ኢሕአዴግ አረጀ፣ ተከፋፈለ፣ ተሸመቀቀና አቅም አጣ እንጂ የመጣ ለውጥ የለም – ይልቃል ጌትነት

በዚህ አስቸጋሪ የፈተና ወቅት የዜጎችን ደኅንነትና የአገር ህልውናን ታድጎ ዴሞክራሲን ዕውን ለማድረግ ሁሉን አቀፍ የሽግግር መንግሥት ማቋቋም የሁሉም ባለድርሻ አካላት ተቀዳሚና ብቸኛ ተግባር መሆን እንዳለበት፣ በአቶ ይልቃል ጌትነት (ኢንጂነር) የሚመራው የኢትዮጵያውያን አገር አቀፍ ንቅናቄ (ኢሀን) ጥሪ አቀረበ፡፡

ፓርቲው የሽግግር መንግሥት መመሥረት አለበት የሚል ጥሪውን ያቀረበው፣ ‹‹ተቀዳሚ መንግሥታዊ ተግባሩን የረሳ አገዛዝን እንደ ሰባት ዓመት ሕፃን የቤት ሥራህን ሥራ እያሉ መጠየቅ፣ ፍፃሜው ራስን እያታለሉ የአገርን ህልውናና የዜጎችን ሕይወት ለአደጋ ማጋለጥ ብቻ ነው፤›› በሚል ርዕስ ዓርብ ጥቅምት 21 ቀን 2012 ዓ.ም. በሰጠው ጋዜጣዊ መግለጫ ወቅት ነው፡፡

የሽግግር መንግሥት ይቋቋም የሚል መደምደሚያ ላይ ያደረሳቸሁ ዋነኛ ምክንያት ምንድነው? ተብሎ ከሪፖርተር ለቀረበላቸው ጥያቄ የፓርቲው ሊቀመንበር አቶ ይልቃል ጌትነት፣ ‹‹የዜጎችን የመኖር መሠረታዊ መብት መንግሥት ማስጠበቅ አልቻለም፡፡ ይህን ካልቻለ ደግሞ መንግሥት አለ ለማለት አይቻልም፡፡ ስለዚህ ሁሉንም ባለድርሻ አካላት ያካተተ የሽግግር መንግሥት መቋቋም አለበት፤›› በማለት ምላሽ ሰጥተዋል፡፡

ከዚህ በተጨማሪም መንግሥት ችግሮች ከመፈጠራቸው በፊት ለመከላከል፣ ከተፈጠሩ በኋላም በፍጥነት ለመቆጣጠርና ለማስቆም፣ ከዚያ በኋላም ወንጀለኞችን ለፍርድ ለማቅረብ ተስኖታል በማለት የሽግግር መንግሥት አስፈላጊና በአስቸኳይ ተፈጻሚ ሊሆን እንደሚገባም ገልጸዋል፡፡

በዚህ ዓመት ይካሄዳል ተብሎ ዕቅድ የተያዘለት ምርጫ ከመካሄዱ በፊትም፣ የሽግግር መንግሥት ምሥረታና የተቋማት ግንባታ ሊቀድም እንደሚገባም ሊቀመንበሩ አስረድተዋል፡፡

ባለፈው አንድ ዓመት ተኩል በአገሪቱ እየተካሄደ ያለውን ፖለቲካዊ ሁኔታ የተቹት ሊቀመንበሩ፣ በዚህ ጊዜ የተከናወነ ለውጥ አለ የሚለውም የተሳሳተ ግንዛቤ እንደሆነ በመግለጽ የሽግግር መንግሥትን አስፈላጊነት አስታውቀዋል፡፡

‹‹ብዙ ሰው ለውጥ አለ የሚል ግንዛቤ ይዟል፡፡ ነገር ግን ኢሕአዴግ አረጀ፣ ተከፋፈለ፣ ተሸመቀቀና አቅም አጣ እንጂ የመጣ ለውጥ የለም፡፡ ስለዚህ አገርን በሚያግባባና በተጠና መንገድ የጋራ ራዕይ ፈጥረን መሠረታዊ የሆኑ የኢትዮጵያ የፖለቲካ ጥያቄዎች ላይ ተወያይተን፣ የጋራ የሽግግር ጊዜ ፍኖተ ካርታ አበጅተንና ተቋማትን ገንብተን ነው ወደ ምርጫ መሄድ ያለብን፤›› ሲሉም አብራርተዋል፡፡

እነዚህን ነገሮች በቅደም ተከተላቸው ማከናወን ካቃተን አሁን በአገሪቱ እየተስተዋሉ ያሉ ችግሮች እንደሚወሳሰቡ፣ እንዲሁም ስፋቱና ጥልቀቱ ጨምሮ ‹‹አገር ወደ መፍረስ አደጋ ሊያደርሰን ይችላል፤›› በማለት ሥጋት አዘል አስተያየታቸውንም አንፀባርቀዋል፡፡

ሕግ ማስከበርን ከፖለቲካ ምኅዳሩ መስፋት ጋር አያይዘው አስተያየት የሚሰጡ የመንግሥት ባለሥልጣናትን የተቹት ሊቀመንበሩ፣ ሕግ የማስከበርና የዴሞክራሲ ምኅዳርን ማስፋት የተለያዩ ነገሮች እንደሆኑ በመግለጽ፣ ‹‹ሰው እየሞተ ምኅዳሩን ለማስፋት ነው የሚል መንግሥት ጤነኛ ነው ማለት ይቻላል?›› ሲሉ ጠይቀዋል፡፡

የአገሪቱን ወቅታዊና ዘላቂ ችግር የሚመጥንና ሁሉም ወገን ከምኞትና ራስን ከማታለል አስተሳሰብ ወጥቶ ችግሩን ፊት ለፊት በመጋፈጥ፣ ለእውነተኛ መፍትሔ አስተዋጽኦ እንዲያደርግ ፓርቲው ጥሪውን አቅርቧል፡፡