በምሥራቅ አማራ ኦሮሞ ብሔረሰብ አስተዳደር ያጋጠመውን የበረሃ አንበጣ መቆጣጠር ፈታኝ መሆኑ ተገለጸ፡፡


መረጃ ቲቪ አባል በመሆን የሳተላይት ቲቪውን ቀጥታ ስርጭት፣ ወቅታዊ ዜናዎችን እና ትንተናዎችን፣ የመዝናኛ ፕሮግራሞችን፣ ስፖርት እና ሌሎችንም ዝግጅቶቻችንን በፍጥነት እና ጥራት ስልክዎ፣ ኮምፒዩተርዎ ወይም ቲቪዎ ላይ ማየት ይችላሉ። እዚህ ሊንክ ላይ በመጫን አባል ይሁኑ


በምሥራቅ አማራ የተከሰተውን የአንበጣ መንጋ የመከላከል ጥረቱ ቢቀጥልም ምንጩ ላይ መቆጣጠር አለመቻሉ አደገኛ መሆኑ ተገለጸ፡፡

(አብመድ) በምሥራቅ አማራ ኦሮሞ ብሔረሰብ አስተዳደር፣ ደቡብ ወሎ እና ሰሜን ወሎ ዞን ከዘጠኝ ባላነሱ ወረዳዎች ያጋጠመውን የበረሃ አንበጣ መቆጣጠር ፈታኝ መሆኑን የክልሉ ግብርና ቢሮ አስታወቀ፡፡ የቢሮው ምክትል ኃላፊ ዶክተር ሰሎሞን አሰፋ ለአብመድ እንዳስታወቁት የበረሃ አንበጣው እንደ አዲስ እየተፈለፈለና የዕድገት ደረጃውን እየጨረሰ ከሚነሳበት የአፋርና ሶማሌ ክልሎች አካባቢ የተደራጀ የኬሚካል ርጭት አለመደረጉ የመከላከል ሥራውን ፈታኝ አድርጎታል፡፡

ዛሬ በሰሜን ወሎ ዞን ሀብሩ ወረዳ ከፍተኛ የአንበጣ መንጋ መኖሩን ያስወቁት ዶክተር ሰሎሞን ‹‹ኅብረተሰቡን አነቃንቀን በርችትም ጭምር ተረጋግቶ እንቁላል እንዳይጥል የመረበሽ ሥራ እየሠራን ነው፤ ኅብረተሰቡም በነቂስ ወጥቶ ለመከላከል እየሞከረ ነው፤ አካባቢው በአውሮፕላን ለመርጨት ስለማይመችና ቢመችም አውሮፕኖቹ በብልሽት ስለቆሙ በሰው እና ተሽከርካሪ ታግዘን ለመከላከል እየጣርን ነው›› ብለዋል፡፡

በኦሮሞ ብሔረሰብ አስተዳደር ደዌ ሀረዋ አካባቢ በኩል የገባው የበረሃ አንበጣ በደቡብ ወሎ ዞን አድርጎ የደሴ ወልድያ አስፓልት መንገድን በመከተል ወደ ሰሜን ወሎ መግባቱን ነው ምክትል ቢሮ ኃላፊው ያመለከቱት፡፡
‹‹በተሽከርካሪም በሰው ኃይልም የኬሚካል ርጭት እየተደረገ ነው፤ የወልድያና ደሴ ተማሪዎች፣ ወጣቶችና አቅም ያለው ሁሉ እንዲሁም ማንኛውም ተሽከርካሪ ተሰማርቶ ለመከላል እየሠራ ነው›› ብለዋል፡፡

ባለቤትነታቸው የምሥራቅ አፍሪካ የበረሃ አንበጣ መቆጣጠሪያ የሆኑ ሁለት የኬሚካል መርጫ አውሮፕላኖች እንደነበሩ የገለጹት ዶክተር ሰሎሞን ‹‹አንዱ ኮምቦልቻ ሌላኛው ድሬዳዋ በብልሽት ምክንያት አርፈዋል፤ መለዋወጫ ዛሬ ከኬንያ አዲስ አበባ መግባት ጀምሯል፤ ምናልባት አውሮፕላኖቹ አፋርና ሶማሌ ክልሎች ላይ ከመነሻው ረጭተው ካልተገታ አደገኛ ነው›› ብለዋል፡፡
በተለይ አፋር ክልል ላይ ያለው ከተረጨና ተጨማሪ የአንበጣ መንጋ ካልመጣ ወደ ክልሉ የገባውን መቆጣጠር አስቸጋሪ ሊሆን ቢችልም የማይቻል እንደማይሆን አመልክተዋል፡፡ የአማራ ክልል የአንበጣው የጥቃት ሰለባ እንጅ መፈልፈያ መሆኑን በማልከት፡፡ አፋር ክልል ጭፍራ፣ ተላላክ፣ አድሀር እና የታችኛው ሚሌ ወረዳዎች እና ሶማሌና አፋር አዋሳኝ አካባቢ የአንበጣ መንጋው እየተነሳ እንደሚመጣም ነው ያመለከቱት፡፡

የአንበጣ መንጋው ረዥም ርቀት የሚበር በመሆኑና በነፋስ እየታገዘ ስለሚንቀሳቀስ በሰው ጉልበት ለመቆጣጠር ማስቸገሩንም አስታውቀዋል፡፡ በየጊዜው ክትትል አድርጎ የእድገት ደረጃውን መለዬትና ርጭት የሚስፈልገውንና በምን እንደሚረጭ ማመላከት ላይ በአፋርና ሶማሌ ክልሎችም ችግር እንደሌለ ያስታወቁት ዶክተር ሰሎሞን የአውሮፕኖቹ በየጊዜው መበላሸት የቅድመ ማስጠንቀቂያውን ውጤት አልባ እያደረገው መሆኑን አስረድተዋል፡፡

መረጨት ባለበት ሰዓት አለመረጨቱ ለአንበጣው መጎልመስና መጠንከር ዕድል እየሰጠው መሆኑን ነው የተናገሩት፡፡ የምሥራቅ አፍሪካ የበረሃ አንበጣ መቆጣጠሪያ ሦስት አውሮፕላኖች ቢኖሩትም ሁለቱን አሰማርቶ አንዱን በሌሎች የቀጠናው ሀገራትም ስጋት ስላለ ለመጠባበቂያ ማስቀመጡን መረጃ እንዳላቸው ያመለከቱት ምክትል ቢሮ ኃላፊው ‹‹ወደ ክልላችን የገባው በዋናነት ለአውሮፕላን ርጭት አይመችም፤ ነገር ግን ከመነሻው ላይ ያለው ካልተገታ በየጊዜው አዲስ የአንበጣ መንጋ ስለሚገባ እንቸገራለን›› ብለዋል፡፡ አጠቃላይ ስጋቱን ለመቀነስ የፌዴራል መንግሥት አርና ሶማሌ ክልሎች ላይ የሕይወት ዑደቱን ማቋረጥ እንዳለበት ነው ያስገነዘቡት፡፡

ደቡብ ወሎ ዞን ሦስት፣ ኦሮሞ ብሔረሰብ አስተዳደር ሦስት እና ሰሜን ወሎ ዞን ሦስት ወረዳዎች የበረሃ አንበጣ መንጋው የተከሰተባቸው ናቸው፤ በአነስተኛ ቀበሌ የተነኩ ወረዳዎችም እንዳሉም ነው የተገለጸው፡፡

የበረሃ አንበጣው እንቁላል ሊጥል ስለሚመጣ በየቀበሌው የግብርና ባለሙያዎች፣ ኬሚካል እና መርጫ መሳሪያ መዘጋጀቱን ያመለከተት ዶክተር ሰሎሞን ኅብረተሰቡ ጥቆማ እንዲሰጥ፣ የደረሱትን ሰብሎች እንዲሰበስብ፣ የሚበር ነፍሳትም ስለሆነ ማሳ ላይ መላ ቤተሰቡን በማሳተፍ እንዲከላከል፣ ኬሚካል ለሚረጩት ውኃ በማቅረብ እንዲተባርና እንዲያግዝ አሳስበዋል፡፡