ሶስት የሲዳማ የፖለቲካ ፓርቲዎች ለምርጫ ቦርድ ማስጠንቀቂያ ሰጡ


መረጃ ቲቪ አባል በመሆን የሳተላይት ቲቪውን ቀጥታ ስርጭት፣ ወቅታዊ ዜናዎችን እና ትንተናዎችን፣ የመዝናኛ ፕሮግራሞችን፣ ስፖርት እና ሌሎችንም ዝግጅቶቻችንን በፍጥነት እና ጥራት ስልክዎ፣ ኮምፒዩተርዎ ወይም ቲቪዎ ላይ ማየት ይችላሉ። እዚህ ሊንክ ላይ በመጫን አባል ይሁኑ


DW : ሶስት የሲዳማ የፖለቲካ ፓርቲዎች ምርጫ ቦርድ የሲዳማ ሕዝበ ውሳኔ የሚካሔድበትን ጊዜ በሚቀጥሉት አምስት ቀናት ውስጥ እንዲያሳውቅ ጠየቁ። የደቡብ ክልል ምክር ቤት ጉዳዩን ትኩረት ሰጥቶ እንዲያስፈፅም የጠየቁት ፓርቲዎቹ የተጠየቀው ሳይፈጸም ቀርቶ ለሚፈጠር ፖለቲካዊ እና ሕዝባዊ ጫና ተጠያቂዎቹ ሁለቱ ተቋማት እንደሚሆኑ አስጠንቅቀዋል።

የየፖለቲካ ድርጅቶቹ ሊቃነ መናብርቶች በተገኙበት በቀረበውና በንባብ የተሰማው የጋራ አቋም መግለጫ የሲዳማ ህዝብ በተደጋጋሚ የጠየቀው በክልል የመደራጀት ጥያቄ ራሳቸውን ባገዘፉ የአምባገነን ሀይሎች ሲታፈን ቆይቷል ሲል ብሏል።
የህዝቡ ጥያቄ መብት እንጂ ልመና አይደለም ያለው መግለጫው ምላሹ መሰጥት ያለበት በፖለቲካ ስሌት እና በሙሁራን ጥናት ሳይሆን በህገ መንግስቱ መሰረት ሊሆን እንደሚገባው አሳስቧል።
ፓርቲዎቹ የሲዳማን ህዝብ በክልል የመደራጀት ጥያቄ ጋር በተያያዘ መሰረታዊና ሊፈጸሙ ይገባል ያሏቸውን ሶስት ነጥቦች በጋራ የአቋም መግለጫቸው ጠቅሰዋል።

የጋራ አቋም መግለጫቸውን ለድርጅቱ አመራሮች ከጋዜጠኖች የተለያዩ ጥያቄዎች ቀርበውላቸዋል።
ከጥያቄዎቹ መካከል የፌደራሉ መንግስት በክልል ለመደራጀት ጥያቄ ያቀረቡ ዞኖች በትዕግስት ጠብቁ በማለት ያቀረበውን ጥሪ እንዴት አያችሁት ? የፊታችን ሀምሌ 11፤ 2011 ዓም የሲዳማ ህዝብ ከደቡብ መስተዳደር ስር መውጣቱን ይታውጃል በሚለው ሀሳብ ዙሪያ የንቅናቄያቸሁ አቋም ምንድነው ? የሚሉት ይገኙበታል።
ለቀረቡት ጥያቄዎች የሲዳማ አርነት ንቅናቄ ሊቀመንበር አቶ ዱካሌ ላሚሶ ምላሽ ሰጥተዋል። ዛሬ የጋራ መግለጫቸውን ካቀረቡት ድርጀቶቹ መካከል የሲዳማ አርነት ንቅናቄ ( ሲአን ) እና የሲዳማ ሀድቾ ዴሞክራሲያዊ ደርጅት ( ሲሀዴ ድ ) ቀደምሲል ጀምሮ በሀገር ውስጥ ሲነቀሳቀሱ የቆዩ ሲሆን የሲዳማ ብሄራዊ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ ( ሲብዴ ፓ ) ግን ለውጡን ተከትሎ ከውጭ ወደ አገር ቤት የገባ ነው ።

የሲዳማ ብሄርን ጨምሮ በደቡብ ክልል የሚገኙ አስር ዞኖች እራሳቸውን በክልል ለማደራጀት የሚያስችላቸውን ጥያቄ አቅርበው ምላሽ እየጠበቁ እንደሚገኙ ይታወቃል ።
የፌደራሉ መንግስት በበኩሉ በክልል ለመደራጀት ጥያቄ ያቀረቡ ዞኖች የምርጫ ቦርድና ሌሎች አስፈፃሚ ተቋማት እስኪደራጁ በትዕግስት ይጠብቁኝ ሲል ጥሪ አቅርቧል ።
ክራይስስ ግሩፕ የተባለው ዓለም አቀፉ የቀውስ አጥኚ ቡድን በደቡብ ክልል የተነሱት የራስ የገዝ ጥያቄያዎች በአግባቡ ካልተያዙ አሁን መንግስት የገጠመውን ፖለቲካዊ ቀውስ ይበልጥ ሊያባብሰው ይችላለ ሲል ስጋቱን እየገለጸ ይገኛል።