ሰሜን ሸዋ አጣዬ ላይ ጥቃት አድራሹ ኃይል የሰለጠነ እና ዘመናዊ ትጥቅ ያለው መሆኑ ተገለጸ

በሳምንቱ መጨረሻ በአማራ ክልል ሰሜን ሸዋ በአጣዬ ከተማ እና አካባቢው ታጣቂዎች የከፈቱት ጥቃት ዛሬም መቀጠሉ ተገለጸ። በተኩስ ልውውጡ የስምንት ሰዎች ሕይወት ጠፍቷል፤ ሦስቱ የፀጥታ ኃይል አባላት ናቸው። አምስት የፀጥታ ኃይል አባላትም ተጎድተዋል።

የአጣዬ ከተማ አስተዳደር ዋና ከንቲባ አቶ ጌታቸው በቀለ ኃይሌ ከሦስት ቀን በፊት የአማራ ልዩ ኃይል የጥበቃ ማማ በነበረበት ቦታ ላይ ጥቃት ለመፈፀም የሞከረ ታጣቂ፤ በተኩስ ልውውጥ ከተገደለ በኋላ ማንነታቸው ያልታወቀ ታጣቂዎች ጥቃት መሰንዘራርን አመልክተዋል። ግለሰቡም በወቅቱ ሦስት ቦምብ እና ክላሽ ይዞ ጥቃት ለማድረስ መሞከሩን ነው የተናገሩት። ትናንት ቀኑን ጀምሮ እስከምሽቱ ሁለት ሰዓት ድረስ ተኩስ የቀጠ ሲሆን ዛሬ ከአጣዬ አቅራቢያ በሚገኙ አካባቢዎች መዛመቱንም ተናግረዋል።

የታጣቂዎቹን ማንነት ለጊዜው መፈረጅ እንደማይቻል ያመለከቱት አቶ ጌታቸው ጥቃት አድራሹ ኃይል የሰለጠነ እና ዘመናዊ ትጥቅ ያለው መሆኑን ለዶቼ ቬለ DW ገልጸዋል።«እኛ እንግዲህ እንደ አመራር እገሌ ነው እገሌ ነው ብለን ስም መስጠት አንችልም። ይሄንን መፈረጅ እና ስም መስጠት የሚችል ኃይል አለ፣ መከላከያ ሠራዊት አለ፤ ፌደራል ፖሊስ አለ።

የአማራ ክልል ልዩ ኃይልም አለ። የታጠቀው ቡድን ማን ነው የሚለውን የፖለቲካ አመራሩ ሳይሆን ሠራዊቱ ነው የሚፈርጀው። ነገር ግን የሰለጠነ፣ ዘመናዊ መሣሪያ የታጠቀ፣ በተለያዩ ቦታዎች መተኮስ የሚችል፣ ማጥቃት፣ መበተን የሚችል ኃይል ነው የለው ኃይል።»ጥቃት አድራሾቹ በተለያዩ አካባቢዎች በአንድ ጊዜ ተኩስ የመክፈት አዝማሚያ እንዳላቸውም ገልጸዋል።

በአሁኑ ጊዜ የመከላከያ ሠራዊት፣ ፌደራል ፖሊስ እና የአማራ ልዩ ኃይል በዚያ እንደሰፈረ የተናገሩት አቶ ጌታቸው በተለይ በገጠር ቀበሌዎች ተኩስ በመኖሩ ኅብረተሰቡ ስጋት ላይ በመውደቁ ተጨማሪ ኃይል እንዲገባ እየጠየቁ መሆኑንም አመልክተዋል። እንዲያም ሆኖ የጥቃት አድራሾቹ አላማ ለጊዜው ግልፅ እንዳልሆነ ነው የተናገሩት። ባለፉት ጊዜያት በደረሰው ጥቃት እንዳጋጠመው ያለ የስነልቡና ጫና ለመፍጠር ያለም ሊሆን ይችላል የሚል ግምታቸውንም ሰንዝረዋል።