ሰማኒያ ለሚጠጉ ሰዎች መገደል ዋነኛ ምክንያቱ ፌስቡክ ነበር ብዬ አምናለሁ


መረጃ ቲቪ አባል በመሆን የሳተላይት ቲቪውን ቀጥታ ስርጭት፣ ወቅታዊ ዜናዎችን እና ትንተናዎችን፣ የመዝናኛ ፕሮግራሞችን፣ ስፖርት እና ሌሎችንም ዝግጅቶቻችንን በፍጥነት እና ጥራት ስልክዎ፣ ኮምፒዩተርዎ ወይም ቲቪዎ ላይ ማየት ይችላሉ። እዚህ ሊንክ ላይ በመጫን አባል ይሁኑ


ኃይሌ ገብረሥላሴBBC Amharic : በፌስቡክ ላይ የተሰራጩ ሐሰተኛ ዜናዎች ከሳምንት በፊት በአገሪቱ ተከስቶ ለ78 ሰዎች ሞት ሰበብ ለሆነው ግጭትና ጥቃት ምክንያት እንደሆነ ኢትዮጵያዊው ስመጥር ሯጭ ኃይሌ ገብረሥላሴ ለቢቢሲ ተናገረ።

ችግሩ የተቀሰቀሰው ከፍተኛ ተጽእኖና ተደማጭነት ያለው የኦሮሞ ሚዲያ ኔትወርክ ዋና ዳይሬክተርና አክቲቪስት ጃዋር መሐመድ የመንግሥት ባለስልጣናት የተመደቡለትን የግል ጠባቂዎቹን በማንሳት ህይወቱን ለአደጋ ለማጋለጥ ሞክረዋል በማለት ያሰራጨውን የማህበራዊ መገናኛ መድረክ መልዕክት ተከትሎ ነው።

መንግሥትና የተለያዩ ወገኖች ለሰዎች ህይወት መጥፋትና ለንብረት ውድመት ምክንያት የሆነው ችግር ሃይማኖታዊና የብሔር ገጽታ እንደነበረው አመልክተዋል።

ማህበራዊ የመገናኛ መድረኮች ለችግሩ መባባስ ምክንያት እንደሆኑ የሚያምነው ኃይሌ ገብረሥላሴ አንዳንድ መልዕክቶችን ከገጹ ላይ እንዲነሱ ካላደረገ ፌስቡክን ሊከስ እንደሚችል ተናግሯል።

ከዚህ አንጻር የትኞቹ የፌስቡክ መልዕክቶች እንዲነሱ እንደሚጠይቅ በግልጽ ባይናገርም፤ አዲስ አበባ ውስጥ ለቢቢሲ “ሐሰተኛ ዜናዎች በቀላሉ መሰራጨት ይችላሉ” ሲል ገልጿል።

ሰማኒያ ለሚጠጉ ሰዎች መገደል ዋነኛ ምክንያቱ “ፌስቡክ ነበር ብዬ አምናለሁ” ሲል የ46 ዓመቱ ኃይሌ የወቀሳ ጣቱን በፌስ ቡክ ላይ ጠቁሟል።

ጃዋር መሐመድ በፌስቡክ ላይ ያሰፈረውን መልዕክት ተከትሎ በተቀሰቀሰው አለመረጋጋት ሳቢያ በኦሮሚያና ሐረሪ ክልሎች እንዲሁም በድሬዳዋ ከተማ አስተዳደር ውስጥ ለቀናት በዘለቀው ሁከት፤ የሞትና የአካል ጉዳት ከደረሰባቸው ሰዎች በተጨማሪ ሌሎች ከቤት ንብረታቸው ሸሽተው በአብያተ ክርስቲያናት ውስጥ ተጠልለው ይገኛሉ።

ከፍተኛ የመንግሥት ባለስልጣናት የጃዋርን ህይወት አደጋ ላይ የሚጥል ነገር እንዲፈጠር አለማድረጋቸውን በመግለጽ፤ ለክስተቱ መፈጠር የጃዋርን ጥበቃ በማንሳት በኩል የተሳተፉ ሰዎች ላይ አስፈላጊውን ምርመራ በማድረግ እርምጃ እንደሚወስዱ ገልጸዋል።

ከተከሰተው ሁከት ጋር የተያያዙ ናቸው በሚል በሰዎች ላይ የሚፈጸሙ ጥቃቶችን የሚያሳዩ አሰቃቂ ፎቶና ቪዲዮዎች በማህበራዊ መገናኛ መድረኮች ላይ ሲታዩ ሰንብተዋል።

ኃይሌ እንደሚያምነው ምስሎቹ የሚያሳዩት በኢትዮጽያዊያን የተፈጸሙ ድርጊቶች አይደሉም ብሎ ነው። “ወገኖቼን አውቃቸዋለሁ፤ እንዲህ አይነት አስቀያሚ ድርጊቶችን አይፈጽሙም” ብሏል።

አለመረጋጋቱ በተከሰተበት ጊዜ አንድ የአካባቢ ባለስልጣን ወጣቶችን አስታጥቃለሁ አለ የተባለበትን ጨምሮ ሌሎች ሐስተኛ ቪዲዮዎች በማህበራዊ መድረኮች ላይ ተሰራጭተው እንደነበር ይታወሳል።

የኖቤል የሰላም ሽልማት አሸናፊው ጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ አህመድ ወደ ስልጣን ከመጡባት እለት አንስቶ ስለአንድነት ባገኙት አጋጣሚ ሁሉ ጥሪ ከማቅረብ ባይቆጠቡም በአገሪቱ የሚታየው የብሔር ውጥረት ከቁጥጥር ውጪ እንዳይወጣ ስጋት አለ።

ከሩጫው ባሻገር ስኬታማ የንግድ ሰው የሆነው ኃይሌ ገብረሥላሴ፤ በሩዋንዳ የተከሰተው የዘር ፍጅት ካጋጠመ ረጅም ጊዜ አለመሆኑን በማስታወስ “ኢትዮጵያ ልትጠነቀቅ ይገባል” በማለት አሳስቧል።

ኃይሌ ጨምሮም ነገሮች ከቁጥጥር ውጪ ከሆኑ በኋላ ምን ሊከሰት እንደሚችል ለማሳየት ሊቢያ፣ ሶሪያና የመን የገቡበትን ችግር እንደ ምሳሌ ጠቅሷል።

በጥቅምት ወር አጋማሽ ካጋጠመው ግጭትና ከተፈጸሙ ጥቃቶች ጋር በተያያዘ የአገሪቱ ባለስልጣናት ከ400 በላይ ሰዎችን በቁጥጥር ስር ማዋላቸው የተነገረ ሲሆን ችግሩ የገጠማቸው አካባቢዎችም ወደ መረጋጋት እየተመለሱ መሆኑ እየተነገረ ነው።

ፌስቡክ ኃይሌ ገብረሥላሴ ላቀረበው ክስ ምላሽ ያልሰጠ ቢሆንም፤ ድርጅቱ ግን “የሐሰተኛ ዜናዎችን ስርጭት ለመግታት” እንደሚሰራ የሚያመለክት ፖሊሲ አለው።