" /> በኮሮና ቫይረስ የሚከሰተው በሽታ ‘ኮቪድ-19’ (Covid-19) የሚል ስም ተሰጠው | Mereja.com - Ethiopian Amharic News

በኮሮና ቫይረስ የሚከሰተው በሽታ ‘ኮቪድ-19’ (Covid-19) የሚል ስም ተሰጠው

በኮሮና ቫይረስ የሚከሰተው በሽታ ‘ኮቪድ-19’ (Covid-19) የሚል ስም ተሰጥቶታል – የዓለም ጤና ድርጅት

ክትባቱ በ18 ወራት ውስጥ ሊቀርብ እንደሚችልም ተገልጿል

Image may contain: 1 person, eyeglasses and closeupበኮሮና ቫይረስ የሚከሰተው በሽታ ‘ኮቪድ-19’ (Covid-19) የሚል ስም እንደተሰጠው የዓለም ጤና ድርጅት ዋና ዳይሬክተር ዶ/ር ቴድሮስ አድሃኖም ገለጹ።

በቫይረሱ ለሚከሰተው በሽታ ስም እንዲሰጠው ያስፈለገው በቫይረሱ የሞቱት ሰዎች ቁጥር ከ1 ሺህ በላይ መድረሳቸውን እና በ10 ሺህዎች የሚቆጠሩት ደግሞ በቫይረሱ መያዛቸውን ተከትሎ ነው።

ዶ/ር ቴድሮስ ቫይረሱን ለመከላከል በአፅንኦት መሠራት አለበት ሲሉም ለዓለም ማኅበረሰብ ጥሪ አቅርበዋል።

ተመራማሪዎች በቫይረሱ ዙሪያ ብዥታ እንዳይፈጠር እና በአንድ የተወሰነ ቡድን ወይም ሀገር ላይ ማግለል እንዳይከሰት በቫይረሱ ለሚከሰት በሽታ ኦፊሴላዊ ስም እንዲሰጠው ሲጠይቁ ቆይተዋል።

ዶ/ር ቴድሮስም “ለበሽታው የሚሰጠው ስም የትኛውንም መልክዓ ምድር፣ እንስሳ፣ ግለሰብ ወይም ቡድን የማይወክል እና በቀላሉ ተነባቢ የሆነ እንዲሁም ከበሽታው ጋር ተያያዥ የሆነ መሆን አለበት” ብለዋል።

ለበሽታው ስም ሲሰየም ተገቢ ያልሆነ እና በሌሎች ላይ መድሎ የሚፈጥር ስምን ከመጠቀም መቆጠብ ተገቢ መሆኑንም ነው ኃላፊው ያስታወቁት።

አዲሱ ስም [ማለትም ‘ኮቪድ-19’ (‘Covid-19’)] የተወሰደው ‘ኮሮና’ /corona/፣ ‘ቫይረስ’ /virus/ እና ‘ዲዚዝ’ /disease/ ከሚሉ ቃላት ሲሆን 19 ደግሞ የቫይረሱ ወረርሽኝ ሪፖርት የተደረገበት የፈረንጆቹ 2019 ዓ.ም መሆኑን ቢቢሲ ዘግቧል።

በሌላ በኩል ቫይረሱ ላይ ያተኮረው የመጀመሪያው ክትባት በ18 ወራት ወስጥ ሊቀርብ እንደሚችል የዓለም ጤና ድርጅት ዋና ዳይሬክተር ዶ/ር ቴድሮስ ማስታወቃቸውን ሮይተርስ ዘግቧል።

ዶ/ር ቴድርስ ይህን ያስታወቁት በትናንትናው ዕለት ጄኔቫ ውስጥ ባደረጉት ገለጻ ሲሆን “ክትባቱ እስከሚጀምር አሁን ላይ ያሉንን መሣሪያዎች ሁሉ ተጠቅመን ቫይረሱን ለመከላከል ጥረት ማድረግ አለብን” ብለዋል።

ምንጭ፤ ሮይተርስ


የመረጃ ቲቪ አባል በመሆን የስራችን ጥራት እንዲሻሻል ያግዙን። አባል ለመሆን እዚህ ላይ ይጫኑ።
JOIN Mereja TV