43 ተማሪዎች ሲመረዙ 6ቱ ክፉኛ መጎዳታቸዉ ታውቋል


መረጃ ቲቪ አባል በመሆን የሳተላይት ቲቪውን ቀጥታ ስርጭት፣ ወቅታዊ ዜናዎችን እና ትንተናዎችን፣ የመዝናኛ ፕሮግራሞችን፣ ስፖርት እና ሌሎችንም ዝግጅቶቻችንን በፍጥነት እና ጥራት ስልክዎ፣ ኮምፒዩተርዎ ወይም ቲቪዎ ላይ ማየት ይችላሉ። እዚህ ሊንክ ላይ በመጫን አባል ይሁኑ


DW : በኦሮሚያ ክልል ምዕራብ ወለጋ ዞን በሚገኘው የኢናንጎ ከተማ መሰናዶ ትምህርት ቤት የሚማሩ ተማሪዎች ሳይመረዙ እንዳልቀረ የህክምና ባለሙያዎች አስታወቁ።ሐኪሞች እንደሚሉት ትናንትና ዛሬ የታመሙ 43 ተማሪዎች ሁለት ሆስፒታሎች ገብተዉ እየተካሙ ነዉ።ከሕሙማኑ መካከል 6ቱ ክፉኛ መጎዳታቸዉን አስታዉቀዋል።

የጊምቢ አባ ዱላ አጠቃላይ ሆስፒታል ሜዲካል ዳይሬክተር ዶ/ር ደሳለኝ አበበ እንዳሉት ሕመም የተሰማቸዉ 28 ተማሪዎች ትናንት እና ዛሬ ሆስፒታል ገብተዋል። በጊምቢ ከተማ በሚገኝ ሌላ ሆስፒታል ደግሞ ሌሎች 15 ተማሪዎች ተመሳሳይ ህክምና እየተደረገላቸው መሆኑን መረጃ እንዳላቸውም ዶ/ር ደሳለኝ ለDW ተናግረዋል። ተማሪዎቹ ወደ ጊምቢ አጠቃላይ ሆስፒታል የመጡት ትናንት ሰኞ ጥቅምት 25 ከጠዋቱ አራት ሰዓት ገደማ እንደነበር የተናገሩት ሜዲካል ዳይሬክተሩ በተደረገላቸው «የመጀመሪያ ደረጃ ምርመራ የመመረዝ ምልክት አይተናል» ብለዋል። ህክምናቸውን እየተከታተሉ ከሚገኙት ተማሪዎች ውስጥ ስድስቱ በጠና መታመማቸውንም ዳይሬክተሩ አስረድተዋል።።
«እኛ ሆስፒታል ቀጥታ የመጡ አሉ ። ከጤና ጣቢያም ወደ እኛ ሪፈር የተደረጉ አሉ። ያው እኛጋ ሲደርሱ ግን ስድስቱም ራሳቸውን ስተው ነበር። ሌሎቹ ደግሞ ቅድም የነገርኩህ ምልክቶች ይታዩባቸው ነበር። እዚህ ከደረሱ በኋላ ምናልባት ምንጩ ባይታወቅም መርዛማ ነገር ወይም ኬሚካል ነገር ሊሆን ይችላል በሚል ጥርጣሬ ነው ያከምናቸው ። »
በጠና ከታመሙት ተማሪዎች ውስጥ ሁለቱን በዛሬው ዕለት ወደ ነቀምቴ ሪፈራል ሆስፒታል ለተሻለ ህክምና መላካቸውንም ዶ/ር ደሳለኝ አክለው ተናግረዋል።
«የታካሚዎች ቁጥር 28 ደርሷል። አብዛኞቹ ተሽሏቸዋል። ሁለት ሰዎች ደግሞ ወደ ነቀምቴ ሆስፒታል ሪፈር ተደርገዋል። ዛሬ ወደ አዲስ አበባ ናሙና ተልኳል። የንጥረ ነገሩን ምንነት ለማወቅ ነው። እሱ ገና ይደርሳል ይህ ነው ለማለት ውጤት እየጠበቅን ነው።»
ተማሪዎቹን ለመመረዝ አጋልጧል የተባለ ዱቄት መሰል ንጥረ ነገር በመማሪያ ክፍላቸው ውስጥ እንደተገኘ መስማታቸውንም ዶ/ር ደሳለኝ አስረድተዋል።

በኢናንጎ መሰናዶ ትምህርት ቤት የ12ኛ ዲ ክፍል ተማሪ የሆነችው ብርትኳን አስፋው እንዳለችው ደግሞ በወቅቱ በትምህርት ቤቱ ከሚገኙ አራት ብሎኮች በአንደኛው ብሎክ የሚገኙ አራት የመማሪያ ክፍሎች ምንነቱ ባልታወቀ ባዕድ ነገር ተበክለዉ ነበር። ተማሪዎቹ የተለያየ የህመም ስሜት ሲሰማቸው የሚማሩበትን ክፍል በመተው ወደ ሌላ ክፍል ቀይረው ለመማር ያደረጉት ጥረት ሌሎች ተጨማሪ ተማሪዎች ለብክለት እንዲጋለጡ ምክንያት መሆኑን ህክምናዋን ከምትከታተልበት ጊምቢ አባዱላ አጠቃላይ ሆስፒታል ለዶይቸ ቨለ ተናግራለች።
«ትምህርት ቤቱ በአራት ብሎኮች የተከፋፈለ ነው ። አንደኛው ብሎክ ሙሉ በሙሉ የተበከለነበር። በአራቱም የመማሪያ ክፍል ውስጥ የነበሩ ተማሪዎች በተፈጠረው እንግዳ ነገር ተረብሸን ክፍል ቀይረን ለመማር ሞክረን ነበር። በዚህ ምክንያት ግን ከአንደኛችን ወደ ሌላኛችን ሊተላለፍ ችሏል። ከዚያ በኋላ ወደ ጤና ጣቢያ ወሰዱን ፤ ነገር ግን እዚያ መፍትሄ ሊያገኙልን ስላልቻሉ ልጆች ሁሉ ራሳችንን ሳትን ፤አሁን እንግዲህ በአባ ዱላ ሆስፒታል እየታከምን ነው።»
በትምህርት ቤቱ የ12ኛ ጄ ክፍል የማህበራዊ ሳይንስ ተማሪ የሆነውና በደረሰበት ብክለት ህክምናውን እየተከታተለ የሚገኘው ተማሪ አብረሃም ቡልቲ በበኩሉ በመማሪያ ክፍል ውስጥ የገጠማቸው ባዕድ ነገር የዕጽዋት ተክል ብናኝ ይሆናል ብለው በማቅለላቸው ለብክለት እንዳጋለጣቸው ገልጿል።
«እኔ የ12ኛ ክፍል የሶሻል ተማሪ ነኝ ። እኔ ልክ የመጀመሪያውን የትምህርት ክፍለ ጊዜ ክፍል ስገባ ሰውነቴን እንደማሳከክ አደረገኝ። እንደማዞርም አድርጎ ጣለኝ። ከዚያ በኋላ መማርም አልቻልንም ልጆች ሰውነታችን ላይ ውሃ ጨመሩልን ፤ የዕጽዋት ቅጠል ነው ጠረጴዛው ላይ የተፈገፈገው ብለው አቅልለውት ነበር። »
ተማሪዎቹ ሳይመረዙ አልቀረም የተባለበትን የምዕራብ ወለጋን ጨምሮ በምዕራብ ኦሮሚያ የሚገኙ አራቱም የወለጋ ዞኖች በአካባቢው ተፈጥሯል በተባለው የጸጥታ ስጋት ምክንያት በኮማንድ ፖስት (በጦር ዕዝ) መተዳደር ከጀመሩ ወራት ተቆጥሯል።