አማራ አለ ወይስ የለም? (ፕሮፌሰር ፍቅሬ ቶሎሳ ጂግሳ)

አማራ አለ ወይስ የለም?
ፕሮፌሰር ፍቅሬ ቶሎሳ ጂግሳ

አማራ እለ ወይስ የለም ብሎ መጠየቅ ራሱ በጠራራ ፀሃይ ብርሃን አለ ወይስ የለም ብሎ አንደመጠራጠር ነው። አማራ ግጥም እድርጎ አለ። ለመሆኑ አማራ ማነው? አማራ የማራ ልጅ ነው። በጥንት ሱባ ቋንቋ “ማራ” ማለት “እውነተኛ ብርሀን” ነው። “ማ” እውነተኛ፣ “ራ” “ብርሃን” ወይም “ፀሃይ” ማለት ነው። የጥንት ግብፃውያን የፀሃይ አምላክ “ራ” ይባል ነበር። “ራዕይ” የሚለው ቃል ከእዚህ ይሰርፃል። የአማራን አባት ስም ከ “ማራ” ወደ “አማራ” ወይም “ሀማራ” የለወጡት አጋዝያን ናቸው። “ማሴ”ን “ሀማሴ”ን ወይም “አማሴን” እንደ እሉት። መሰረቱ “ማራ” ነው። ማራ— እውነተኛ ብርሃን። ውብ ስም ነው። ማራ ራሱስ ማነው? ማራ የማጂ ልጅ ነው። ማጂስ ማነው? ማጂ የነብዩና የፈላስፋው የደሸት (ደሴት)ልጅነው። ደሸት ማጂን፣ ጂማን፣ መንዲን እና መደባይን ይወልዳል። በጎጃም ከጣና ደሴቶች በአንደኛው። ደሸትን የሚዘክር ደሸት የሚባል መንደር ወይም ክተማ አሁንም ድረስ አለ። እዛው ጎጃም። እንግዲህ ደሸት አባትነቱ ለማጂ ብቻ አይደለም፤— በኋላ ከጎጃም ርቀው ሄደው ከሌሎች ህዝቦች ተደባልቀው ኦሮሞ ተብለው ለተጠሩት ለመደባይ፣ ለመንዲ፣ ለጂማም እንጂ። ደሸት ለአማራ ደግሞ አያት ነው። ማጂ እማራን ብቻ አልወለደም። ሌላም ልጅ ነበረው። ጀማ የሚባል። የአማራ ወንድም ማለት ነው። ጎጃም ሳሉ ሁሉም ቋንቋቸው ሱባ ነበር። የሱባ ፊደላት፣ የሱባ እና ግእዝ መዝገበቃላት እንዲሁም ሙሉ የሱባ መፅሃፍ በእጃችን አሉ። የፊደላቱ እና የመፅሃፉ ቁንፅል እኔ የፃፍኩአቸው ሁለትt የታሪክ መፃህፍት ውስጥ ለናሙና ይታያሉ። ማጂ እና ወንድሞቹ ከአባታቸው ከደሽት በጣና ደሴት ላይ የተወለዱት የዛሬ 3600 ዐመት አካባቢ ነው። ያኔ ቋንቋችው ንፁህ ሱባ ነበር።

የደሸት ልጆች አይተባዙ ጎጃም ሲጠብ በመላው ኢትዮጵያ መሰራጨት ጀምረው የመደባይ ልጆች ወደ ጎንደር ወንበርማ እና የዛሬው ትግራይ አቀኑ። ዛሬ “መደባይ ወለል” እና “መደባይ ዛና” ተብለው ቋንቋቸው ትግሪኛ ሆኗል። መደባይ ዛና እና መደባይ ወለል በአሁኑ ሰዐት ክትግራይ ትልልቅ አውራጃዎች ሁለቱ ናቸው። የጂማ ልጆች የዛሬው ጂማ ላይ ሰፈሩ። አሁንም የአባታቸውን ስም አንደጠበቁ ኦሮምኛ እየተናገሩ እዛው ጂማ አሉ። የመንዲ ልጆች የዛሬው ወለጋ ላይ ተቀመጡ። እሁንም ያባታቸውን ስም እያስጠሩ እዛው መንዲ፣ ወለጋ ናቸው። አነሱም ኦሮምኛ እያወሩ። የተወሰኑት የማጂ ልጆች ማራ እና ጀማ፣ ዘረ-ደሸት እና እነማይ ተብለው እዛው ጎጃም ሲቀሩ፣ የተረፉት በቦታ ጥበትና ከጋፋት ህዝቦች ጋራ መጋጨት ሰልችቶአቸው እስከዛሬ ድረስ ባባታቸው ስም ወደሚጠራው ወደ ማጂ፣ የዛሬው ወሎ እና ሸዋ መረሹ። አንዲሁም በተለያዩት የኢትዮጵያ ክፍለ-ሃገሮች ተሰማሩ። እንግዲህ ማጂ የተባለው ስፍራ የአባታቸውን ስም አስከዛሬ እያንፀባረቀ ነው። አነሱ ጎጃምን የለቀቁት የዛሬ 3200 ዐመት እካባቢ ነበር። የጀማ ልጆች ሸዋ ከደረሱ በኋላ አንድ ወንዝ አገኙና ለአባታቸው መታሰቢያ ስሙን ጀማ (ዠማ) አሉት። ይህ በሸዋ ያለው ጀማ (ዠማ ም ይባላል) ወንዝ አሁንም ድረስ አገር አቋርጦ በሸዋ ይፈስሳል። የጀማ ልጆች ከማራ ልጆች ጋራ እስከ 16ኛው መቶ ክፍል ዘመን፣ ማለትም እስከ አህመድ ግራኝ ጦርነት ድረስ በጀማ ወንዝ ማዶና ማዶ ይኖሩ ነበር። አህመድ ግራኝን በብርቱ ተዋጉትና አሸነፋቸው። በእዚህ ምክንያት ለ አረቦች በባርነት ሸጣቸው። አረቦች ደግሞ ለእንግሊዞች። ሲሸጡ ሲለወጡ ቆይተው በመጨረሻ ጃማካ ጃሜይካ ተገኙ። አገሪቱና ህዝቦቹ ጃማካ ጃማይካ የተባሉት ከእዚህ የተነሳ ነው። የጃማካኖች መልካቸው ክእማሮች በምንም አይለይም። በደመነፍሳቸው ኢትዮጵያውያን መሆናቸውን አውቀው፣ ሀይማኖታችውን የኢትዮጵያ ተዋህዶ አድርገው፣ ግእዝን ተምረው የኢትዮጵያን ሰንደቅአልማ እያውለበለቡ፣ ባህላቸውንም ኢትዮጵያዊ ለማድረግ አየተጣጣሩ ናቸው። የተወሰኑትም ወደ ኢትዮጵያ ፈልስወ ርስታችውን በሻሸመኔ መስርተዋል። ራሳቸውን እንደ ኢትዮጵያዊ ይቆጥሩ ከነበሩት ታዋቂ ጃማካኖች አንዱ እሬሳዬን በኢትዮጵያ ቅበሩት ያለው የሬጌ ዘፋኙ ቦብ ማርሊ ነበር። የደሸትን እና ልጆቹን ታሪክ እውነተኛነት ለማረጋገጥ በስሞቻችው የተመዘገቡትን ማጂ፣ መደባይ፣ ጂማ እና መንዲ የተባሉትን ስፍራዎች የሚያስንቅ ምስክር የለም።
ጎጃምን ለቅቀው ሁሉም ክሌሎች ጥንታዊ ሰዎች፣ ለምሳሌ ከ ቅማንት፣ ከሲዳማ፣ ከሃዲያ እና ከሱማሌ፣ በተደባለቁ ጊዜ፣ እንዲሁም ከግእዝ ጋራ ከበተገናኙበት ወቅት አንስቶ፣ የማራ ልጆች አማሮች፣ ከዘመን ብዛት ከሱባ የተለየ ቋንቋን አዳበሩ። ያን ቋንቋ በስማቸው አማርኛ አሉት። አማሮች የሚናገሩበት ቋንቋ ማለት ነው። ልክ የአማሮች አጎቶች የጂማ፣ የመደባይ፣ እና የመንዲ ልጆች ከጎጃም እና ክሱባ ቋንቋ ርቀው ከሌሎች ህዝቦችና ቋንቋዎች ጋር ሲደበላለቁ የፈለሰፉትን አዲስ ቋንቋ በመጀመሪያ ጋሊኛ፣ በመጨረሻ ኦሮምኛ እንደ አሉት። ነገደ “ጋሊ” ከእነሱ ውስጥ ስመጥር ነበርና በመጀመሪያ ሁሉንም ወከለ። በኋላም “ጋላ” ተባለ። ወሪጅናሉ “ጋሊ” ነው። ሰገል ወይም ጠቢብ የተሰኘው ቃል ከእዚህ ይመነጫል። ሰብአ-ሰገል ወይም ጠቢባን ሰዎች የሚለውም አባባል ከእዚሁ የተገኘ ነው። በእዚህ ዐይነት፣ ዛሬ እማራ እና ኦሮሞ የሚባሉት ነገዶች ዝቅ ሲል የደሸት፣ ክፍ ሲል ስሙን የኢትዮጵያ መጠሪያ የአደረገው ታላቅ ንጉሠነገሥት እና ካህን የነበረው የኢትዮጵ ልጆች ናችው።

ኢትዮጵ የሁለቱ ነገዶች ብቻ ሳይሆን የመላው ኢትዮጵያኖችም አባት ነው። ይህ በ ጊዜው እና በቦታው ይብራራል። ጎጃም ውስጥ የቀሩት የደሸት ልጆች ዘረ ደሸት ይባላሉ። አሁንም ድረስ። ጥቂቶች ደግሞ አነማይ ተብለው ይታወቃሉ። ይህ ሁሉ የትርክታችን ማስረጃ ነው። ሱባ ሞቶ እማርኛ ሲያብብ እነሱም የአማርኛ ተናጋሪ ሆነዋል።
እላይ አንደተጠቀሰው የደሸት ልጆች እና ልጅ ልጆች ጎጃምን ለቀው ሁለት የተለያዩ ቋንቋዎችን– አማርኛን እና ኦሮምኛን፣ መናገር ስለጀመሩ ባእዳን መስለው መተያየት ጀመሩ።

አማሮችን ብቻ ነጥለን ግን ስለህልውናቸው ስናወሳ፣ በእርግጥም አማሮችና አማርኛ የተባለው ቋንቋቸው ህያው ሆነው አብረው አሉ። ሰላእዚህ፣ አማርኛ ተናጋሪ ብቻ እንጂ አማራ የሚባል ነገድ የለም፤ የሚባለው የስህተት ስህትት ነው። ሁለቱም ቁልጭ ብለው አሉና። ለምሳሌ ሌሎች ኢትዮጵያውያን፣ አነሱ ቀርተው ፈረንጅም እንኳን አማርኛ እጥንቶ አማርኛ ሊናገር ይችላል። ሆኖም አማርኛ ስለተናገረ ብቻ በደም ወይም በዘር የማራ (የአማራ) ልጅ ሊሆን እይችልም። ለደም ወይም ለዘር ዝምድና ወሳኙ ቋንቋ ስላልሆነ። ለምሳሌ ከአፍሪካ ተፈንግለው ወደ ሰሜን አሜሪካ የተወሰዱት ጥቁር እፍሪካውያኖች በአሁኑ ሰአት ቋንቋቸው እንግሊዝኛ ነው። ነግር ግን ቋንቋቸው እንግሊዝኛ ስለሆነ በዘር እና በቆዳ ቀለም እንግሊዛዊ ወይም ነጭ አንግሎሳክሶን ሊሆኑ አይችሉም። ነን ቢሉ መሳቂያ እና መሳለቂያ ነው የሚሆኑት። ፈረንሳይኛ ወይም ጣልያንኛ ጠንቅቆ የሚናገር ትውልደ እትዮጵያዊም ቢሆን ፈረንሳይኛ እና ጣልያንኛ ስለተናገረ ብቻ በቆዳው ቀለም፣ በደሙ ወይም በዘሩ ነጭ ፈረንሳዊ ወይም ጣልያናዊ ሊሆን አይችልም። የተገላቢጦሽም አነዚህን ቋንቋዎች ስለተናረ በቀለሙ እና በዘሩ ኢትዮጵያዊ መሆኑ እይፋቅበትም።

በጎጃም የቀሩት የማራ ልጆች በአሉበት በጎጃም ፀንተው ሎሎቹ ቤታቸውን በጎንደር፣ በወሎ፣ በ 16ኛው መቶ ክፍለ ዘመን በአንድ የኦሮሞ እባት ስም ወሎ እስከመባሉ ድረስ አነሱ ላኮ መልዛ፣ ገነቴ፣ የጁ እና አማራ ሳይንት በአሉአቸው ቦታዎች፣ በሸዋ ደግሞ በቀዳማዊ ምንይልክ የጦር ሰራዊት ስም ሸዋ ክመባሉ በፊት እና በኋላ እነሱ ግራርጌ በአሉት ከግራኝ አህመድ በኋላ ሰላሌ በተባለው ስፍራ፣ እንዲሁም መንዝ፣ ተጉለት፣ አዲስጌ፣ መራቤቴ እና ቡልጋ ሲሉ በሰየሙእቸው መኖሪያዎች ከ3200 ዐመታት ያላነሰ ኖረዋል። ኦሮሞዎች፣ የእነዚሁን የወንድሞቻችውን ልጆች ፈለግ በመከተልም ከእነሱ እምብዛም ሳይርቁ በሸዋ ላይ ስፍረዋል። ዝምድናቸውንም በማስተዋል ለ 3000 ዘመናት ተቻችለው በጋብቻ፣ በሙጋሳ እና በጉዲፈቻ ይበልጥ ተቀራርበው፣ በደቦም አብረው እያረሱ የውጭ ጠላትም ሲመጣ አብረው እየመከቱ፣ በፍቅር እና ኅብር ኖረዋል። በአንድ ቤተሰብ ውስጥ አልፎ አልፎ ጠብ እንደሚኖረው ሁሉ አንዳንዴ ቢጣሉም ሳይጨካከኑ አየታረቁ ለሶስት ሺ ዐመታት አብረው ዘልቀዋል። ወደፊትም ይዘልቃሉ።

አማሮች ለኢትዮጵያ ስልጣኔ በተለያዩ ዘርፎች አበርክተዋል። ለምሳሌ ከብዙ በጥቂቱ– በሀገር አስተዳደር፣ በትምህርት፣ በስነመንግሥት፣ በስነመለኮት፣ አብያተክርስትያን በመገንባት፣ በውትድርና ሳይንስ፣ በእርሻ፣ በከብት እርባታ፣ የዱር እውሬዎችን በማሰልጠን፣ በምህንድስና፣ በክህነት፣ በመድሀኒት ጥብብ፣ በስነግጥም፣ በቅኔ፣ መፃህፍትን በመድረስ እና በምግብ አሠራር ሙያ ከፍተኛ ብቃት እና ክህሎት አሳይተዋል። ከእዚህ ሁሉ በተጨማሪ፣ የኢትዮጵያ ስልጣኔ እምብርት የሆነውን የኢትዮጵያ ተዋህዶ ቤተክርስትያንን በመንከባከብ እና ውስጣቸው ያሉትን ጥንታዊ መፃህፍት እና ንዋየቅዱሳት በመጠበቅ፣ ለሃገራቸው ዳር ድንበር በመስዋዐትነት ደማችውን በማፍሰስ፣ የንጉሠነገሥታቸውን ዙፋን በውትድርና ጥበባችው ከኢትዮጵያ እስክ ኑብያ-ሱዳን፣ ከሊብያ እስከ ግብፅ፣ ከግብፅ እስክ የመን፣ ከየመን እስከ ባቢሎን አረጋግተዋል። አፅንተዋል። ለእዚህ አባባል እማኙ አፄ አክሱማይ በልጅነቱ ራሚሱ ተብሎ የግብፅ ፈሪዖን ሳለ ዙፋኑን አየጠበቁ እነሱ በግብፅ የቆረቆሩት አማርና ብሰው የሰየሙት መንደር አሰከአሁን በግብፅ ይገኛል። አየሱስ ከርስቶስ፣ ቅድስት ማርያም እና ጠባቂያቸው ቅዱስ ዮሴፍም ከሄሮድ ሸሽተው የተጠጉት በእዚሁ በአማርና ነበር። ጠባቂያቸውም የጎጃሙ ተወላጅ ንጉስ አማናቱ ተትናይ ነበር። እየሱስ ክርስቶስ እድሜው 22 ሆኖ ወደ ኢትዮጵያ ድንበር ሊሽጋገር ሲል ይህ ንጉሥ በዛን ጊዜ ኑብያን ያስተዳድር ስለነበር ለአንድ ሳምንት ቤቱ ቆይቶ እሱን እና ቤተስቡን ባርኮአቸዋል። ይህም ታሪክ ከእየሱስ ጋራ ኢትዮጵያ ውስጥ ለ ሶስት ዐመታት የተጓዘው የንጉሡ ልጅ ማርሄር ዜና ማርሄር በተባለ መዋዕሉ ዘግቦታል። አማራ የሚለው ስም በግብፅ ክመሰራጨቱ የተነሳ ብዙ ግብፃውያን፣ ምናልባትም የኢትዮጵያ ዝርያ ያለባችው ሰዎች አማራ ተብለው ይጠራሉ። የካይሮን ከተማ ስልክ ማውጨ መመልከት ብቻ ይህን ያረጋግጣል።
አማሮች ከግብፅ ዘልለው በባቢሎን ተገኝተው አማራ የተባለውን እስከዛሬ ስማቸውን የሚያስጠራውን ከተማቸውን በባቢሎን ገንብተዋል። እንዴት ቢባል፣ ይህው በግብፅ በልጅነቱ ፈሪዖን ሳለ በጉብዝናችው እና በታማኝነታቸው እማሮችን የሚያውቃችው አክሱማይ ልጁን ሪብላን ለ ባቢሎን ንጉሥ ለ ናቡከደነፆር ሲድር ሶስት መቶ ሺ የሚደርሱትን የአማራ ወታደሮች እስዋን አጅበዋት ወደ ባቢሎን፣ የዛሬው ኢራክ፣ እንዲሄዱ ስለአደረገ ነው። ከ 13 ዐመታት በፊት ይህን ከተማ ሺአይት ጂህዲስቶች ክማእከላዊው የኢራክ መንግሥት ነጥቀው ይዘውታል። ይህ ዜና በ ወቅቱ በኒውዮርክ ታይምስ ጋዜጣ ላይ ተዘግቦ ጋዜጣው በእዚህ ፀሃፊ እጅ ይገኛል። ዳሩ ግን ከተማውን ሺአይቶች ቢይዙትም አሁንም እማራ ተብሎ አየተጠራ አማሮችን ከኢትዮጵያ ውጭ ይዘክራቸዋል። ኢትዮጵያ አገራቸው ውስጥ የሉም እይተባለ እስከነአካቴው ህልውናችው እየተካደ ባለበት ሁኔታ በግብፅና በጥንቱ ሜሶፕታሚያ ግን ጥንት ገንብተው በተዉአቻው ከተሞቻቸው መኖራቸው ይታስባል።

እላይ የሰፈረውን ለመድገም፣ ጎሳ ማለት ቋንቋ ማለት ነው። ቋንቋ ማለትም ጎሳ ማለት ነው። ቃሉም ጎስአ ከሚለው የግእዝ ቃል የወጣ ነው። የንንግግር ከፍል እንጂ የደምና ስጋ ወይም የዘር ዘርፍ እይደለም። “ጎስአ ልብየ ቃለ ሰናይ” ቅዱስ ዳዊት በመዝሙሩ እንደሚለው። “ልቤ መልካም ቃል ተናገረ” ማለት ነው። “ጎስአ” ሲዘረዘር “ተናገረ፣ ከውስጥ አፈለቀ” ማለት ነው። “አገሳ” የሚለውም ቃል ከዚህ የመነጨ ነው። የጎሳ ትርጉሙ ቋንቋ እስከሆነ ድረስ አንድ ሰው አፉን የፈታበት ቋንቋ ጎሳው ይሆናል። ቋንቋ ከዘር ወይም ከደም ጋራ ምንም ግኑኝነ ስለሌለው። ለምሳሌ አንድን የኦሮሞ ህፃን አፍ ከመፍታቱ በፊት አማሮች ተቀብለው በጉዲፈቻ ቢያሳድጉትና አፉን በእማርኛ ቋንቋ ቢፈታ ዘሩ ምንም አሮሞ ቢሆንም ጎሳው አማራ ነው። ይህ ቀሊል ፎርሙላ ነው ። በደም ከደሸትና ማጂ የሚወርደውም እማራ በህፃንነቱ ለኦሮሞ በጉዲፈቻ ቢሰጥና አፉን በኦሮምኛ ቢፈታ፣ ጎሳው ያለ ምንም ጥያቄ ኦሮሞ ነው። አንግዲህ አማራ የለም የሚለው ውዥንብር የተፈጠረው በጎሳ እና ዘር የአለውን ልዩነት ባለመገንዘብ ነው። “እማራ አለ ወይስ የለም?” ብለን ስንጠይቅ በምን? በጎሳ ወይስ በዘር ወይንስ በሁለቱም? ብለን መጠየቅ አለብን። የማራ ልጅ ማራ ወይም እማራ በሁለቱም በኩል እለ። እሱ አማራ ነው፤ ቋንቋው ደሞ አማርኛ። ኦሮሞም እንደዛው ነው። በቋንቋው ምክንያት ኦሮሞ የሚባለው ሰው በዘሩ፣ ልክ እንደ እማራው ከደሸት እና ከእሱ ሶስት ልጆች፣ ማለትም ከ መደባይ፣ ክ ጂማ እና ክ መንዲ ይወርድና ከአማራው በአንድ እባትነት ይዛመዳል። አማራ እና ኦሮሞ በቋንቋ ከመለያየታቸው በተቀር በዘር ምንጫቸው አንድ ናችው። ለዝምድና ወሳኙ ቋንቋ እንዳልሆነ፣
ይልቁንም ዘር ወይም ደም እንደሆነ ከፍ ብለን ዐይተናል። ኢትዮጵ አባታችን እና የሱ ዝርያ ደሸት ኩሻውያን ነበሩ። ስለእዚህ ሁላችንም ኢትዮጵያውያን የእነሱ ልጆች ሰለሆንን እኛም ኩሻውያን ነን። የዛሬ 4000 ዐመት ኩሻዊው ኢትዮጵ 10 ወንዶች ልጆች ወልዶ አነሱ ተባዝተው የደሸትንም ልጆች ጨምረው የአሁኖቹን ኢትዮጵያዎያኖች ሁሉ አስገኝተዋልና።
አማራ ማለት ክርስትያን ነው። ከርስትያን ማለትም እማራ ነው፤ የሚሉ አሉ። አብዛኛው አማራ ክርስትያን በመሆኑ አማራ የሚለው ስም ከርስትያን የሚል ትርጉም ለመፍጠር ቸሎአል። ሆኖም እማራ ሁሉ ክርስትያን አይደለም። በሃይማኖታቸው ሙስሊም የሆኑ አማሮችም እሉ።

ደሞም በዘር አማራ ሴም ነው የሚሉ፣ አማራን ከኩሻውያን ወገኖቹ ለመነጠልና ለማግለል የሚሹ የኢምፔሪያሊስት ዝንባሌ የአላቸው የነጭ ምሁራን እና የእነሱን ስህትት የሚያስተጋቡ እባብኛ አኪያሄድ የሚሄዱ መልካቸው ኢትዮጵያዊ የሚመስል መሰሪዎች አሉ። አማራ በዘሩ ኩሽ ነው ወይንስ ሴም አማራ በእርገጥ ኩሽ ነው እንጂ በፍፁም ሴም አይደለም። የኩሹ የኢትዮጵ ዝርያ የሆነው አያቱ ደሽት እና አባቱ ማጂ ኩሽ ሆነው እሱ በምን ሂሳብ ነው ሴም የሚሆነው? ኦሮሞዎቹ አጎቶቹ የደሸት ልጆች ኩሽ ሆነውስ እሱ በምን ምክንያት ሴም ይሆናል? በእርግጥ አማራ ኩሽ ነው እንጂ ሴም እይደለም። አማራውን ሴም ብሎ የፈረጀው ፈረንጅ ሲሆን እሱም እንዲያ ብሎ የፈረጀው አማራ እማርኛ ስለሚናገር አማርኛን እንደሴም ቋንቋ በመቁጠር ነው። ሁለተኛ ደግሞ በውትድርና ሙያው ፈረንጅን ስለአርበደበደው ይህ አማራ እንዲህ ኅይለኛ የሆነው የነጭ ዘር ሴማዊ ቢሆን ነው ብሎ የራሱን የተንሽዋረረ መላምት ስለአመነበት ነው። ፈረንጅ ያለውን ያለምርምር ኢትዮጵያውያን ምሁራን አስተጋብተው አማራ ሴም ነው፣ ብለው ደመደሙ። ይህ ታላቅ ስህተት ነው። አማርኛ ከአጋዝያን ሴማዊ ቋንቋ ከ ግእዝ ጋራ ስለተካለሰ አማሮችም እጋዝያን ወይም እስራኤላውያን ሆነዋል ማለት አይደለም። አጋዝያን የእስራኤል፣ አማሮች ደግሞ የኢትዮጵ ልጆች ናቸው። እስቀድሞ እንደአብራራሁት፣ ለዝምድና ወይም ለዘር ማንነት ወሳኙ ቋንቋ ሳይሆን ደም ነው። አማርኛ ቋንቋም ከሴሙ ቋንቋ ከግእዝ በኋለኛው ዘመን መጋባት ቢጀምርም የዛሬ 3000 ዐመት አጋዝያንን ቀዳማዊ ምንይልክ ወደ ኢትዮጵያ አምጥቶ ቋንቋቸውን ግእዝን በሱባ ቋንቋ ላይ ከማወጁ በፊት፣ እማርኛ በህይወት አንደነበረ ማስረጃዎች አሉ። ለምሳሌ ቀዳማዊ ምንይልክ ሲወለድ ስሙን ምንይልክ አባትህ ሰለሞን ቢያይህ ለማለት ምንይልክ ብለው በቋንቋቸው በአማርኛ ስም ያወጡለት እማሮች ናችው። ከቀዳማዊ ምንይልክ በሁዋላም ለሁለት ሺ ዐመታት የአማርኛ ስሞች የነበራቸው ሰለሞናዊ አጋዝያን ነገሥታት ተመዝግበዋል። ከ 3000 ዐመታት አስቀድሞ በኢትዮጵ ስርወመንግሥት ውስጥ የነገሡ የአንዳንድ ነገሥታት ስመ-መንግሥትም አማርኛ የሆነበትም ሁኔታ አለ። አማርኛ የሴም ቋንቋ ክፍል ነው የሚለውም አባባል አጠያያቂ ነው። የግእዝ እና የአማርኛ የአረፍተ ነገር የግስ አቀማመጥ ራሱ የተለያየ ነው። አማርኛ ቋንቋ ምናልባት ከግእዙ ይበልጥ ወይም ያላነሰ በኦሮምኛ ቃላት አሸብርቋል። ይህም ሃቅ የኦሮሞ እና የአማራና እውነተኛው የዘር ምንጭ በተሰኘው መፅሃፌ ተዘርዝሯል።

አማራን ሴም ነው የሚሉ ሰዎች ኦሮሞን ሁሉ ልክ ከማዳጋስካር ፈልሶ የመጣ ነው ብለው እንደሚተርኩት አማራንም ከአረብያ የመጣ ለማስመሰል ይጥራሉ። ይህንንም ሊሉ አማራን እረብ ማድረጋቸው ነው። ነገሩ ግን የተገላቢጦሽ ነው። በውትድርና ተግባሩ አማራ ወደ ግብፅና ሜሶፕታሚያ አንደዘመተው ሁሉ ወደ ቅርቧ አረብያ ወደ የመንም ጎራ ብሎ ነበር። አማራ በመጀመርያ ደቡብ አረብያን “ናግራን” አላት። በውትድርና ቋንቋ “ግራውን ይዘህ ና” ማለት ነው። በኋላ ደግሞ “የማን” ብሏት ከጊዜ ብዛት “የመን” እንደተባለች የታሪክ ሰነዶች ይጠቁሙናል። በጠቅላላው ብናወጋ፣ የሰው ዘር መገኛ የሆንነው እና በስልጣኔም ክአረቦች የምንቀድመው እኛ ኢትዮጰያውያን ቀይ ባህርን በመርከቦቻችን ተሻግረን ወደ የመን ዘምተን የስልጣኔአችንን አሻራ አትመናል። ለምሳሌ ፊደሎቻችንን በሃውልቶቻችው ላይ ቀርፀናል። ወንዝን ገድበን የመረብ ወንዛችንን ለማስታወስ ስሙን “መረብ” ወይም “ማህረብ”ብለናል። ከተማም ገንብተን አፄ እስያኤል በኢትዮጵያ ቆርቁሮአት የነበረችውን የሳባን ከተማ ለማስታወስ ስሟን ሳባ ብለነዋል። አማሮች በመጀመሪያ “ፅና” አሁን “ሰና” ወይም “ሰንአ” ለተባለችው የየመን ከተማም እድገት ኢትዮጵያውያን አስተዋፅዖ እድርገን አብያተከርስትያናት ገንብተናል። በመካ አና በመዲናም እስልምና ከመነሳቱ አስቀድመን አብያተከርስትያናት አንፀናል። ለማጠቃለል፣ አኛ ከኢትዮጵያ ተነስተን ወደ አረብያ ሄደን አረብን አሰለጠንን እንጂ በዛን ጊዜ ግመል ጠባቂ ዘላን የነበረው አረብ ከአረብያ ፈልሶ መጥቶ እኛን አላስለጠነንም።

“አማራ አለ ወይስ የለም?” የሚለውን ጥያቄ ዳግመኛ ለመመለስ ያህል፣ አዎን አማራ እለ፤ ቋንቋውም አለ። ቋንቋውም ይመስገን የኢትዮጵያን ህዝብ ሁሉ እያገናኘ ይገኛል። በዘርና በቋንቋ ወይም በጎሳ መሃል የአለውን ልዩነትም አንባቢው ከእዚህ ፅሁፍ ሊረዳ ይችላል። ታዲያ አማራው ማነው? ደግሞስ እማራ ሀበሻ ነውን? በፍፁም አይደለም። ሀበሻ የሚለው ቃል ከእዚህ በፊት አንደተነገረን አማራውን አይመለከትም። ይህ ቃል የሚመለከተው ቤተእስራኤልን ነው። ቃሉ ለቤተእስራኤልም ቢሆን መልካም እይደለም። ከቀዳማዊ ምንይልክ ጋራ ወደኢትዮጵያ የገቡት አይሁዳውያን ከኢዮጵያውያን ጋራ በሃይማኖት፣ በባህል እና በደም ተዋህድው ኢትዮጵያ ውስጥ ለ አምስት መቶ ዐመታት ከቆዩ በኋላ በባሊሎን ስድት ምክንያት የመጡት አዲሶቹ ቤተእስራኤሎች የቀድሞዎቹ ከኢትዮጵያውያን ጋራ ተካልስው ወይም ተደበላልቀው ቢያገኙአቸው፣ እናንተማ አበሳ ያለባችሁ አበሶች “ሃበሾች” ወይም “ክልሶች” ናችሁ፤ ብለው ዘለፏችው። ቀድሞ የመጡት ደግሞ “እኛስ ኢትዮጵያ የምትባል ሀገር አለችን። እናንተ ግን መጤ ፈላሾች ናችሁ፣ ወግዱ!” አሉአቸው። ሃበሻም ሆነ ፈላሻ የሚለው ቃል በቤተእስራኤሎች መሀል ያለ መተቻቻ ነው። የአማራ ጉዳይ አይደለም። አዎን አማራው ሴምም ሀበሻም አይደለም። አማራው ሃበሻ ካልሆነ ታዲያ ምንድን ነው? መልሱ በቋንቋ ምክንያት ኦሮሞ የተባሉት አጎቶቹ እንደሆኑት፣ ከፍ ሲል የኢትዮጵያ መስራች የታላቁ ንጉሠነገሥት እና ካህን የኩሻዊው የኢትዮጵ ዝርያ፣ ዝቅ ሲል ደግሞ የኩሻዊው የደሽት አብራክ፣ እንዲሁም የኦሮሞዎች ወንድም የሆነው የማጂ ልጆች ናቸው። እንግዲህ አማራው እና ቋንቋው ለመኖሩ ይህ ፅሁፍ በቂ ግንዛቤ ሰለሚሰጥ “አማራ የለም፤ አማርኛ ተናጋሪ ብቻ ነው የእለው፣” የሚሉ ሁሉ ስህተታችውን ተገንዝበው የአማራውን ህልውና እንዲቀበሉ አመክራለሁ። አማራም፣ እኔ በሃቅ እና በተጨባጭ ማስረጃ ላይ ተመርኩዤ የፃፍኩልህን ትክክለኛ ማንነትህን የሚገልፀውን ፅሁፍ ጋሻ እድርገህ ዛሬ ለተካዱት፣ ግን ህያው ለሆኑት ህልውናህ እና ማንንትህ መክትላቸው።

ፍቅሬ ቶሎሳ ጂግሳ
የኢትዮጵ እና የደሸት ልጅ፣
ደሞም የደሸት ልጆች– የመደባይ፣ የመንዲ፣ የጂማ እና የማጂ ዝርያ

ዋቢ መፃህፍት

አእምሮ ንጉሤ፥ ጥንታዊ የኢትዮጵያ የሰላም ጥበቃ ታሪክ፥አዲስ አበባ፥
ት.መ.ማ.ማ.ድ.፥2000።
አማን በላይ፥ የጥንትዋ ኢትዮጵያ ትንሳኤ ታሪክ፥አዲስ አበባ፥ቦሌ ማተሚያ ቤት፥1985።
ህዝባዊ ቀዳማዊ የኢትዮጵያ መስታወት ታሪክ፥አዲስ አበባ፥ በራስ ህትመት፥1988።
መፅሐፈ ሱባኤ ዘበአማን ካልዕ፣ አዲስ አበባ፥በራስ ህትመት፥1998።
Bowersock, G.W., The Throne of Adulis, Oxford, Oxford University Press. 2013.
Budge, E.A. Walllis (Sir) The Kebra Nagast, (translated from the Ethiopic) London, Oxford University Press,1922.
Sergew Hable Sellassie, Ancinet and Medieval Ethiopian History to 1270, Addis Ababa, United Printers, 1972.
ተክለፃድቅ መኩሪያ፥ የኢትዮጵያ ታሪክ፥ ከዐፄ ይኩኖ አምላክ እስከ ዐፄ ልብነ ድንግል፥ አዲስ አበባ፥በተስፋ ማተሚያ ቤት፥በግርማዊ ቀዳማዊ ዐፄ ኅይለሥላሴ በ 28ኛው ዘመነ መንግሥት።
“NewYork Times”, Saturday, October 21, 2006