ጠ/ሚ ዐብይ አህመድ የ2019 የኖቤል የሰላም ሽልማት ያሸንፋሉ ተብለው ግምት ተሰጥቷቸዋል።

በመጪው አርብ በኖርዌይ መዲና ኦስሎ በሚዘጋጀው የ2019 የኖቤል የሰላም ሽልማት ያሸንፋሉ ተብለው ከሚጠበቁ ሰዎች አንዱ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ አህመድ ሊሆኑ እንደሚችሉ ታይም መፅሄት አስነብቧል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ አሕመድ ከኖቤል የሠላም ሽልማት ጋር

ጠቅላይ ሚኒስትሩ ወደ ስልጣን ከመጡ በኋላ በኢትዮጵያና በኤርትራ መካከል ከሁለት አስርት አመታት ፍጥጫ እልባት በመስጠት፤ ሰላም በማምጣት፣ የፖለቲካ እስረኞችን በመፍታትና ሌሎች ባመጧቸውም መሻሻሎች ሽልማቱን ሊያሸንፉ እንደሚችሉ በእንግሊዝ የተለያዩ ፖለቲካዊ ትንበያዎችን በመስጠት የሚወራረደው ላድብሮክ አሳውቋል። ድርጅቱ 80% (4/1) ሊያሸንፉ እንደሚችሉ ግምቱን አስቀምጧል።

ዓመታዊው ሽልማት በአለም ውስጥ ለሰላም አስተዋፅኦ ያደረጉ ግለሰቦችን ወይም ድርጅቶችን እውቅና ይሰጣል።

በባለፈው ዓመት የኮንጎ ዜግነት ያለው ዶክተር ዴኒስ ሙክዌጋና የሰብዓዊ መብት ተሟጋቿ ናዲያ ሙራድ ወሲባዊ ጥቃትን ለጦርነት መሳሪያነት መጠቀሚያነት ለማቆም በሰሩት ስራ አሸናፊ ሆነዋል።

በዚህ ዓመቱ ሽልማት 301 ዕጩዎች ያሉ ሲሆን፤ 223 ግለሰቦች እንዲሁም 78 ድርጅቶች መሆናቸውንም የኖቤል ተቋም አስታውቋል። ምንም እንኳን እነማን ዕጩዎች እንደሆኑ ባይታወቁም የተለያዩ ግለሰቦችና ድርጅቶች ግምቶቻቸውን እያስቀመጡ ነው።

ከጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ በተጨማሪ የአየር ንብረት ለውጥ ተሟጋቿ ግሬታ ተንበርግና የኒውዚላንዷ ጠቅላይ ሚኒስትር ጃሲንዳ አርደርን ግምት ተሰጥቷቸዋል።

BBC Amharic