በኦሮሚያ ክልል ምዕራብ ሸዋ ዞን ‘ፅንፈኛ’ የተባሉ ታጣቂዎች ህጻናትና ሴቶችን ጨምሮ በርካታ ንጹሃንን ገደሉ፡፡
DW : የንጹሃን ግድያ ተደጋግሞ በተሰማበት በምዕራብ ሸዋ ዞን ኖኖ ወረዳ ሃሎዲንቂ ቀበሌ እሁድ ምሽት በግምት ሁለት ሰዓት ግድም የታጠቁ አካላት ባደረሱት ጥቃት ከ20 በላይ ሰዎች ወዲያው መገደላቸውን ተጎጂዎች እና የአከባቢው ነዋሪዎች ተናግረዋል፡፡
ጥቃቱ ከትናንት በስቲያ እሁድ ጥቅምት 09 ቀን 2018 ዓ.ም. ማምሻውን አገር ሰላም ብለው እንደወትሮው ወደ ቤታቸው በገቡ ንጹሃን የኖኖ ወረዳ ሃሎዲንቂ ቀበሌ ነዋሪዎች ላይ ነው የተወሰደው ያሉት አስተያየታቸውን ለዶይቼ ቬለ የሰጡ አንድ የአከባቢው ነዋሪ፤ በአጎራባች የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ጉራጌ ዞን ወረዳዎች የሚንቀሳቀሱ ያሏቸው ታጣቂዎቹ ወሰን ተሻግረው ባደረሱት ጥቃት የአከባቢው ሰላማዊ ዜጎች ላይ ዘግናኝ ያሉትን ግድያ መፈጸሙን ተናግረዋል፡፡ “ጥቃቱን ያደረሱት በአከባቢው የሚንቀሳቀሱ ጽንፈኛ የተባሉ ታጣቂዎች ናቸው” ያሉት አስተያየት ሰጪው፤ በእሁድ ምሽቱ ድንገተኛ ጥቃት 22 ሰዎች ወዲያው መገደላቸውን አመልክተዋል፡፡ በኖኖ ወረዳ ሃሎዲንቂ ቀበሌ ልዩ ስሙ ዳርጌ በሚባል ስፍራ እሁድ ምሽት ከአንድ እስከ ሁለት ሰዓት ግድም በተወሰደው በዚህ ጥቃት ህጻናት እና ሴቶች በስፋት ተጠቂ መሆናቸውን አስረድተዋልም፡፡
ቤተሰቦቻቸው የጥቃቱ ሰለባ መሆናቸውን የነገሩን ነገር ግን አለብን ባሉት የደህንነት ስጋት ስማቸውን ከመግለጽ የተቆጠቡት ሌላው የአከባቢው ነዋሪ፤ “ሰላማዊ ዜጎችን በጭለማ ገብተው ነው የፈጁዋቸው፡፡ አሁን በእሁድ ምሽቱ በዚህ ጥቃት የተገደሉ ሰዎች ቁጥር 29 ደርሰዋል፡፡ 22 ሰዎች ወዲያው መገደላቸው ሲረጋገጥ ቀሪዎቹ አስከሬናቸው በየጥሻው የወደቁና በሆስፒታል ህይወታቸው ያለፉ ናቸው” ብለዋል፡፡ የተገደሉትን ለመለየት ትናንት እስከ ምሽት የአስከሬን አሰሳ በአአከባቢው ሲደረግ ነበር ያሉት አስተያየት ሰጪው፤ ከሟቾች አባወራ የሆኑ ትልልቅ ሰዎች ከስድስት የማያልፉ ሲሆን ቀሪዎቹ ህጻናት እና አብዛኛው ደግሞ ታዳጊ ተማሪዎች እና ሴቶች ናቸው ብለዋል፡፡
በዚህ ወረዳ ተመሳሳይ ትቃቱ ለምን ተደጋገመ?
ለደህንነታቸው ሲባል ስማቸው ያልተጠቀሰው አስተያየት ሰጪ በኦሮሚያ ክልል ምዕራብ ሸዋ ዞን አጎራባች በሆነው የጉራጌ ዞን አበሽጌ ወረዳ ውስጥ ወታደራዊ ስልጠና የሚወስዱ ያሏቸው ታጣቂዎች በተደጋጋሚ እየገቡ ህጻናትን ጨምሮ ያገኙትን በምንም ፖለቲካ ውስጥ የሌሉ ሰላማዊ ሰዎችን እያጠቁ ይመለሳሉ፡፡ “እነዚህ ሟቾች ምንም ውስጥ የሌሉና ምንም ጥፋት የሌለባቸው ናቸው” ያሉን አስተያየት ሰጪው ጥላቻ እና ማንነት ላይ የሚያተኩር ጥቃት ካልተባለ ውጪ ከሶስት ዓመት እስከ 14 ዓመት እድሜ ክልል ውስጥ የሚገኙ ህጻናት ምን ውስጥ ይሆናሉ ተብሎ ይታሰባል ሲሉ ጠይቀዋል፡፡ በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ጉራጌ ዞን አበሽጌ ወረዳ በተለያዩ ቀበሌዎች የሚንቀሳቀሱ ጥቃት አድራሾቹ በምዕራብ ሸዋ ዞን ኖኖ ወረዳ በተለያዩ ጊዜያት በተፈጠረ ግጭት ቤተሰቦቻቸውን ይዘው የተፈናቀሉም እንደሚገኙባቸው ገልጸዋል፡፡ አሁን ላይ ጥቃት ከሚያደርሱ ታጣቂዎቹ አብዛኞቹ በ2016 ዓ.ም. በአንድ ሰርግ ላይ ቦምብ ተጥሎ 36 ሰዎች ግድም መገደላቸውን ተከትሎ ከአከባቢው የተፈናቀሉ ናቸውም ብለዋል እኚህ አስተያየት ሰጪ የአከባቢው ነዋሪ፡፡
ሰኔ ወር 2016 ዓ.ም. በዚሁ ኖኖ ወረዳ ቆንዳላ ቀበሌ በአንድ ሰርግ ቤት ላይ ቦምብ ተጥሎ ሙሽሮችን ጨምሮ 36 ሰዎች ከተገደሉ በኋላ ተደጋጋሚ የንጹሃን ጥቃቶች እና የግድያ ዜናዎች ከዚህ አከባቢ ተለይቶ አያውቅም፡፡ በቅርቡ 2017 ዓ.ም. ሰኔ ወር ላይ ዳግም በንጹሃን ላይ ባነጣጠረው የዚሁ አከባቢ ጥቃት ከአንድ ቤት የተገደሉ ስድስት የቤተሰብ አባላትን ጨምሮ 14 ሰላማዊ ነዋሪዎች ማለቃቸውን መዘገባችን ይታወሳል፡፡
የአሳሳቢው ተደጋጋሚ ጥቃት ማቆሚያው የት ይሆን?
የጸጥታ ስጋቱ በተደጋገመበት የኖኖ ወረዳ አዋሳኝ ቀበሌያት አከባቢ የነዋሪዎቹ ስጋት ከጊዜ ወደ ጊዜ ዘላቂ እልባት ከማግኘት ይልቅ እያደር እየከፋና እየተባባሰ መምታቱን የአከባቢው ነዋሪዎች ይገልጻሉ፡፡ በዚህ ላይ ማረጋገጫ ለማግነትና መንግስት በዘላቂነት የዜጎቹን የደህንነት ስጋት ለመፍታት ምን እየሰራ ነው የሚለውን ለመጠየቅ ዶይቼ ቬለ ለወረዳው ዋና አስተዳዳሪ አቶ ወንዳፍራሽ ሉሌሳ እና ሌሎች የአከባቢው ባለስልጣናት የስልክ ጥሪ እና የጽሁፍ መልእክት በመላክ ጥረት ቢያደርግም ለዛሬ አልሰመረም፡፡
አስተያየት ሰጪ የአከባቢው ነዋሪዎች ግን አሁንም ስጋታቸው ብርቱ ነው፡፡ “አሁን ምርቱን መሰብሰብ በተጀመረበት ወቅት የተቃጣው የፀጥታ ስጋት እንደመሆኑ በጣም ከባድ ነው፡፡ ጥቃት አድራሾቹም በብዛት ገበሬው ተረጋግቶ ምርት እንዳይሰበስብ ነው ፍላጎታቸው፡፡ የመንግስት ፀጥታ አካላትም መሃል እየሄዱ ማህበረሰቡ መሃል ግጭት እንዳይፈጠር እየታገሉ መሆኑን እንመለከታለን እንጂ መንግስት በዜጎቹ ጥቃት ላይ ማብራሪያ እየሰጠ አይደለም” ብለዋል፡፡
ኦሮሚያ ክልልን በሚያዋስነው የማዕከላዊ ኢትዮጵያክልል ጉራጌ ዞን አበሽጌ ወረዳ ውስት ታጥቀው የሚንቀሳቀሱ የተባሉ ታጣቂዎች በቅርቡ ከወልቂጤ ከተማ ወጣ ብሎ በሚገኘው ከጅማ ወደ አዲስ አበባ በሚወስደው መንገድ ላይ በተደጋጋሚ ሾፈሮች ላይ ጥቃት ማድረሳቸው መሰማቱን ተከትሎ የፌዴራል ፖሊስን ጨምሮ የሁለቱ ክልሎች የፀጥታ አካላት በወልቂጤ ከተማ ተገናንተው በመምከር የአከባቢውን ፀጥታ ማረጋጋት በሚቻልበት መንገድ ላይ አቅጣጫ መስጠታቸው መነገሩ ይታወሳል፡፡