ኅብረተሰቡን በብሔር፣ በሃይማኖትና በአካባቢ በመከፋፈልና በማጋጨት በንፁኃን እሳት የመሞቅ ፍላጎት አለ


መረጃ ቲቪ አባል በመሆን የሳተላይት ቲቪውን ቀጥታ ስርጭት፣ ወቅታዊ ዜናዎችን እና ትንተናዎችን፣ የመዝናኛ ፕሮግራሞችን፣ ስፖርት እና ሌሎችንም ዝግጅቶቻችንን በፍጥነት እና ጥራት ስልክዎ፣ ኮምፒዩተርዎ ወይም ቲቪዎ ላይ ማየት ይችላሉ። እዚህ ሊንክ ላይ በመጫን አባል ይሁኑ


አድማሳቸው እየሰፋ ያለ ጥቃቶችና አሳሳቢነታቸው

የኢትዮጵያ ሕዝቦች አብዮታዊ ዴሞክራሲያዊ ግንባር (ኢሕአዴግ) ከአራት ዓመታት በፊት በጊንጪ ከተማ ከተጀመረውና መላ አገሪቱን ካጥለቀለቀው ሕዝባዊ ተቃውሞና አመፅ አንዴ በጥልቅ መታደስ፣ አንዴ ሕግና ሥርዓት የማስከበርና ሙሰኞችን ወደ ፍትሕ የማቅረብ ዘመቻ እያደረግኩ ነው ሲል ቆይቶ በመጋቢት ወር 2010 ዓ.ም. የግንባሩን ሊቀመንበር በመቀየር የአገሪቱንም ጠቅላይ ሚኒስትር እንዲተኩ በማድረግ፣ መፍትሔ ማበጀቱን ራሱም ሆኑ በርካቶች ሲናገሩ ቆይተዋል፡፡ እነሆ ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) ሥልጣን ከያዙና በተለያዩ ምክንያቶች ስማቸው ሲጠራና ሲወቀሱ የነበሩ ከፍተኛ የአገሪቱ ባለሥልጣናትና የተለያዩ ተቋማት ኃላፊዎች ዘወር ከተደረጉ ዓመት ከመንፈቅ ቢሆንም፣ አገሪቱ በየወቅቱ ከግጭት ወደ ግጭት፣ ከብጥብጥ ወደ ብጥብቅ የሚያስገባት አዙሪትና አባዜ ሊለቃት አልቻለም፡፡

እስከ ዛሬ በታዩ ሁከቶች የብሔርና የሃይማኖት ገጽታ ያላቸው ግጭቶች በርካቶችን በማሳዘን የሰው ሕይወት ሲቀጥፉ፣ አካል ሲያጎድሉ፣ አብሮ የመኖርና እሴቶችን ሲንዱ፣ ንብረት ሲያወድሙና በርካቶችን ሲያፈናቅሉ ተስተውለዋል፡፡ ለእነዚህ ችግሮች መንግሥት የሰጠው ምላሽ እምብዛም በመሆኑ፣ ከአንዱ ግጭት በኋላ ሌላ ግጭት እንዳይከሰት የማድረግ አቅሙ እዚህ ግባ የሚባል እንዳልሆነ በተደጋጋሚ ሲተች ነበር፡፡ በዚህ ሳቢያም ማብቂያው ቅርብ የማይመስል ቀውስ በየቦታው በረደ ሲባል እንደገና  እየተነሳ፣ እዚህ አበቃ ሲባል እዚያ እያበበ ሰዎች ከቦታ ቦታ ለመንቀሳቀስና ለመሥራት ቀርቶ ባሉበት ለመርጋትም የማያስችሉ ክስተቶች እየተስተዋሉ ነው፡፡

ከእነዚህ የበርካቶችን ሕይወት እንደ ዘበት እየቀጠፉና አካላዊና ሥነ ልቦናዊ ጉዳት አስከትለው ከሚያልፉ ግጭቶች፣ የሰሞኑ የ78 ሰዎችን ሕይወት ከመንገድ ያስቀረው ተጠቃሽ ነው፡፡ ጥቅምት 11 ቀን 2012 ዓ.ም. በግምት ከሌሊቱ በስድስት ሰዓት በመንግሥት የተመደቡላቸው ጠባቂዎች አጠራጣሪ በሆነ መንገድ ሊነሱበት እንደሆነ በመጥቀስ ለደጋፊዎቹና ለተከታዮቹ ዕወቁልኝ ያለው የኦሮሞ ሚዲያ ኔትወርክ (ኦኤምኤን) መሥራችና ሥራ አስኪያጅ፣ እንዲሁም የማኅበራዊ ትስስር ገጽ አንቀሳቃሽ አቶ ጃዋር መሐመድ መልዕክት ሳቢያ በየአካባቢው ድርጊቱን ተቃውመው በርካታ ወጣቶች ወደ አደባባይ ወጥተዋል፡፡

ከእነዚህ መካከልም ለአቶ ጃዋር ከለላ ለመስጠት በእሱ የመኖሪያ አካባቢ ተሰባስበው እንደነበር የሚታወስ ሲሆን፣ በነጋታው ረቡዕ ጥቅምት 12 እና ሐሙስ ጥቅምት 13 ቀን 2012 ዓ.ም. የነበሩ የተለያዩ የተቃውሞ መንፈስ ያላቸው ሠልፎች ወደ ብጥብጥ፣ ግጭትና ጥቃቶች ለመቀየር ጊዜ አልፈጀባቸውም፡፡  ቀጥሎ የተከተሉት ሕዝብን ሥጋት ውስጥ የሚጥሉና የብዙዎችን ሕይወት የቀጠፉ ጥቃቶች ናቸው፡፡ በዚህም ምክንያት በርካቶች ተጎድተዋል፡፡

ይኼንን ችግር አስመልክቶ ሐሙስ ጥቅምት 20 ቀን 2012 ዓ.ም. የሰጡት የጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት ፕሬስ ሴክሬታርያት ኃላፊ አቶ ንጉሡ ጥላሁን፣ ባለፈው አንድ ዓመት ከመንፈቅ የለውጥ ጊዜ ውስጥ መፈናቀልና በማንነት የሚደርሱ ጥፋቶች እንዳልቆሙ በመጥቀስ መነሻዎችን መገምገም ያስፈልጋል ሲሉ አሳስበዋል፡፡ ከቀውስ ማግሥት የተሰጠ መግለጫ ስለነበር በርካቶች ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) ራሳቸው ቀርበው ይሰጣሉ ተብሎ የተጠበቀ ቢሆንም፣ በፕሬስ ሴክሬታሪያት ኃላፊው በተሰጠው መግለጫ መንግሥት በደረሱ ጉዳቶች እጅግ ማዘኑ ተገልጿል፡፡ ችግሩን ለማለፍም የሚቻለው በኢትዮጵያውያን ተሳትፎና የችግሩን ምንጭ ማወቅ ሲቻል እንደሆነ አቶ ንጉሡ ተናግረዋል፡፡ እንደ አቶ ንጉሡ ገለጻ፣ መንግሥት ትዕግሥትና ሆደ ሰፊነትን ሲያሳይ እንደ ደካማነት እየተወሰደ እንዳለና በሕግ ሳይሆን ባጫካ ሕግ የመተዳደር ፍላጎቶች እየጎሉ በመምጣታቸው፣ የመንግሥትን ትዕግሥት እየተፈታተኑ ይገኛሉ፡፡

አቶ ንጉሡ እንደሚሉት፣ ግጭቶቹ የሚከሰቱት በሁለት ምክንያቶች ነው፡፡ የመጀመርያው መንግሥት ደካማ ነው የሚል መልዕክት በማስተላለፍ መንግሥት ትዕግሥቱ እንዲያልቅ ከመፈለግ የመነጨ ነው ይላሉ፡፡ ሁለተኛው ደግሞ መንግሥት ሕግና ሥርዓትን ለማስከበር ኃይል ሲጠቀም ለውጥ የለም፣ መንግሥት የቀድሞ የመግደልና የማሰር ባህሉን ቀጥሎበታል ማለት ስለተፈለገ ነው በማለት ያብራራሉ፡፡

‹‹ኅብረተሰቡን በብሔር፣ በሃይማኖትና በአካባቢ በመከፋፈልና በማጋጨት በንፁኃን እሳት የመሞቅ ፍላጎት አለ፡፡ ይኼ ደግሞ መንግሥትን በእጅጉ ትዕግሥቱን እየተፈታተነ የመጣ ነው፤›› ሲሉም፣ አቶ ንጉሡ በመግለጫቸው አምርረው ተናግረዋል፡፡

በተጨማሪም የኢሕአዴግ ውህደት ሌላ ትርጉም በመስጠት አሃዳዊ ሥርዓት ለማምጣትና የብሔረሰቦች መብት ማፈኛ ሒደት አድርገው በማቅረብ ለግጭት ማቀጣጣያ የሚያውሉ መኖራቸውን በመግለጽ፣ ውህደቱ ይኼንን እንደማያስከትልና የየትኛውንም ወገን የበላይነት ለመሸከም የሚችል ትከሻ አለመኖሩን በማውሳት ተከራክረዋል፡፡

አቶ ንጉሡ ለግጭቶች መንስዔ ናቸው ያሏቸውን ጉዳዮች እንዲህ ተንትነው ቢያስቀምጡም፣ በርካቶች የሚያነሱት አንድ መከራሪያ መንግሥትን ወደ ለውጥ ያስገቡት ጥያቄዎች ወደ ጎን ተደርገው የጠቅላይ ሚኒስትሩን ህልም ለመኖር ሲባል የሕዝቡን ጥያቄ የማይመልሱ ጉዳዮች ላይ በርካታ ጊዜና ገንዘብ ሲወጣ ይታያል የሚል ነው፡፡ ከእነዚህ አንዱ በተለይ በኦሮሞ ልሂቃን የሚቀርበው ጉዳይ የቤተ መንግሥቱ ዕድሳት ሲሆን፣ ያለ ጊዜው ከአምስት ቢሊዮን ብር በላይ ገንዘብ ወጥቶበት የተገነባው ፓርክ የትኛውን ጥያቄ ነው የሚመልሰው ሲሉ ይጠይቃሉ፡፡ ከዚህ በተጨማሪም በውይይትና በተሳትፎ ይቀየርልን ያልተባለን ርዕዮተ ዓለም ለመቀየር፣ እጅግ ሰፊ ጊዜና በጀት ተመድቦ የተዘጋጀን ‹‹መደመር›› መጽሐፍ አስተሳሰብ የሚያነሱ አሉ፡፡

በሌላ ወገን መንግሥት አቅም ቢኖረኝም እየታገስኩ ነው እንጂ ችግሩ እየሰፋና በየጊዜው እየተከሰተ ያለው ቢልም ዕውን መንግሥት አቅም አለው በማለት የሚጠይቁ እየተበራከቱ ነው፡፡ በየሥፍራው ለግጭት የሚያመቹ ሁኔታዎች ሲከሰቱ እየታየና ከየአካባቢው ለግጭት ተልዕኮ በቡድን እንቅስቃሴዎች እየተደረጉ ምልክቶችን ዓይቶና ተንትኖ መከላከል የሚያስችል የደኅንነት ጥንካሬ በሌለበት ሁኔታ፣ እንዲሁም ግጭቶች ሲከሰቱም ምክንያቶቻቸውን ከመተንተን ይልቅ በአፋጣኝ ለማስቆም የሚችል የፀጥታ መዋቅር በሌለበት የመንግሥት አቅም ምንድነው ሲሉ አስተያየት ሰጪዎች ጥያቄ ያነሳሉ፡፡ መንግሥት እየታገሰ ሳይሆን ቁርጠኝነት እንደሚያንሰውና አድልኦ እንደሚታይበት ይናገራሉ፡፡

ከሰሞኑ ግጭትና ጥቃት ጋር በተያያዘ መግለጫ ያወጣው የኢትዮጵያውያን ሀገር አቀፍ ንቅናቄ (ኢሀን) ያወጣው መግለጫም ይኼንን ያሰምርበታል፡፡ በኦሮሚያ፣ በሐረርና በድሬዳዋ የተከሰቱት አሰቃቂና ማንነት ላይ ያነጣጠሩ ጉዳቶች ዘግናኝ ናቸው ያለው ኢሀን፣ ‹‹እንዲህ ዓይነቱ አሳፋሪና አሰቃቂ ተግባር በተደጋጋሚ ሲፈጠር የዜጎችን ደኅነነት መጠበቅ ዋና ተግባሩ የሆነው መንግሥት ድርጊቱ በሚፈጸምበት ወቅትም በፍጥነት በማስቆምና በመከላከል፣ እንዲሁም ድርጊቱን የፈጸሙ ወንጀለኞችን ለፍርድ በማቅረብ በኩል የሚያሳየው ቸልተኝነትና ዳተኝነት በኢትዮጵያ መንግሥት አለ ለማለት ፈጽሞ አያስችልም፤›› በማለት የሰላ ሒስ አቅርቧል፡፡

‹‹ይኼ አካሄድ በፍጥነት ካልታረመ የነገሮችን ቅደም ተከተልና ውስብስብነት የተመለከተና ቀጥሎ ሊመጣ የሚችለውን ነገር ማንም ጤነኛ አዕምሮ ያለው ሰው የሚገነዘበው፣ የአገር መፍረስና የእርስ በርስ ጦርነት ነው፡፡ እጅግ በጣም የሚገርመውና የሚያሳዝነው ደግሞ ይኼ ሁሉ አሰቃቂ ግፍ የሚፈጸመው የደረሰውን ጥፋትና ሊያመጣብን የሚችለውን አደጋ መቀልበስ የሚችል የመከለካያና የደኅንነት ኃይል እያለ መሆኑ ነው፡፡ ወደ አገር መፍረስ እየተንደረደረን የምንገኘውና የዜጎች መጨፍጨፍ በተጠናከረ ሁኔታ የቀጠለው፣ በአስፈጻሚ አካላት በኩል በተፈጠረ የቁርጠኝነት ማጣት፣ አድልኦና ራስ ወዳድነት ምክንያት ነው፤›› ብሏል፡፡

ስለዚህም የዜጎችን ደኅንነትና የአገርን ህልውና ለመታደግ፣ እንዲሁም ዴሞክራሲን ዕውን ለማድረግ ‹‹ሁሉን አቀፍ የሽግግር መንግሥት ማቋቋም የባለድርሻ አካላት ተቀዳሚና ብቸኛ ተግባር መሆን አለበት፤›› ሲል ኢሀን አስታውቋል፡፡

ከዚሁ ጉዳይ ጋር ተያይዞ ጥቅምት 18 ቀን 2012 ዓ.ም. መግለጫ ያወጣው የኢትዮጵያ ዜጎች ለማኅበራዊ ፍትሕ ፓርቲ (ኢዜማ)፣ ‹‹ለዜጎች ሞት ደንታ የሌላቸውና በግጭት የሚነግዱ የማኅበራዊ ድረ ገጽና የተለያዩ የብዙኃን መገናኛዎች ሕዝባችንን በሌላ ተከታታይ ግጭቶች ከመዳረጋቸው በፊት፣ ሥልጣን በተሰጠው አካል የማስተካከያ ዕርምጃ እንዲወስድ፤›› በማለት ጥሪ ያቀረበ ሲሆን፣ ‹‹እስካሁን ለተፈጸሙ ሕገወጥ ተግባራት መንግሥት አስተማሪ ዕርምጃ ባለመውሰዱ ሕዝብ መንግሥትን ተጠያቂ እያደረገ ይገኛል፡፡ የመንግሥት ኃላፊነቱን አለመወጣቱ ደግሞ ሕዝቡ ተደራጅቶ ራሱን ወደ መካላከልና ደመነፍሳዊ ሁኔታ ይገፋዋል፡፡ ይኼም ማንም አሸናፊ ወደማይሆንበት የእርስ በርስ ዕልቂተ ይከተናል፡፡ ይኼንን ለመከላከል እንደ ማኅበረሰብ አቀፍ ፖሊስ የመሳሰሉ ሕጋዊ አደረጃጃቶች በአስቸኳይ ማጠናከርና ሥራ ላይ ማዋል ይገባል፤›› በማለት አሳስቧል፡፡

ከእነዚህ የመንግሥት ኅብረተሰቡን ከጥቃት የመከላከልና ደኅንነት የማረጋገጥ ከፍተኛ ትችቶች ጋር በተያያዘ የሚቀርበው ሌላው ትችት፣ መንግሥት ሕጋዊ ዕውቅና የሌላቸውና ከፍተኛ ፖለቲካዊ ተፅዕኖ እያሳደሩ የሚገኝ አካላትን የመቆጣጠርና የመሥራት ፍላጎቱም ሆነ ጥረቱ ምን ያህል እንደሆነ የታየ ምልክት አለመኖሩ ነው፡፡

በተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎች የተለያዩ የማኅበረሰብ ጥያቄዎችን አንግበው የተነሱ በርካታ የማኅበረሰብ ኢመደበኛ አደረጃጀቶች በተለይ አሁን እንደ ፋሽን የበዙ መሆኑን በመግለጽ የሚከራከሩት ተቺዎች፣ መንግሥት የእነዚህን ኃይሎች ማንነት በማወቅና በመረዳት እንዲሁም ሕጋዊ ተቋማት እንዲሆኑ የተቻለውን ድጋፍ ሁሉ ማድረግ አለበት ይላሉ፡፡ ተጠያቂነት ኖሮባቸው አሉታዊ አስተዋጽኦ እንዳያበረክቱ ማድረግ ተገቢ ነው ሲሉም ያሳስባሉ፡፡

ስለእነዚህ ኢመደበኛ አደረጃጀቶች በመግለጫቸው ያኑሰት አቶ ንጉሡ ቀድሞ እነዚህ ቡድኖች የተደራጁት አቃፊ ባልሆነና ኢሰብዓዊ አሠራሮች በሰፈኑበትና እነዚህን አሠራሮች ለመታገል ሲሉ እንደሆነ ገልጸዋል፡፡ የሰው ሕይወት ለማጥፋት፣ ንብረት ለማውደም ወይም ላሌላ ጥፋት ሳይሆን ለፍትሕና ለእኩልነት ሲሉ ነበር የተደራጁት በማለት አብራርተዋል፡፡ ሆኖም አሁን ‹‹የመንግሥትን ሚና ተክተው የመሥራት ሁኔታዎች ይታያሉ፤›› በማለትም የሚና ለውጥ እንዳለ ጠቁመዋል፡፡

ይኼ የሆነበትን ምክንያት ሲያስረዱ መንግሥት አደረጃጀቶቹን በፍጥነት ለፍትሕና ለልማት ሊኖራቸው፣ የሚችለውን ጠቀሜታ ተመልክቶ ለዚሁ ዓላማ ሚና እንዲኖራቸው ማድረግ ሲገባው ይኼንን ሳያደርግ በመቆየቱ አጥፊ እየሆኑ እንደሆነ አምነዋል፡፡ መደራጀታቸው መልካም ቢሆንም ለሐሳብና ለውይይት ቅድሚያ በመስጠት አስተዋጽኦ ማድረግ እንደሚጠበቅባቸውም ጠቁመዋል፡፡

ከእነዚህ ጉዳዮች ባለፈ መንግሥትን የሚያክሩ ባለሙያዎችም ሆኑ ሌሎች አጋዥና እሺ ባዮች እንጂ አይሆንም በማለት የሚከራከሩ አለመሆናቸው፣ የተሰጣቸውን ከማነብነብና ከማስተጋባት በዘለለም ሙግትና ክርክር አድርገው የሐሳብ ፍጭት እንደማያደርጉ በማንሳትም የሚተቹ አሉ፡፡

በተለይም በ‹‹መደመር›› ዕሳቤ ላይ በተደረጉ ውይይቶች ላይ እንደታየው፣ አንብቦ ከመናገርና ይኼ መጽሐፉ ያለው ነው የሚል መልስ ከመስጠት ባለፈ፣ ለጥያቄዎችም ሆነ ለአስተያየቶች የራሳቸውን እሴት የማይጨምሩ አቅራቢዎችና አስተያየት ሰጪዎች፣ በርካታ ሥራዎች እንዴት እንደሚሠሩ ማሳያ ናቸው ሲሉ አስተያየታቸውን የሚሰጡ ጥቂት አይደሉም፡፡ ስለዚህም እንደ መንግሥት ሐሳብ አብላልቶ ውሳኔ ለመስጠት የሚያስችል አቋም እንዳይኖር የሚያደርጉ አሠራሮች፣ መንግሥት ቁርጠኛ ዕርምጃዎችን እንዳይወስድና በሁለት እግሩ መቆም እንዳይችል አድርገውታል በማለትም ይተቻሉ፡፡