" /> በሀዋሳ ዩኒቨርስቲ ህይወት ያጠፋው ተማሪ በቁጥጥር ሥር ዋለ | Mereja.com - Ethiopian Amharic News

በሀዋሳ ዩኒቨርስቲ ህይወት ያጠፋው ተማሪ በቁጥጥር ሥር ዋለ

ድርጊቱ በቀን 30/4/2012 ዓ.ም ምሽት 4 ሰዓት አካባቢ የተፈፀመ መሆኑን የገለፁት ኮለኔል ሮዳሞ ኪአ በሀዋሳ ከተማ አስተዳደር የሰላምና ፀጥታ አስተዳደር መምሪያ ኃላፊ ናቸው፡፡

በሀዋሳ ዩኒቭርስቲ ተማሪ በሆኑ ሁለት ግለሰቦች መካከል በግል ፀብ በተፈጠረው በዚህ ግጭት የአንደኛ ዓመት የተፈጥሮ ሳይንስ ተማሪ የሆነው ግለሰብ ህይወት በስለት ተወግቶ ማለፉን ኃላፊው ገልፀዋል፡፡

ግጭቱ በተፈጠረ ሰዓት በአካባቢው የነበሩ የህብረተሰብ ክፍሎች ለፖሊስ ባደረጉት ጥሪ መሰረት የከተማው ፖሊስ በፍጥነት ደርሶ ጉዳት የደረሰበት ተማሪ በዩኒቨርስቲው ባለ ክሊኒክ የህክምና እርዳታ እንዲያገኝ ያደረገ ቢሆንም ተጎጂው ሪፈር ተፅፎለት ወደ ሪፈራል ሆስፒታል ተልኮ የህክምና እርዳታ እያገኘ ባለበት ህይወቱ ማለፉን ጨምረው ገልፀዋል፡፡

ድርጊቱን የፈፀመው ግለሰብ እና በድርጊቱ የተሳተፉ አካላት በፖሊስ በቁጥጥር ሥር ውለው በተደረገው ምርመራ እና ማጣራት ወንጀሉ የተፈፀመው በሟች እና በገዳዩ መካከል በነበረ የቆየ ግጭት ምክንያት በተያዘ ቂም መሆኑን የገለፁት ኮለኔል ሮዳሞ ናቸው፡፡

በዚህ ድርጊት ባልተጠበቀ ሁኔታ የተማሪው ህይወት ከጠፋ በኋላ በሀዋሳ ዩኒቨርስቲ ዋናው ግቢ ጥዋት ላይ ብቻ የመማር ማስተማር ሂደቱ መጠነኛ መስተጓጎል እንደገጠመው የገለፁት ኮለኔል ሮዳሞ በአሁን ሰዓት በሀዋሳ ዩኒቨርስቲ በሁሉም ካፓስ የመማር ማስተማር ስራው በሰላማዊ መንገድ የቀጠለ መሆኑን ነው የገለፁት፡፡

በአሁን ሰዓት ከሁሉም የፀጥታ ሀይል የተውጣጣ ኮማንድ ፖስት በሁሉም ካምፓሶች የተቋቋመ መሆኑን የገለፁት ኮለኔል ሮዳሞ አስተማማኝ የፀጥታ ሁኔታ መኖሩን ጨምረው ገልፀዋል፡፡

ምንም እንኳን ግጭቱ በግል ቂም በተፈጠረ ፀብ የተፈፀመ መሆኑ በምርመራ የተረጋገጠ ቢሆንም በማህበራዊ ሚዲያዎች የሁለቱን ተማሪዎች ግጭት የብሔር ካባ በማልበስ የሀሰት መረጃ የሚያሰራጩ አካላት መኖራቸውን ኃላፊው ገልፀው እነዚህ ኃላፊነት የጎደላቸው በጥቅም የታወሩ አካላት የሚያሰራጩት የሀሰት መረጃ ከእውነት የራቀ ሚዛናዊነት የጎደለው መሆኑን መላው ህብረተሰብ ሊገነዘበው እንደሚገባም አሳስበዋል፡፡

በዚህ ባልተጠበቀ አጋጣሚ በጠፋው የተማሪ ህይወት የተሰማቸውን ጥልቅ ሀዘን የገለፁት ኮለኔል ሮዳሞ ኪአ በከተማ አስተዳደሩ ስም ለሟች ቤተሰቦች፣ ዘመድ አዝማድና ወዳጆች መፅናናትን ተመኝተዋል፡፡

(ምንጭ:-የሀዋሳ ከተማ አስተዳደር ኮምኒኬሽን ቢሮ)


የመረጃ ቲቪ አባል ይሁኑ - JOIN US