) ስም ፋውንዴሽን ለማቋቋም ሐሳብ እንዳለ ገልጸዋል።

“የጎደለብን ነገር የለም እግዚአብሔር ይመስገን። በዚያ ላይ መንግሥትም መሪ ድርጅቱም ገንዘብ ሰጥተውናልናል። አሁንም መንግሥትን ሕዝብንም ሁሉንም ነው የምንጠይቀው። ለፋውንዴሽኑን የሚደረግ ትብብር እንጂ ለቤታችንና ለኑሯችን ችግር የለብንም።”

ቤተሰባቸውና ወዳጆቻቸው በአምባቸው መኮንን (ዶ/ር) ስም የሚቋቋመው ፋውንዴሽን በትምህርት እና በበጎ አድራጎት ላይ ያተኩራል ተብሏል።

“አምባቸው የፊዚክስና የሒሳብ ትምህርቶችን የሚወድ በጣም ጎበዝ ተማሪ ነበር። በእነዚህ የትምህርት ዘርፎች ላይ ዝንባሌ ያላቸውን ተማሪዎችን ለመደገፍና ለእሱም ማስታወሻ ለማቆም ነው በፋውንዴሽኑ የታሰበው። ዘወትር መልካም ነገሮችን ለሰዎች ስለሚያስብ የበጎ አድራጎት ሥራዎችን በስሙ እንሠራለን ብዬ እናስባለሁ” ብለዋል።

የአምባቸው መኮንን (ዶ/ር) ህልፈት በቤተሰቡ ላይ የማይጠገን ክፍትት ከመፍጠሩ ባሻገር ለእናታቸውም ሞት ምክንያት ነው ብለው ባለቤታቸው ያምናሉ።

እሳቸው እንደሚሉት ለቤተሰባቸው የመጀመሪያ ልጅ የነበሩት አምባቸው የእናታቸው ተንከባካቢና የዘወተር ተስፋ ነበሩ “የእሱን ሞት ሲሰሙ መኖር አልቻሉም። በሕይወት መቆየትም አዳጋች ሆነባቸው። በዚህም አልበላም አልጠጣም በማለት ራሳቸውን ጉድተዋል” ሲሉ የልጃቸው ሞት የነበረውን ተጽእኖ ይናገራሉ።

ወ/ሮ የሹሜ አምባቸው (ዶ/ር) ሞት በቤተሰቡ ላይ ካሳረፈው ከባድ ጉዳት ሁሉ ትንንሹቹ ልጆቻቸው የአባታቸውን ፍቅር ሳያጣጥሙ መቅረታቸው ነው።

“ከባዱ ጉዳት ልጆች በእሱ ፍቅር በእሱ አዕምሮ ተቀርጸው ማደግ ነበረባቸው። እነዚህ ትንንሽ ልጆች ልክ እንደትልልቆቹ ማሳደግ ነበረበት። በአንድ እናት ብቻ ከባድ ነው። በጣም ነው ያሳዘነኝ። ለሃገር ለህዝብ ሲል ለልጆቹም ሳይሆን የእሱን ፍቅር እና የእሱን ስነምግባር ሁሉንም ነገር ሳያውቁ ሲያድጉ መሞቱ በጣም ያሳዝነኛል” ሲሉ ሳግ በሸፈነው ድምጽ ቁጭታቸውን ገልጸዋል።

ባህር ዳር ላይ የክልሉ ርዕሰ መስተዳደር የነበሩት አምባቸው መኮንን (ዶ/ር)፣ አቶ ምግባሩ ከበደ በምክትል ርዕሰ መስተዳደር ደረጃ የክልሉ ጠቅላይ አቃቤ ሕግ እና አቶ እዘዝ ዋሲ የርዕሰ መስተዳድሩ የሕዝብ አደረጃጀት አማካሪ በክልሉ ምክር ቤት ውስጥ በተፈጸመባቸው ጥቃት ተገድለዋል።

አዲስ አባባ ላይ ደግሞ የአገሪቱ ጦር ኃይሎች ጠቅላይ ኤታማዦር ጄነራል ሰዓረ መኮንንና ጓደኛቸው ጡረታ ላይ የነበሩት ሜጀር ጀመነራል ገዛኢ አበራ ኤታማዦር ሹሙ ቤት ውስጥ ሳሉ አመሻሽ ላይ በተፈጸመባቸው ጥቃት ህይወታቸው አልፏል።