ዐይነስውራን ተማሪዎች በኦሮሚያ ትምሕርት ቢሮ ላይ ተቃውሞ አሰሙ


መረጃ ቲቪ አባል በመሆን የሳተላይት ቲቪውን ቀጥታ ስርጭት፣ ወቅታዊ ዜናዎችን እና ትንተናዎችን፣ የመዝናኛ ፕሮግራሞችን፣ ስፖርት እና ሌሎችንም ዝግጅቶቻችንን በፍጥነት እና ጥራት ስልክዎ፣ ኮምፒዩተርዎ ወይም ቲቪዎ ላይ ማየት ይችላሉ። እዚህ ሊንክ ላይ በመጫን አባል ይሁኑ


DW : በኦሮሚያ ክልል በሰበታ ከተማ የሚገኘው የአይነ ስውራን ትምህርት ቤት የክልሉ ትምህርት ቢሮ አወጣው በተባለ አዲስ መመሪያ ከተወሰነ የእድሜ ክልል ውጪ ያሉ ዐይነስውራን ተማሪዎችን ያገለለ፤ ወይም ተጠቃሚ አያደርግም ሲሉ ተማሪዎች ተቃውሞአቸውን አሰምተዋል።

የክልሉ ትምህርት ቢሮ በበኩሉ አዲሱ አሰራር ተማሪዎችን ተጠቃሚ ያደርጋል ባይ ነው የሰበታ ዐይነ ስውራን ትምህርት ቤት በሀገሪቱ ካሉ ቀደምት የአይነ ስውራን ትምህርት ቤቶች አንደኛው ነው። ትምህርት ቤቱ እስከቅርብ ጊዜ ድረስ አይነስውራን ተማሪዎችን ከስድስት አመት እድሜያቸው ጀምሮ በመቀበል አና በማስተማር ለከፍተኛ የትምህርት ተቋም የሚበቁትን በማሸጋገር ፣ የተቀሩትን በሌሎች የስራ መስኮች እንዲሰማሩ ሁኔታዎችን በማመቻቸትም ይታወቃል።

ነገር ግን ቀቅርብ ጊዜ ወዲህ በትምህርት ቤቱ ውስጥ ተከሰቱ በተባሉ አስተዳደራዊ ችግሮችና የኦሮሚያ ትምህርት ቢሮ አይነስውራን ተማሪዎችን ተቀብሎ የሚያስተናግድበትን አዲስ አሰራር በመዘርጋቱ የትምህርት ቤቱ ተማሪዎች ተቃውሞሟቸውን እያሰሙ ነው።

ዐይነስውርነት በየትኛውም የእድሜ ክልል ሊከሰት እንደሚችልና ይህንኑ በአግባቡ መምራት ካልተቻለ ቁትራቸው ቀላል የማይባሉትን አይነስውራን ቤታቸው ሊያስቀር ይችላል ሲሉ ስጋታቸውን ይገልጻሉ። በዚሁ ምክንያት በተጠራው ተቃውሞ ላይ ተቃውሞውን ሲያስተባብሩ ከነበሩትና አሁን በሃሮማያ ዩኒጸርሲቲ ትምህርቱን በመከታተል ላይ የሚገኘው ተማሪ ሽብሩ ጉታ ይናገራል። «ተማሪዎች መጠየቅ የጀመሩት የኦሮሚያ ትምህርት ቢሮ ያወጣውን መመሪያ በመቃወም ነው ። መመሪያው ከሰባት እስከ አስራሁለት ዓመት የእድሜ ክልል ውስጥ የሚገኙ አይነስውራን ብቻ ናቸው በትምህርት ቤቱ ገብተው መማር የሚችሉት ይላል።

ዐይነስውርነት ደግሞ በተጠቀሱት የእድሜ ክልል ብቻ አይደለም የሚከሰተው። ጥያቄያችን በ14 እና በ15 አመት የእድሜ ክልል ውስጥም ሊከሰት ይችላል ነው። ይህ ታሳቢ አልተደረገም ። በመሆኑም መመሪያው አይነስውራንን ቤት ለማስቀረት ታስቦ የተዘጋጀ ነው እንጂ ለዐይነስውራን ለመጥቀም የመጣ አይደለም።» በትምህርት ቤቱ ለሚታየው አስተዳደራዊ ችግር ምክንያት ነው ያለውን ተማሪ ሽብሩ ጉታ ሲገልጽ አካል ጉዳተኞችን በሚያስተምር ትምህርት ቤት ውስጥ ሊያስተዳድሩ የሚገባቸው ሞያተኞች ባለመኖራቸው ችግሩ ተባብሷል ሲል ይወቅሳል።
«ትምህርት ቤቱ እየተዳደረ የሚገኘው በትክክለኛ ሞያተኞች አይደለም ።በዚያ ላይ ስለአካል ጉዳተኝነት ጠንቅቆ የሚያውቅ ሰው አይደለም እየተመራ ያለው። በመሆኑም ትምህርት ቤቱ መተዳደር ያለበት በትክክለኛ ሞያተኛ እና አካል ጉዳተኝነትን በትክክል በሚረዳ ሰው መሆን አለበት የሚል እምነት ነው ያለኝ።»

የሰበታ አይነስውራን ትምህርት ቤት እንደአንጋፋነቱ ብቃት ባላቸው ሞያተኞች የመማር ማስተማር ስራው መከወን ሲገባው በተለይ ካለፉት ሶስትና አራት አመታት ወዲህ አስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ ነው የሚሉት ደግሞ የቀድሞ የትምህርት ቤቱ መምህር ናቸው። በእርግጥ የትምህርት ጥራት ችግር በመላው አገሪቱ ያለ ቢሆንም የአካል ጉዳተኞች ሲሆን ግን የተለየ ትኩረት ሊሰጠው ይገባ ነበር የሚሉት አቶ ከተማ ሮቢ ናቸው። «የዚህ ትምህርት ቤት የትምህርት ጥራት ወድቋል። ይህም የሚለካው አንዱ የብሬል ትምህርት በሚመለከት ነው። እያየነው ነው ፤ ድሮ ስንሰራበት ከነበረው በጣም እየወረደ ሂዶ በአሁኑ ጊዜ 10ኛ፣ 7ኛ እና 8ና ክፍል ደርሰው ብሬል መጻፍ የማይችሉበት ደረጃ ደርሰዋል።»

የክለሉ ትምህርት ቢሮ በበኩሉ የሰበታ ኣ,ይነስውራን ትምህርት ቤት የትምህርት ጥራት ችግር ከሌሎች ትምህርት ቤቶች የተለየ አይደለም ይላል። የቢሮው ምክትል ኃላፊ አቶ ዓለማየሁ አሰፋ ለዶቼ ቨሌ እንደተናገሩት በመመሪያው ከአሁን ቀደም ውጪ ሆነው ይማሩ የነበሩ የ7ኛ እና የ8ኛ ክፍል ተማሪዎች ወደ ውስጥ ገብተው እንዲማሩ በማድረግ ልዩ ትኩረት ሰጥተናል ብለዋል።
የትምህርት ቤቱ ተማሪዎች ተቃውሞ ለፖሎቲካ ፍጆታ ውሎ አቤቱታቸው ተገፍቷል ለሚለው ወቀሳ አቶ ዓለማየሁ መልስ ሰጥተዋል።

«እንግዲህ ተቃውሞው የፖሎቲካ ሽፋን ተሰቶታል የሚለው እርግጠኛ ነኝ በዚህ ጉዳይ ትክክል አይደለም። ነገር ግን የትምህርት ጥራትን በተመለከተ ለማስተካከል ጥረት እያደረገ ነው ያለው። በርግጥ የብሬል ፣ የመጽሃፍት ችግር በሚከሰትበት ወቅት በውጪም ሆነ በሃገር ቤት ካሉ የአይነስውራን ማህበራት ጋር በመተባበር ችግሩን ለመቅረፍ እየሞከርን ነው።»
የክልሉ ትምህርት ቢሮ በበኩሉ አዲሱ አሰራር ተማሪዎችን ተጠቃሚ ያደርጋል ባይ ነው።