ታሪክ ትምህርት ቤት እንጂ እስር ቤት መሆን የለበትም


ኢትዮጵያን ካጋጠሟት እጅግ ውስብስብ ችግሮች ለማዳን የተለያዩ ጠቃሚ ሃሳቦችን እና ገንቢ ትችቶችን የሚያቀርቡ ነፃ ሚዲያዎች ወሳኝ ሚና እንደሚጫወቱ ይታወቃል። ስለዚህም ኢትዮ360፣ መረጃ ቲቪ፣ አዲስ ድምጽ፣ ምንሊክ ቲቪ እና ሌሎችም የኢትዮጵያዊነት አጀንዳ የሚያራምዱ ሚዲያዎች በመተባበር ፕሮግራሞቻቸውን በሳተላይት ቲቪ ለኢትዮጵያ ህዝብ በማቅረብ ላይ ይገኛሉ። እነዚህ ሚዲያዎች የፈጠሩት ማህበር የሳተላይት ወጪውን መሸፈን እንዲያስችለው ይህን የጎፈንድሚ ፔጅ ከፍተናል → እዚህ ሊንክ ላይ ይጫኑ። ለትብብርዎ እናመሰግናለን።

ታሪክ ትምህርት ቤት እንጂ እስር ቤት መሆን የለበትም
****
የኢትዮጵያ ሳይንስ አካዳሚ ወርሐዊ የሕዝብ የውይይት መድረክ ዝግጅቱን በሁለቱ የአዲስ አበባ ጉምቱ ምሁራን በፕሮፌሰር ባሕሩ ዘውዴ ‘የኢትዮጵያ ታሪክ አጻጻፍ ዕድገትና ተግዳሮት’ በሚል ርዕስ አቅራቢነትና በፕሮፌሰር ሽፈራው በቀለ የመድረክ መሪነት አካሂዷል። ውይይቱ በጣም አስተማሪና ጥሩ ጥሩ ጥያቄዎች የቀረቡብት ነበር። የተነሱ ዋና ዋና ሐሳቦችን ጨመቅ አድርጌ ከዚህ እንደሚከተለው አቀርባለሁ።

ታሪክ ሁለት መሠረታዊ ገጽታዎች አሉት ሲሉ ነበር ንግግራቸውን የጀመሩት። አንዱ ታሪክን ባንዴ ሁሉንም ማወቅ ስለማይቻል፣ በጊዜ ሂደት እንደሚያድግና ሊቀየር የሚችልበት ዕድል መኖሩ እና ታማኝና ሊረጋገጥ የሚችል በጊዜው የነበሩ ቀዳማዊ ምንጭ (primary source) እና ሁለተኛ ምንጭ (secondary source) የሚጠቀም መሆኑ ነው ብለዋል። ከዚህ ጋር በተያያዘ የማንኛውም መረጃ ታማኝነትና ትክክለኝነት በሳይንሳዊ መንገድ መረጋገጥ ይኖርበታልም ብለዋል። ይህን ሲያብራሩም ስለ ያ ትውልድ መጻፋቸውንና በውስጡም የነበርኩበት ስለነበር ሚዛናዊ መሆኔን የሚገመግመው አንባቢ ነው ብለዋል።

ኢትዮጵያን በተመለከት ይህን ሲያብራሩ፣ ሥነ ጽሑፍ ቅርስ ነው። ኢትዮጵያም የዚህ ቅርስ ባለቤት፤ ይህ የመዛግብት ቅርስ ግን በተለያየ ጊዜና ቦታ በዩዲት ጉዲት፣ በግራኝ ሞሐመድ፣ በእንግሊዝ፣ በጣልያን፣ በደርግ እንዲሁም በኢሕአዴግ ተሰርቋል፣ ተቃጥሏል ወይም የት እንደደረሰ አይታውቅም ብለዋል። መዛግብቶች ሁሉ ከ25 ዓመታት በኋላ ወደ አብያተ መዘክር መግባት ቢኖርባቸውም ይህ እየተደረገ አይደለም ብለዋል። ይህ በዚህ እንዳለ፣ በፊት የመዛግብት ችግር ስለነበረብን ለታሪክ ምርምር የግዴታ ወደ ውጭ መሄድ አስፈላጊ የነበረ ቢሆንም አሁን ግን እነዚሁን መዛግብት በማይክሮ ፊልም ወደ የኢትዮጵያ ጥናትና ምርምር ተቋም በማምጣት ተማሪዎቻችን እዚሁ ምርምራቸውን እንዲሰሩ ማድረግ ተችሏል ብለዋል።

የዘመናዊ ታሪክ አጻጻፍ የተጀመረው በጀርመን ሀገር መሆኑንና ይህም ተመሳክሮ የተገኘን ትክክለኛ መረጃ መጠቀምን፣ የሙያተኛውን ገለልተኝነት፣ ብይንን ከጊዜው ጋር በነበረው ኹነት መሰረት ማድረግን የሚጠይቅ ነው። ነገር ግን የሚጠናው በዋነኝነት የፖለቲካ ታሪክ ብቻ በመሆኑ ችግር ነበረበት። በኋላ ግን የኢኮኖሚና ማኅበራዊ ታሪክን እንዲያካትት ተደርጓል። በብዙ የአፍሪካ ሀገሮች እስከ 20ኛው ክፍለ ዘመን አጋማሽ ድረስ ዘመናዊ ታርክ አልተጻፈም። እንዲያውም የጽሑፍ ባህሉ ስላልነበር፣ ምእራባውያን ጸሐፍት ብዙዎችን አፍሪካውያን ታሪክ የላቸውም እስከ ማለት ደርሰዋል። ነገር ግን ታሪክ የጽሑፍ ብቻ ሳይሆን አፈ-ታሪክም በሳይንሳዊ መንገድና ገለልተኝነትን ጠብቆ እስከተሰራና በሌሎችም እስተረጋገጠ ድረስ ታሪክ ነው ነበር ያሉት። ችግሩ በጠባብ ብሔርተኞችና በፖለቲከኞች ጣልቃ ገብነት ትርክት ሆነው ለፖለቲካ ፍጆታ ሲውል ነው ብለዋል።

ለምሳሌ የአርሲ የአኖሌና አዞሌ ታርክ የተጻፈበት ሁኔታ የዚሁ ውጤት ነው። አሁን ደግሞ አዲስ አበባን ፊንፊኔ ማለት ተጀምሯል፤ ሁለቱ ይለያያሉ። አዲስ አበባ ከመቶ አመት በላይ በብዙ ኢትዮጵያዊያን የተሠራች ትልቅ ከተማ ስትሆን ፊንፊኔ ደግሞ የፍልውሃ ሰፈር ነች። ስለዚህ ሁለቱን ማመሳሰል ስህተት ነው ብለዋል። ከዚሁ ጋር አገናኝተውም ስለታሪክ ሞጁውሉ ደካማነትና የሚሻሻልበት መንገድ እንዳለ፣ እርሳቸውን ጨምሮ ሌሎችም ያላቸውን መዛግብት እንደሰጡና ሰዎች እየሰሩበት ነው ብለዋል።

ታሪክ በታርክ ሙያተኞች (professional historiography) በአካዳሚዎች ውስጥ ባሉ ሙያተኞች ወይም ሕዝባዊ (popular historiography) በኛው ሀገር እንደ ተክለጻዲቅ ሞኩሪያና ዘውዴ ረታ ዓይነቶች ሊጻፍ ይችላል። የመጀመሪያዎቹ ሳይንሳዊ መንገድን ተከትለው መሥራት ሲኖርባቸው፣ ሁለተኛዎቹ ግን በዚህ አይገደዱም፤ እንዲያውም የቋንቋ አጠቃቀማቸው ድራማ ሊበዛው ይችላል። ስለዚህም በሙያተኞች የሚጻፈው የበለጠ ተቀባይነት ይኖረዋል። ትዝታዎች በራሳቸው ታሪክ ባይሆኑም የታሪክ ግባት ሆነው ግን ያገለግላሉ። ከዚህ ጋር በተገናኘ፣ የደርጎቹ ባለስልጣናት እድሜ አግኝተው ጽፈውልን ስናይና አክሊሉ ሀብተወልድ እስር ቤት እያለ የጻፈውን እያየን ሁሉም የኀይለ ሥላሴ ባለሥልጣናት በሕይወት ቆይተው ጽፈውልን ቢሆን ሲሉ ቁጭታቸውን ተናግረዋል።

በኢትዮጵያ ደረጃ፣ የጽሑፍ ባህሉ ለዘመናት በመኖሩ ምክንታት የታሪክ ምንጭ አለ። በተለይም ለሰሜኑ የሀገራችን ክፍል። ብዙ ምዕራባውያን በኢትዮጵያውያን እርዳታ ጭምር ታሪካችንን ጽፈዋል። ከ19ኛው ክፍለ ዘመን መጨረሻ ጀምሮ ታሪካዊ ሂሶችና ታሪክም በተለያዩ ኢትዮጵያውያን ጸሐፍት መጻፍ ተጀምሯል ብለዋል። አካዳሚያዊ የሆነውና ዘመናዊ የኢትዮጵያ ታሪክ ግን የ60 ዓመታት ወጣት ነው ነበር ያሉት። ለዚህም የአዲስ አበባ የታሪክ ትምህርት ክፍልና የኢትዮጵያ ጥናትና ምርምር ተቋም የራሳቸውን አስተዋጽዖ፣ ብዙ ሙያተኞችን በማስመረቅ፣ ምርምሮችን በመሥራት፣ ዓመታዊ ሴሜናሮችን በማዘጋጀት፣ ከሰሜኑ ወደ ደቡብ ጥናቶች ትኩረት እንዲያደርጉ በማድረግ፣ ከፖለቲካው በተጨማሪ የኢኮኖሚና የማኅበራዊ ታሪክ እንዲካተት በማድረግና ከጥንቱ ወደ ዘመናዊው ታሪክ ትኩረት በማድረግ የተቻላቸውን አበርክተዋልም ሲሉ ጨምረዋል።

ነገር ግን የተሠሩ ሥራዎችን አለማሳተም፣ የጥራት ማሽቆልቆል፣ የታሪክ ባለሙያዎችን ክብር ማውረድ፣ የመንግስት ጣልቃ ገብነትና የሐሰት ትርክት፣ የማይቻለውን ታሪክን ወደ ኋላ ለመከለስ የሚደረግ ሙከራ፣ የምርምር ገንዘብ እጥረት፣ የሂሳዊ ትችቶች ማነስና የሕትመት ጥራት መቀነስ፣ የሀገራዊ ታሪክና የብሔር ብሔረሰቦች ታሪክ አለመመጣጠንና አለመጣጣም፣ ለማኅበራዊ ሳይንስ ትምህርቶች የተሰጠው ያነሰ ትኩረትና 70-30 ፖሊሲ፣ ታሪክ ጽሑፎች የተጻፉበት ቋንቋ እንግሊዝኛ መሆኑና ለዜጋው ተደራሽ አለመሆኑ፣ የጥንቱን ታሪክ ተትቶ በዘመናዊው ታሪክ ላይ ብቻ መረባረቡ፣ የታሪክ ሙያ ማኅበር አለመኖርና የታሪክ ሙያተኞችና ምሁራን ደግሞ ፖለቲከኞችና ጠባብ ብሔርተኞች በማይመለከታቸው ገብተው ታሪክን ሲያቦኩና ሀገርን ችግር ሲከቱ ሂሳቸውን አለማሰማታቸው ግን ችግሮች ተብለዋል። አቅራቢዎቹ ግን መልስ ያልሰጠነው አበላሹ ከፖለቲካው ጋር የተያያዘና ብልሽቱም ብዙ ስለሆነ ለሁሉ መልስ መመለስ ሥራንና የሥራ ጊዜን የሚያውክ ስለሆነ ነው ሲሉ አስተባብለዋል። በተጨማሪም አቅራቢው ፕሮፌሰር መስፍን ወልደማሪያም የታሪክ ሙያተኞችን በእንግሊዝኛ ብቻ ጻፉ በማለት የተቹበት መንገድና የአቶ አንዳርጋቸውን ታሪክን የተረዳበትን መንገድና መሠረት የሌላቸውን ጽሑፎች ሲሉ ተችተዋል።

በማጠቃለያውም ከዚህም ችግር ለመውጣት ሁላችንም የሚያስማማ ታሪክ መኖር አለበት ተብሏል። ታሪክ ተፈጥሯዊ ችግር የለበትም። የችግሩ ምንጭ ታሪክን ለራሳቸው ጥቅም ለማዋል የሚሞክሩ ጠባብ ብሔርተኞችና ፖለቲከኞች ናቸው። ማንም ሀገር ቢሆን በሰላማዊ ሂደት የተፈጠረ እንደሌለ ማመንና ግፉንና በጎውን የጋራችን መሆኑን ማመን፣ ከሱም መማርንም ይጠይቃል። ይህ የሚኖረው ግን ለታሪክ ባለሙያዋችና ለሳይንሳዊ መንገድ እምነትና ክብር ሲኖረን ነው። የፖለቲከኞች ጣልቃ ገብነት መቀነስና የሚያስፈልጉ ግባቶችንም ማገዝ ይኖርባቸዋል። የመጻህፍት በሙያተኞን መገምገም ግዴታ የሚሆንበት መንገድ መፈለግም ይኖርበታል። መደራጀትና መማማርም ያስፈልጋል። በተጨማሪም ሚዲያዎች የማስተማር ኀላፊነታቸውን እንዲወጡ መሥራት ይጠይቃልም ብለዋል።

(መላኩ አዳል- The Black Lion – ጥቁር አንበሳ )