ብሄረተኝነት ለኦሮሞ አይጠቅምም፣ ለማንም አይጠቅም ይላሉ አቶ ታከለ ኡማ #ግርማካሳ


ኢትዮጵያን ካጋጠሟት እጅግ ውስብስብ ችግሮች ለማዳን የተለያዩ ጠቃሚ ሃሳቦችን እና ገንቢ ትችቶችን የሚያቀርቡ ነፃ ሚዲያዎች ወሳኝ ሚና እንደሚጫወቱ ይታወቃል። ስለዚህም ኢትዮ360፣ መረጃ ቲቪ፣ አዲስ ድምጽ፣ ምንሊክ ቲቪ እና ሌሎችም የኢትዮጵያዊነት አጀንዳ የሚያራምዱ ሚዲያዎች በመተባበር ፕሮግራሞቻቸውን በሳተላይት ቲቪ ለኢትዮጵያ ህዝብ በማቅረብ ላይ ይገኛሉ። እነዚህ ሚዲያዎች የፈጠሩት ማህበር የሳተላይት ወጪውን መሸፈን እንዲያስችለው ይህን የጎፈንድሚ ፔጅ ከፍተናል → እዚህ ሊንክ ላይ ይጫኑ። ለትብብርዎ እናመሰግናለን።

አቶ ታከለ ኡማ በጋዜጠኛና አክቲቪስት እስክንድር ነጋ ከሚመራው የባለአደራ ምክር ቤት ጋር ለመነጋገር ቀጠሮ መያዙን ሰምቻለሁ። ይሄ መልካም ዜና ነው። መሰረታዊ የአዲስ አበባ ሕዝብ ጥያቄ ይዘው ከተነሱ ጋር የአዲሳ አበባ ከተማ አመራር ነን የሚሉ ማዳመጥና መስማት ከስራ ዘርፋቸው አንዱ ነው። እግርጠኛ ነኝ አቶ ታከለ ኡማ እነ እስክንድር ባቀረቡት ጥያቄዎች ላይ ይስማማሉ የሚል እምነት አለኝ።

ይሄን ብዬ ኢንጂነር ታከለ ኡማ ስለሰጡት አንድ ንግግር ልውሰዳችሁ። ንግግሩን በጣም ሃሪፍ ንግግር ሆኖ አግኝቼዋለሁ። “ብሄረተኝነት ለኦሮሞ አይጠቅምም፣ ለማንም አይጠቅም” ይላሉ ኢንጂነር ታከለ።

ኢንጂነር ታከለ ሲሾም የተሾሙበት አካሄድ በጣም መስመር የለቀቀና ከአዲስ አበበ አስተዳደር አሰራር ውጭ በኦዴፓ/ኦህዴድ የተሰጠ ሹመት በመሆኑ ከፍተኛ ተቃዉሞ ማቅረቤ ይታወቃል።

“ለምን ታከለ ኡማ መነሳት እንዳለበት” በሚል ርእስ ከሰባት ወራት በፊት ሶስት ምክንቶችን በማቅረብ ነበር ኢንጂነሩ እንዲነሱ ጥያቂር አቅርቤ የነበረው። አንደኛው አሿሿማቸው ትክክል ስላልነበ፣ ሁለተኛው ከመሾማቸው በፊት የነበራቸው አቋም ለአ.አ ጥቅም እንዲቆሙ አያደርጋቸው ብዬ በማሰቤና ሶስተኛ የጣይቱ ሃዉልት እንዲሰራ ከፈቀዱ በኋላ እንዳይሰራ በማድረጋቸው ነበር።

ከሶስት ሳምንታት በፊት “ሶስት ነጥቦች ስለታከለ ኡማ” በሚል ርእስ ስለ ም/ከንቲባው አዎንታዊ አስተያየት ሰጥቻለሁ።

አንደኛው አቶ ታከለ ምንም እንኳን የእቴጌ ጣይቱ ሃዉልት እንዲሰራ ከፈቀዱ በኋላ እንዳይሰራ ማድረጋቸው በወቅቱ ተቃዉሞ እንዳቀርብ ካደረግኝ አንዱ ምክንያት የነበረ ቢሆንም፣ ከመከልከላቸው በፊት መፍቀዳቸው ግን ፣ አይምሯቸው እንደተበላሸ የኦሮሞ ብሄረተኞ አንዱ አለመሆናቸውን የሚያሳይ ነው። እንደዚያ ቢሆኑ ኖሮ በመጀመሪያዉኑ አይፈቅዱም ነበር። ሆኖም ከሌሎች፣ የኦሮሞ ብሄረተኞችና በዉሸት ትርክት በአጤ ሚሊሊክ ላይ ጥሩ ያልሆነ አመለካከት ያላቸው ግፊትና ጫና ሲያሳድሩባቸው፣ በቀላሉ መንበርከካቸው ያኔ ድክመታቸው ነበር። ሁለተኛው በአድዋ በእል ላይ ተገኝተው ንግግር ማድረጋቸው በአጤ ሚኒሊክ ሃዉልት ስር አበባ ማስቀመጣቸው በአመለካከት ከጽንፈኞች የራቁ መሆኑን አሳይቶኛል። ሶስተኛና ትልቁ ጃዋርና ቄሮዎቹ፣ እንዲሁም አቶ ለማ በዉጭ አገር ሆነው ሳለ፣ በወ/ሮ ጠይባ ሃሰን የሚመራው የኦሮሞ ክልል መንግስት፣ የተሰሩ ኮንዶሚኒየሞች እጣ ለወጣላቸው ዜጎች እንዳይሰጥ በጠየቁበት ጊዜ፣ ከሳምንት በላይ ከፍተኛ የሆነ ዘመቻ በአቶ ታከለ ላይ ተደርጎም፣ አቶ ታከለ ያንን ሁሉ ግፊትና ዛቻ ወደ ጎን አድርገው ነው ስራቸው በትክክል የሰሩት።

አዎን ተቃወሞ አቶ ታከለ ኡማ ላይ ብዙ ጊዜ አቅርቢያለሁ። ወደፊት ከማቅረብ ወደኋላ አልልም። ሆኖም ተቃወሞ ሳሰማ፣ እንደ አንድ ሃላፊነት የሚሰማው ጦማሪ ምክንያታዊ በመሆን ነው። አቶ ታከለን መተቸት ብቻ ሳይሆን በሌላ ጎኑ ለሰሩትም ጥሩ ስራ እውቅና መስጠት አስፈላጊ ነው ብዬ አምናለሁ። በምክንያት እንደምቃወም በምክንያት መደገፍም አስፈላጊ ነው።

ለታከለ ኡማ ትችት ስናቀርብ፣ ኦሮሞ ስለሆነ አልነበረም። ጥሩ ነገርም ስንጽፍ ኦሮሞ ስለሆነ አይደለም። አንዳንዶች ታከለ የሚተቸው ኦሮሞ ስለሆነ ነው የሚል ደካማ አመለካከት አላቸው። ይሄ ከበታችነታቸው የተነሳ የሚናገሩት ነው። ዞረው ዞረው በሐሳብ ሲሸነፉ የጎሳ ካርድ መምዘዝ !!!

አቶ ታከለ ኡማ በቅርቡ አድ መድረክ ላይ ልብ መሳጭና ጥሩ ንግግሮች ያደረገበት አንድ ቪዲዮ አየሁ። የዶ/ር አብይ አህመድና የአቶ ለማ መገርሳ ተከታታይ ቃለ መጠይቆች ተከትሎ በተመሳሳይ መንፈስ የተቃኘ ንግግር መስሎ ነው የተሰማኝ።

አቶ ታከለ ከተናገሩት ውስጥ የሚከተለው ይገኝበታል፡

“አንድ ሰው ከኦሮሚያ እኔን እንደሚያዞር ይነገራል። እኔ ዛሬም ነገም የምሰማው የአ.አ ሕዝብ ነው”

“እኔ እኮ ማንም መናገር በማይችልበት ወቅት ኢሕአዴግን የተናገርኩ ነኝ። እንዴት ከተራ አክቲቪስት(ጃዋርን ማለታቸው ነው ብዬ አስባለሁ) ጋር ያገናኘዋል”

“ተጠያቂነቱ ለአ.አ ነዋሪ ነው። ብሄርን ከብሄር የምለይ አይደለሁም። የተወለድኩት ያደኩት አምቦ ነው። አምቦ ብሄር አይጠየቅም”

“በኢሃዴግና በሰው ፊት ቆሜ፣ አዲስ አበባ እንደ ስሟን አዲስ አባባ አደርጋታለሁ” ብዬ ቃለ መሐላ አድርጊያለሁ።

” ያደጉት አማራ ነኝ፣ ትግሬ ነኝ፣ ኦሮሞ ነኝ ከሚል ጋር አይደለም። አምቦ ነኝ ከሚል ጋር ነው።

“ብሄረተኝነት ለአዲስ አበባ አይጠቅም፤ ለኦሮሞውም አይጠቅም። የሚጠቅመው አንድ ላይ ማደግ፣ አንድ ላይ መበልጸግ ነው”

https://www.facebook.com/ethiodream18/videos/400099777437286/