ኀዘናችን ጥልቅ ነው። ( መልእክተ ብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያርክ )

መልእክተ ብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያርክ (የኀዘን መግለጫ)
=====
በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን፡።
++++
“አድኅነኒ እግዚኦ እስመ ኀልቀ ኄር። አቤቱ፥ አድነኝ፥ ደግ ሰው አልቋልና።” (መዝ. 11፥1)

እግዚአብሔር በየዘመናቱ አገርን ያለ መካሪ፣ ሕዝብን ያለዘካሪ አይተወውም! ለዚህም ምስክሩ ታላቅ አረጋዊ፣ የበሳል አእምሮ ባለቤት፣ አገርን የሚወዱ፣ ሕዝባቸውን የሚያከብሩ፣ የተጠቁት ወዳጅ፣ የትውልድ አባት የሆኑት የክብር ዶክተር ተቀዳሚ ሙፍቲ ሐጂ ዑመር ኢድሪስ ነበሩ፡፡

ኢትዮጵያ በጣት ከሚቆጠሩ አረጋውያን፣ አፈ ማር ከሆኑ መካሪዎችዋ መካከል አንዱ የሆኑትን፣ ለመወደድ የታደሉትን የዘመናችን ጌጥ አጥታለች። ይህንን የድካም ዓለም መገላገል ለእርሳቸው ዕረፍት ቢሆንም ለአገር ግን ታላቅ ጉዳት ከመሆኑም በላይ ዕድሜን ከጥበብ ጋር ያዋሐዱ በሁሉ ዘመን አይገኙምና ኀዘናችን ጥልቅ ነው።

ለቤተሰቦቻቸው፣ ለእስልምና ሃይማኖት ተከታዮችና ለመላው የኢትዮጵያ ሕዝብ መጽናናትን እንመኛለን፡፡

እግዚአብሔር አምላክ ኢትዮጵያንና ሕዝቦችዋን ይባርክ
አሜን።