“የዘመኑን ጥበብና ስልት ያልተከተለ ሐዋርያዊ ተልእኮአችንና አስተዳደራችንም ምእመናንን አላረካም፤ ክፍተቱ የሚድያ ቀለብ ከመሆንም አልፎ በጎቻችን በሌሎች እንዲዘረፉ ትልቅ በር እየከፈተ ነው” ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ
የቅዱስነታቸው የቅዱስ ሲኖዶስ ምልዓተ ጉባኤ የመክፈቻ መልእክት ከዚህ እንደሚከተለው ይቀርባል።
በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን!
• ብፁዕ አቡነ ሳዊሮስ
የመንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ቤተ ክህነት ዋና ሥራ አስኪያጅ፤
• ብፁዕ አቡነ ዲዮስቆሮስ
የቅዱስ ሲኖዶስ ዋና ጸሐፊ፣
• ብፁዓን አበው ሊቃነ ጳጳሳት የቅዱስ ሲኖዶስ አባላት፣
በአጠቃላይ በዚህ ዓመታዊ ቅዱስ ጉባኤ የተገኛችሁ በሙሉ፤
የጎደለብንን እየሞላ አገልግሎታችንን እያቃና ከዚህ ላደረሰን፣ ይህንን ዓመታዊና ሐዋርያዊ ጉባኤያችንን ለማካሄድም ለሰበሰበን ለአምላካችን ለእግዚአብሔር ምስጋና እናቀርባለን፡፡
“ወእፌጽም ታሕጻጸ ሕማሙ ለክርስቶስ በሥጋየ በእንተ ሥጋሁ እንተ ይእቲ ቤተ ክርስቲያኑ፡- ስለ አካሉ ማለትም ስለ ቤተክርስቲያኑ ስል በሥጋዬ በክርስቶስ መከራ የጎደለውን እፈጽማለሁ” (ቈላ.፩÷፳፬)
ያለንበት ዓለም በሁሉም ነገር በጉድለቱ የሚታወቅ ነው፤ ጉድለት ባይኖርና ሁሉም የሞላለት ቢሆን ኖሮ ፍጥረት እርስ በርስ የሚተረማመስበት ሁኔታ አይኖርም ነበር ወይም አሁን ባለበት ደረጃ የከፋ አይሆንም ነበር፡፡
እግዚአብሔር ሁሉንም አሟልቶ መፍጠር ወይም መስጠት የሚችል ከሃሊ አምላክ ቢሆንም፣ እሱ ባወቀ ፍጥረትን ሁሉ ጉድለት ያለበት አድርጎ ፈጥሮታል፤ በዚህም ምክንያት እያንዳንዱ ጉድለቱን ለመሙላት በሚያደርገው ፍትጊያ እየተጋጨ እርስ በርስ ሲተረማመስ ማየቱ የተለመደ ነው፡፡ ምድራዊቷ ቤተ ክርስቲያንም በጐዶሎው ዓለም እስካለች ድረስ ከሚመጣው ፈተና አታመልጥም፤ ይህም በመሆኑ ቅዱስ ጳውሎስ ለቈላስይስ ሰዎች “የጎደለውን እፈጽማለሁ” በማለት ሲጽፍ እናስተውላለን፡፡
• ብፁዓን አበው ሊቃነ ጳጳሳት የቅዱስ ሲኖዶስ አባላት!
በጐዶሎው ዓለም የምትኖር ቤተ ክርስቲያን ጉድለቷን ለመሙላት ብዙ መሥዋዕትነት ከፍላለች፤ ቤተ ክርስቲያን ለቀጣዩ ትውልድ መሸጋገርና የጐደለባትን ለመሙላት ስትል ከቅዱሳን ሐዋርያት አንሥቶ እስካለንበት ዘመን ድረስ ብዙና የብዙ ብዙ አበው ካህናትን፣ ሊቃውንትንና ምእመናንን ከደም ጠብታ፣ እስከ ቁስ ስጦታ ገብራለች፡፡
አሁን በምድር ላይ ያለችው ቤተ ክርስቲያን የዚህ ሁሉ ውጤት ናት፤ ቤተ ክርስቲያን እንደ ሌላው ጊዜ ሁሉ ዛሬም የጐደለባት ብዙ ነገር አለ፤ በተቻለ መጠን እርሱን ለሟሟላት መጣርና በተሻለ ሁኔታ ወደፊት ማሻገር ደግሞ የዚህ ጉባኤ ተቀዳሚ ተግባር ነው፡፡ በዚህ ረገድ ይህ ጉባኤ ብቻው አይደለም፤ በብዙ ሚሊዮኖች የሚቈጠሩ የእግዚአብሔር ልጆች ድምፁን ለመስማት ከዙሪያው ሆነው በጉጉት ይጠብቃሉ፡፡ እነኝህ የእግዚአብሔር ልጆች ለመስማት ብቻ ሳይሆን ድምፁን ሰምተው ለመታዘዝም የተዘጋጁ ናቸው፣ ከሁሉ በላይ ደግሞ “ሁለትም ሦስትም ሆናችሁ በስሜ በተሰበሰባችሁበት እኔ በመካከላችሁ እገኛለሁ” በማለት ጉባኤውን የመሠረተው አምላክ ከዚህ ጉባኤ መካከል አለ፡፡
በመሆኑም ይህ ጉባኤ የተወሰን አባቶች ብቻ ሳንሆን ብዙ ሰማውያንና ምድራውያን ባለድርሻ ያሉበት፣ መንፈስ ቅዱስም በመንፈስ የሚመራው እንደሆነ የማይታበል ነው፡፡ ከዚህ አንጻር ጉባኤው በምድር ያለችውን የእግዚአብሔር መንግሥት በበላይነት የሚመራ ነውና፣ ያለበት ኃላፊነት ከባድና እጅግ የላቀ ነው፡፡ ጉባኤው ኃላፊነቱን በአግባቡ ሲወጣ የሚሰጠው ሽልማት ታላቅ እንደሆነ ሁሉ፣ ኃላፊነቱን በትክክል ካልተወጣ ደግሞ ተጠያቂነቱ በዚያው ልክ ከባድ ነው፤ ብዙ ከተሰጠው ብዙ ይፈለጋል ተብሎአልና፡፡
• ብፁዓን አበው ሊቃነ ጳጳሳት የቅዱስ ሲኖዶስ አባላት!
እኛ በአገልግሎትና በመሪነት በምንገኝበት በዚህ ዘመን ቤተ ክርስቲያን የጐደሉባት ነገሮች ብዙ ናቸው፤ ከሁሉ በላይ በውስጣችን የአንድነት ጐድለት በስፋት ይታያል፤ ለተሰየምንለት መለኮታዊ ተልእኮ አንድ ሐሳብ፣ አንድ ቃል፣ አንድ ልብ ሆነን መሰለፍ ያለመቻል ክፍተት እየተንጸባረቀ ነው፡፡ የዘመኑን ጥበብና ስልት ያልተከተለ ሐዋርያዊ ተልእኮአችንና አስተዳደራችንም ምእመናንን አላረካም፤ ክፍተቱ የሚድያ ቀለብ ከመሆንም አልፎ በጎቻችን በሌሎች እንዲዘረፉ ትልቅ በር እየከፈተ ነው፡፡ በእነዚህ ዓበይት ጉዳዮች እና በመሳሰሉት ጉድለቶቻች ላይ ፈጣን፣ ቈራጥና አዋጭ የሆነ ሥራ ካልሰራን ለወደፊት የቤተ ክርስቲያንን ህልውና ጥያቄ ውስጥ መክተቱ አይቀሬ ነው፡፡
• ብፁዓን አበው ሊቃነ ጳጳሳት የቅዱስ ሲኖዶስ አባላት!
ቤተ ክርስቲያናችን በተጠቀሱት ችግሮች ተከባ ባለችበት ሁኔታ የሀገራችን ሰላም መቀዛቀዝ ደግሞ ሌላው ተጨማሪ ጉድለትን እያስከተለብን ነው፡፡ አማንያን የመንፈስና የሥነ ልቡና ሰላም ከማጣታቸውም በላይ አካላቸው ለሞትና ለጉዳት፤ ሃብታቸው ለዝርፊያና ለውድመት እየተዳረገ ነው፡፡ ይኽም ሁሉ ሆኖ ፍትሕን እያገኙ አይደለም፤ አብያተ ክርስቲያናትም በምእመናን ፍልሰት እየተዘጉም እየተቃጠሉም ነው፡፡
ከዚህም ሌላ የሌለን ነገር እንዳለ አስመስሎ ከየአቅጣጫው የሚወረወረው የባዕዳን ስም የማጥፋት ዘመቻ፣ የቤተ ክርስቲያኗን እምነት ከመንቀፍና ከማብጠልጠል በላይ አልፎ የቅዱሳንን ቅዱስ ሥዕል በአደባባይ እስከ መቅደድ ተደርሶአል፤ በቤተ ክርስቲያናችን ህልውና ላይ በዓላማ የተነሡ አካላት የላኳቸው እንዳሉ በሚመስል መልኩ በስመ ተሐድሶ የሚደረገው እንቅስቃሴ የኛው መለያ የሆነውን ንዋየ ቅድሳትና ልብሰ ተክህኖ፣ መዝሙርና ሥርዓተ አምልኮ በመጠቀም ቤተ ክርስቲያናችንን በአደባባይ እየተዳፈረ ይገኛል፡፡
ይህ አላስፈላጊ ተግባር የሀገሪቱን ዜጎች በእኩልነት የሚያስተዳድረውን ሕገ መንግሥት በቀጥታ የሚፃረር ድርጊት ነው፤ ሆኖም በሕግ የሚጠይቅና የሚያስቆም አካል አልተገኘም፤ እኛም ዝምታን የመረጥን መስለናል፡፡ ነገር ግን መፍትሔው ዝምታ ሳይሆን በሕግ አግባብ ነገሩን ለመፍታት መንቀሳቀስ እንደሆነ ሁሉም ሊገነዘበው ይገባል፡፡
• ብፁዓን አበው ሊቃነ ጳጳሳት የቅዱስ ሲኖዶስ አባላት!
በዘመናችን እየተከሠተ ያለው ችግር ስንዘረዝር ውለን ብናድር መናገሩ በራሱ መፍትሔ ሊያመጣልን አይችልም፤ ጉባኤው ከዚህ በላይ መናገር እንደሚችልም እንገነዘባለን፤ ነገር ግን ለዚህ ሁሉ ችግር ዘላቂ መፍትሔ ሊያመጣ የሚችል መደላድል ይህ ጉባኤ በዚህ ስብሰባ ሊተልም ይገባል ብለን ከአደራ ጋር ማሳሰብ እንወዳለን፡፡ በሌላ በኩል በሀገራችን ያለው ያለመረጋጋት በሕዝባችን አጠቃላይ ሥነ ልቡና በሀገሪቱ አንድነትና ዕድገት የሚያስከትለውን ጫና በቀላሉ የሚታይ አይሆንም፤ የሕዝቡ ሥነ ልቡና ከተጐዳ የነገው ዕድል ጤናማ ይሆናል ተብሎ አይታሰብም፡፡
ችግሩ እየታየ ያለው በዋናነት በሀገራችን ፖለቲከኞች በመሆኑ ነገሩ የተወሳሰበና የተራዘመ እንዲሆን አድርጎታል፤ በመሆኑም ይህ የርስ በርስ ግጭት ቆሞ ችግሮች በውይይትና በድርድር በመፍታት የወንድማማች እልቂት የሚያስቆም የሰላምና የዕርቅ ዕድል ቅድሚያ እንዲሰጠው ጉባኤው የበኩሉን ጥረት ማድረግ ይገባዋል፡፡ የነገው ትውልድ ልማታዊ ተስፋ እውን ሊሆን የሚችለው ሰላምና አንድነት ሲኖር ነውና መንግሥት፣ ተፎካካሪ ፖለቲከኞችና ነፍጥ ያነሡ ወገኖች ሁሉ ለሰላም መስፈንና ለልማት ዕድገት መረጋገጥ ሲባል ወደ መግባባት እንዲመጡ በእግዚአብሔር ስም አባታዊ ጥሪያችንን እናስተላልፋለን፡፡
በመጨረሻም ዓመታዊውና ቀኖናዊው የቅዱስ ሲኖዶስ ዓቢይ ጉባኤ በዛሬው ዕለት በጸሎት የተከፈተ መሆኑን ለሕዝበ ክርስቲያኑ በእግዚአብሔር ስም እናበስራለን፡፡
እግዚአብሔር የተባረከና የተቀደሰ ጉባኤ ያድርግልን፤
እግዚአብሔር ኢትዮጵያንና ሕዝቦችዋን ይባርክ
ወስብሐት ለእግዚአብሔር፤ አሜን፡፡
አባ ማትያስ ቀዳማዊ
ፓትርያርክ ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ
ሊቀ ጳጳስ ዘአክሱም ወዕጨጌ ዘመንበረ ተክለ ሃይማኖት
ጥቅምት ፲፪ ቀን ፳፻፲፰ ዓመተ ምሕረት
አዲስ አበባ – ኢትዮጵያ