ኢትዮጵያና ግብፅ በታላቁ የሕዳሴ ግድብ ግንባት ዙሪያ ሊግባቡ የቻሉ አይመስልም – ወደየት ያመራ ይሆን?


ኢትዮጵያን ካጋጠሟት እጅግ ውስብስብ ችግሮች ለማዳን የተለያዩ ጠቃሚ ሃሳቦችን እና ገንቢ ትችቶችን የሚያቀርቡ ነፃ ሚዲያዎች ወሳኝ ሚና እንደሚጫወቱ ይታወቃል። ስለዚህም ኢትዮ360፣ መረጃ ቲቪ፣ አዲስ ድምጽ፣ ምንሊክ ቲቪ እና ሌሎችም የኢትዮጵያዊነት አጀንዳ የሚያራምዱ ሚዲያዎች በመተባበር ፕሮግራሞቻቸውን በሳተላይት ቲቪ ለኢትዮጵያ ህዝብ በማቅረብ ላይ ይገኛሉ። እነዚህ ሚዲያዎች የፈጠሩት ማህበር የሳተላይት ወጪውን መሸፈን እንዲያስችለው ይህን የጎፈንድሚ ፔጅ ከፍተናል → እዚህ ሊንክ ላይ ይጫኑ። ለትብብርዎ እናመሰግናለን።

BBC Amharic : ኢትዮጵያና ግብፅ በታላቁ የሕዳሴ ግድብ ግንባት ዙሪያ ሊግባቡ የቻሉ አይመስልም። የኢትዮጵያ፣ ግብጽ እና ሱዳን የውጪ ጉዳይ ሚንስትሮች ከትናንት ጀምሮ በዋሽንግተን ዲሲ ተገናኝተው እየመከሩ ይገኛሉ።

አራት የቴክኒክ ውይይቶችን አድርገው ከመግባባት ላይ ሊደርሱ ያልቻሉት ኢትዮጵያና ግብፅ ዛሬ የመጨረሻውን ውይይት አድርገው ከስምምነት መድረስ የማይቻል ከሆነ ከዚህ ቀደም ሶስቱ ሃገራት የተፈራረሙት ‘ዲክላሬሽን ኦፍ ፕሪንስፕልስ’ አንቀጽ 10 ተግባራዊ ይደረጋል።

የሕዳሴው ግድብ ሲጠናቀቅ በአፍሪቃ ግዙፉ ከውሃ የኤሌክትሪክ ኃይል የሚያመነጭ ግድብ ይሆናል ተብሎ ይጠቃል። ግንባታው 2003 ላይ የተጀመረው ይህ ግድብ፤ 85 በመቶ ውሃ ለናይል ወንዝ የሚያበርከትው አባይ ወንዝን መሠረት አድርጎ ነው የሚታነፀው።

ነገር ግን የግድቡ ግንባታ ለግብፅ ሰላም የሰጣት አይመስልም። ከግድቡ ግንባታ መጀመር አንስቶ ኢትዮጵያ እና ግብጽ አንድ ጊዜ ሲኮራረፉ በሌላኛው ሲታረቁ ዓመታት ተቆጥረዋል።

በዚህ ቅራኔ ሳቢያ ሳዑዲ አራቢያ ሁለቱን ሃገራት ለማግባባት በሚል ደፋ ቀና ስትል ጉዳዩ ወደ ጦርነት ሊያመራ ይችላል ተብሎ ተሰግቶ ነበር። አሁን ደግሞ አሜሪካ ሁለቱን ሃገራት ‘ላስታርቅ’ እያለች ነው። ምንም እንኳ የትራምፕ መንግሥት ለግብፅ ይወግናል ሲሉ የአሜሪካንን ጣልቃ ገብነት ያልስደሰታቸው ቢኖሩም።

የግብጽ ስጋት

የግብፅ ፍራቻ ኢትዮጵያ ግድቡን መሙላት ስትጀምር ከአባይ ወንዝ ወደ ናይል የሚወርደው የውሃ መጠን ይቀንሳል ነው። ይህ ደግሞ በተዘዋዋሪ ለኢትዮጵያ ኃያልነት ያድላታል።

ምንም እንኳ በውሃ የሚሠሩ ኃይል አመንጭ ግድቦች ውሃ ባያባክኑም ኢትዮጵያ በምን ያህል ነው ግድቡን የምትሞላው የሚለው ግብፅን ከሚያሳስቡ ጉዳዮች አንዱ ነው።

ግድቡ ሲጠናቀቅ ግሬተር ሎንዶን [74 ቢሊዮን ኪዩቢክ ሜትር ውሃ] በላይ ቦታ ይይዛል የሚባልለት የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ለመሙላት የሚወስድባት ጊዜ ረዘም ያለ ከሆነ ግብፅ ይህን ያህል ጭንቀት ይኖርባታል ተብሎ አይታሰብም።

ሶስቱ ሃገራት ከዚህ ቀደም በነበራቸው ስምምነት መሠረት ኢትዮጵያ ግድቡን በሰባት ዓመታት ሞልታ ማጠናቀቅ ትፈልጋለች።

«ዕቅዳችን በሚመጣው ክረምት ሙሙላት መጀመር ነው። በሁለት ማመንጫዎች [ተርባይን] በመታገዝ ታኅሣሥ 2013 ላይ ኃይል ማመንጨት እንጀምራለን» ሲሉ የውሃ፣ መስኖና ኢነርጂ ሚኒስትሩ ስለሺ በቀለ [ዶ/ር ኢንጅነር] መናገራቸው አይዘነጋም።

ግብጽ ግን ሰባት ዓመት የሚለው የተዋጣላት አይመስልም። ለዚህ ደግሞ እንደ ምክንያት የጠቀሰችው ውሃው በአንድ ጊዜ መጠኑ እንዳይቀንስ የሚል ነው።

  የውሃ፣ መስኖና ኤነርጂ ሚኒስትር ስለሺ በቀለ [ዶ/ር ኢንጅነር]
የውሃ፣ መስኖና ኤነርጂ ሚኒስትር ስለሺ በቀለ [ዶ/ር ኢንጅነር]

ባፈለው ሳምንት አዲስ አበባ ላይ ሶስቱ ሃገራት ተገናኝተው ያደረጉት ውይይት ፍሬያማ አልሆነም። የውሃ፣ መስኖና ኤነርጂ ሚኒስትሩ ግብፅ ስምምነት ላይ የመድረስ ሃሳብ የላትም ሲሉ ይወቅሳሉ።

«ስምምነት ላይ ለመድረስ ዝግጁ ሆነው የመጡ አልመሰለኝም። በዚያ ላይ አዲስ የሙሊት መርሃ ግብር ይዘው መጥተዋል። ይህ መርሃ ግብር ከ12-21 ዓመታት የሚል ነው። ይህ ደግሞ በፍፁም ተቀባይነት የለውም።»

የግብፁ ውሃ ሚኒስትር ሞሐመድ አብደል አቲ በበኩላቸው ሶስቱ ወገኖች በግድቡ አሞላል ዙሪያ አሁን የተሻለ መግባባት ላይ ናቸው ሲሉ ተደምጠዋል።

የግብፅ አቋም

ግብፅ 90 በመቶ የውሃ ፍላጎቷን የምታሟላው ከናይል ወንዝ ነው። ሃገሪቱ ሁልጊዜም ስትል እንደምትደመጠው የናይል ወንዝ ሕልውና ማለት የግብፅ ሕልውና ማለት ነው።

የግብፁ ፕሬዝደንት አብድል ፋታህ አል-ሲሲ ባለፈው መስከረም ግብፅ የራሷ ችግር ላይ [የአረቡ ዓለም አብዮት] ባትሆን ኖሮ ኢትዮጵያ ግድቡን መገንባት ስትጀምርም ነበር ማለታቸው ይታወሳል።

ከአባይ ወንዝ የሚመጣው የውሃ ኃይል ቀነሰ ማለት የናስር ሐይቅ አቅም ተዳከመ ማለት ነው። ናስር ኃይቅ ደግሞ ግብፅ አብዛኛውን የኤሌክትሪክ ኃይሏን የምታገኝበት የአስዋን ግድብ ደጀን ነው።

የናይል ወንዝ በግብፅ

ግብፅ እንደ ቅድመ መስማሚያ ካስቀመጠቻቸው ሃሰቦች አንዱ የአስዋን ግድብና የሕዳሴ ግድብ ይገናኙ የሚል ነው። ‘ይህ ተግባራዊ ሊሆን አይችልም’ ብለው ለግብጽ ተደራዳሪዎች እንደ ነገሯቸው ሚኒስትር ስለሺ ይናገራሉ።

ኢትዮጵያ ግዙፍ ግድብ መገንባት ለምን አስፈለጋት?

በብዙ ቢሊዮን ብር ወጪ የሚገነባው የሕዳሴ ግድብ የኢትዮጵያ ዕድገት ልብ ምት ተደርጎ ይቆጠራል። ግድቡ ሲጠናቀቅ 6ሺህ ዋት የኤልክትሪክ ኃይል የማመንጨት አቅም ይኖረዋል።

በርካታ ሕዝብ የኤሌክትሪክ ኃይል እንደልብ ለማያገኝባት ኢትዮጵያ የግድቡ አስፈላጊነት የማያጠያይቅ ነው። ከዚህ ባለፈም እያደገ ለመጣው የማኒዩፋከቸሪንግ ዘርፍ ትልቅ እፎይታን የሚሰጥ ነው።

ኢትዮጵያ ግድቡ ሙሉ በሙለ ኃይል ማመንጨት ሲጀምርላት ለጎቤት ሃገራትም ኮረንቲ መሸጥ ትችላለች። ሱዳን፣ ደቡብ ሱዳን፣ ኤርትራና ጂቡቲ ከሕዳሴው ግድብ ጥቅም ሊያገኙ ይችላሉ።

ሌላኛው ኢትዮጵያ ከግድቡ የምታገኘው ጥቅም በገንዘብ የማይለካ ነው ይላሉ ባለሙያዎች – ሉዓላዊነት።

ሁኔታዎች ወደ ጦርነት ያመሩ ይሆን?

ሁለቱ ሃገራት ካልተስማሙ ወደ ግጭት ሊያመሩ ይችላሉ የሚል ፍራቻ ነበር። 2005 ላይ የተለቀቀ አንድ ተንቀሳቃሸ ምስል የግብፅ ፖለቲከኞች ኢትዮጵያ ላይ ሊሰነዘሩ የሚችሉ ጥቃቶች ላይ ሲመክሩ አሳይቷል።

ፕሬዝደንት አብዱል ፈታህ አል-ሲሲም ግብፅ የትኛውንም ዓይነት እርምጃ ትወስዳለች ሲሉ ተሰምተዋል። የኢትዮጵያው ጠቅላይ ሚኒስትር አበይ አሕመድም ለሕዝብ እንደራሴዎች ባደረጉት ንግግር የትኛውም ዓይነት ኃይል ኢትዮጵያን አያቆማትም ሲሉ ተናግረዋል።

አሜሪካ በሁለቱ ሃገራት መካከል ጣልቃ መግባቷ የጉዳዩን አሳሳቢነት ያሳያል። ግብጽ የአሜሪካን አደራዳሪነት ቀድም ጠይቃ ነበር። ኢትዮጵያ በበኩሏ የአሜሪካን ጣልቃ ገብነት አልፈቀደችም ነበር። በአሁኑ ወቅት የሶስቱ ሃገራት የቴክኒክ ኮሚቴዎች ባደረጓቸው ውይይቶች ላይ አሜሪካ እና የዓለም ባንክ የታዛቢነት ድርሻ ኖሯቸው በውይይቶቹ ላይ ተካፋይ ሆነው ቆይተዋል።

በቀጣይስ?

የሶስቱ ሃገራት የውጪ ጉዳይ ሚንስትሮች ከትናነት ጀምሮ አሜሪካ ላይ ተገናኝተው በመምከር ላይ ናቸው።

ሃገራቱ በቀጠሯቸው መሠረት ጥር 6/2012 መስማማት ላይ ካልደረሱ ጉዳዩ ወደየ ሃገራት መሪዎች ወይም ወደ ሶስተኛ አደራዳሪ አካል ሊመራ ይችላል።

«የመጀመሪያው አማራጭ ከአወያይ አካል ቁጭ ብሎ ለመስማማት መሞከር ነው። ሶስቱም ሃገራት መስማማት አለባቸው። አንቀፅ 10 በአንድ ሃገር ይሁንታ ላይ ብቻ ተመሥርቶ ሃሳብ ይፅደቅ አይልም» ይላል የኢትዮጵያ ውሃ ሚኒስትር ስለሺ በቀለ።