ወጣቶቹ ያለ ፍርድቤት ትዕዛዝ ታስረዋል፤ ቤተሰብ እንዳይጠይቃቸውም ተደርጓል

‎” ወጣቶቹ ያለ ፍርድቤት ትዕዛዝ ታስረዋል፤ ቤተሰብ እንዳይጠይቃቸውም ተደርጓል ” – ቤተሰቦችና ነዋሪዎች

‎በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ጌዴኦ ዞን ኮቾሬ ወረዳ ፍሰሃ ገነት ተብሎ የሚጠራዉ አከባቢ ነዋሪዎች እና ” ልጆቻችን ያለ አግባብ ታስረዋል ” የሚሉት ወላጆች ለቲክቫህ ኢትዮጵያ ቅሬታቸውን አሰምተዋል።

በአከባቢዉ ማህበረሰብ በተደጋጋሚ ሲጠየቅ የቆየዉን የፍሰሃ ገነት የወረዳ መዋቅርነት ጥያቄ ” በማህበራዊ ሚዲያዎች አሰራጭታችኋል ” በሚል ወጣቶችን እያሰሱ እያሰሩ ነው ሲሉ ነው ቃላቸውን የሰጡት።

” ‎ስድስት ወጣቶች ያለ ፍ/ቤት ትዕዛዝ ታስረዋል ” የሚሉት ነዋሪዎቹ የፍሰሃ ገነት ወረዳ በቀደመዉ ጊዜ የወረዳ መዋቅር የነበረዉ መሆኑንና የመዋቅር ጥያቄዉ የሕብረተሰቡ በመሆኑ እነዚህም ወጣቶች ይህንኑ ሃሳባቸዉን በማህበራዊ ሚዲያ በማሰራጨታቸው ብቻ ከስራና የትምህርት ገበታቸው እየታሰሱ መታሰራቸውንና ቤተሰብ እንዳይጠይቃቸዉ መደረጉን ገልጸዋል።

‎” ፖሊስ ልጆቻችንን እንዳናገኝ ከማድረጉም በላይ ‘ በተባባሪነት አስራችኋለዉ ‘ እያለ እያስፈራራን ነዉ ” ሲሉ ለቲክቫህ ኢትዮጵያ የተናገሩት የአከባቢው ወጣቶች ” እኛም እየተፈለግን በመሆኑ አከባቢያችንን ለቀን ሸሽተናል ” ሲሉ ተናግረዋል።

‎ቲክቫህ ኢትዮጵያ ከጌዴኦ ዞንና የኮቾሬ ወረዳ ፖሊስ በጉዳዩ ላይ ተጨማሪ መረጃ ለማግኘት ያደረገው የዞኑ ፖሊስ አዛዥ ፈቃደኛ ባለመሆናቸዉ የኮቾሬ ወረዳ አዛዥ ደግሞ ስልካቸዉ ባለመስራቱ ለጊዜው አልተሳካም።