ግጭቶችን ለማርገብ ተነሳሽነት ወስደው ባልሰሩ የዩንቨርሲቲ ፕሬዘዳንትና ምክትል ፕሬዘዳንቶች ላይ የሚወሰዱት እርምጃዎች ይቀጥላል ተባለ፡፡


መረጃ ቲቪ አባል በመሆን የሳተላይት ቲቪውን ቀጥታ ስርጭት፣ ወቅታዊ ዜናዎችን እና ትንተናዎችን፣ የመዝናኛ ፕሮግራሞችን፣ ስፖርት እና ሌሎችንም ዝግጅቶቻችንን በፍጥነት እና ጥራት ስልክዎ፣ ኮምፒዩተርዎ ወይም ቲቪዎ ላይ ማየት ይችላሉ። እዚህ ሊንክ ላይ በመጫን አባል ይሁኑ


ከዩንቨርሲቲ ፕሬዘዳንቶች ጀምሮ በግጭት በተሳተፉ ተማሪዎችና ሰራተኞች ላይ የሚወሰዱት እርምጃዎች እንደሚቀጥሉ የሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስቴር አስታወቀ፡፡

ሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስቴር ለኢትዬ ኤፍ ኤም እንዳስታወቀው በዩኒቨርሲቲዎች ሰላማዊ የመማር ማስተማር ስራ እንዳይኖር ተሳትፎ ባደረጉ ተማሪዎችና ሰራተኞች ላይ ዩኒቨርሲቲዎች የሚወስዱት አስተዳደራዊ እርምጃ ተጠናክሮ ይቀጥላል፡፡

በርካታ ዩኒቨርሲቲዎች በተማሪዎች ላይ እርምጃ እየወሰዱ ሲሆን ፤ግጭቶችን ለማርገብ ተነሳሽነት ወስደው ባልሰሩ ፕሬዘዳንትና ምክትል ፕሬዘዳንቶች እንዲሁም ተሳትፎ የነበራቸው ሰራተኞች እየተለዩ እርምጃ እየተወሰደባቸው መሆኑን ነው የሚኒስቴሩ የህዝብ ግንኙነት ሃላፊ አቶ ደቻሳ ጉርሙ የነገሩን፡፡

ሚኒስቴሩ ባለፈው ሳምንት በሰጠው መግለጫ በአማራና ኦሮሚያ ክልል በሚገኙ ዩኒቨርሲቲዎች ተፈጥሮ በነበረው ግጥት ተሳታፊ ናቸው ተብለው በተጠረጠሩ ከ450 በላይ በሚሆኑ ተማሪዎች ላይ አስተዳደራዊ እርምጃ መወሰዱን መናገሩ ይታወሳል፡፡

ከ170 በላይ ተማሪዎች ከአንድ አመት ቅጣት እስከ መባረር የደረሰ እርምጃ የተወሰደባቸው ሲሆን፤ ከ280 በላይ የሚሆኑት ተማሪዎች ደግሞ የመጨረሻ ማስጠንቀቂያ የተሰጣቸው ናቸው፡፡

ድሬዳዋ ፣ጅማ፣ወሎ እና ሌሎች ዩንቨርሲቲዎች በተማሪዎች፣በአመራሮችና ሌሎች ሰራተኞች ላይ እርምጃ እየወሰዱ ነው ያሉት ሃላፊው በሌሎች ዩንቨርሲቲዎች ግጭት እንዲፈጠር ድጋፍ ያደረጉ፣ግጭት የፈጠሩ እና ሌሎች ሃላፊነታቸውን ባልተወጡ አካላት ላይ እርምጃው ይቀጥላል ብለዋል።

ከተማሪዎች በተጨማሪም ፕሬዘዳንትና ምክትል ፕሪዘዳንቶችን ከቦታቸው ማንሳትን ጨምሮ ሰራተኞችና መምህራንም ቅጣት እየተላለፈባቸው መሆኑን ገልጸዋል፡፡

ኢትዬ ኤፍ ኤም