ከ21 አመታት በኋላ ኦብነግ አዲስ ሊቀመንበር ሊመርጥ ነው።


መረጃ ቲቪ አባል በመሆን የሳተላይት ቲቪውን ቀጥታ ስርጭት፣ ወቅታዊ ዜናዎችን እና ትንተናዎችን፣ የመዝናኛ ፕሮግራሞችን፣ ስፖርት እና ሌሎችንም ዝግጅቶቻችንን በፍጥነት እና ጥራት ስልክዎ፣ ኮምፒዩተርዎ ወይም ቲቪዎ ላይ ማየት ይችላሉ። እዚህ ሊንክ ላይ በመጫን አባል ይሁኑ


DW : የኦጋዴን ነጻነት ብሔራዊ ግንባር (ኦብነግ)ድርጅቱን ላለፉት 21 ዓመታት ሲመሩ የቆዩትን አድሚራል መሐመድ ኡመር ኡስማንን በአዲስ መሪ ሊተካ ነው። ድርጅቱ እስካሁን የነበረውን አወቃቀር በመቀየር ምክትል ሊቀመንበርም እንደሚመርጥ ተገልጿል።

ኦብነግ የአዳዲስ አመራሮቹን ምርጫ የሚያካሄደው ነገ ሐሙስ በሶማሌ ክልል ጎዴ ከተማ በሚጀምረው ጠቅላላ ጉባኤው ነው። የፓርቲው የውጭ ጉዳይ ኃላፊ አቶ ሀሰን ሙአሊን ለዶይቼ ቬለ እንደተናገሩት በጉባኤው ፓርቲው የሚከተለው አዲስ የፖለቲካ ፕሮግራም እና ስትራቴጂም ይጸድቃል።

ከዛሬ ጀምሮ ለተከታታይ ስድስት ቀናት ይካሄዳል በተባለው የኦብነግ ጠቅላላ ጉባኤ ላይ ከአስራ አንዱ የሶማሌ ክልል ዞኖች፣ ከኢትዮጵያ የተለያዩ አካባቢዎች እና ከውጭ ሀገራት የተውጣጡ ከ700 እስከ 1000 የሚደርሱ አባላትና ደጋፊዎች እንደሚሳተፉ አቶ ሀሰን ተናግረዋል።

በነገው የመክፈቻ ዝግጅት ላይ ኢዜማ፣ ኦነግ፣ አብን እና ሌሎችም የኢትዮጵያ የተቃዋሚ ፓርቲዎች ተወካዮች እንዲገኙ መጋበዛቸውን ገልጸዋል። ከጠቅላላ ጉባኤው አስቀድሞ ካለፈው ቅዳሜ ጀምሮ መደበኛ ስብሰባውን ሲያካሄድ የቆየው የኦብነግ ማዕከላዊ ኮሚቴ ስብሰባ ዛሬ አብቅቷል።ኦብነግ በያዝነዉ ዓመት ይደረጋል ተብሎ በሚጠበቀዉ ምርጫ እንደሚካፈል ከዚሕ ቀደም አስታዉቋል።