የኢትዮጵያ መንግሥት ሠራዊትና በአማራ ክልል የሸመቁት የፋኖ ታጣቂዎች ዉጊያ ከገጠሙ ወዲሕ የመንግሥት ጦር በሰዉ አልባ አዉሮፕላኖች (ድሮን) ባደረሰዉ ተደጋጋሚ ጥቃት በትንሹ 450 ያክል ሰዎች መገደላቸዉ ተዘገበ። የኢትዮጵያ ፒስ ኦብዘርቫቶሪ የተሰኘዉ ተቋም እንደሚለዉ ከሚያዝያ 2015 እስከ ሕዳር 2017 ባለው ጊዜ ዉስጥ በአማራ ክልል 54 የድሮን እና የአየር ጥቃቶች መፈጸማቸውን መዝግቧል። ይሁንና “ራቅ ባሉ የሀገሪቷ አካባቢዎች የሚፈፀሙ የድሮን ጥቃቶችን ለመዘገብ ያለው አስቸጋሪ ሁኔታ ሲታይ ይህ አሃዝ ዝቅተኛ ግምት” ሊሆን እንደሚችል ፒስ ኦብዘርቫቶሪ አስታውቋል።
በጥቃቶቹ የፋኖ ታጣቂዎች እና ሰላማዊ ሰዎችን ጨምሮ 449 ሰዎች መገደላቸው ሪፖርት እንደተደረገ በኢትዮጵያ ፒስ ኦብዘርቫቶሪ ተመዝግቧል።የአማራ ማኅበር በሰሜን አሜሪካ የአድቮኬሲ ዳይሬክተር ሆነ ማንደፍሮ ደግሞ በአማራ በሚደረገዉ ጦርነት የመንግሥት ሥልት “በከፍተኛ ደረጃ ድሮን መሠረት ያደረገ” በመሆኑ “ንጹኃን ዜጎች ላይ ከፍተኛ ሰብአዊ ጉዳት እየደረሰ ነው” ሲሉ ይናገራሉ።
ጥቃቶቹ ሰዎች የሚሰበሰቡባቸው አደባባዮች፣ የትምህርት፣ የጤና እና የዕምነት ተቋማት ዒላማ ማድረጋቸውን የሚናገሩት አቶ ሆነ “ ከጦርነቱ ጋር ግንኙነት የሌላቸውን ንጹኃኖችን እየጨፈጨፉ ነው። ይኸ ደግሞ በስሕተት አይደለም” ሲሉ ለዶይቼ ቬለ ተናግረዋል። ማኅበራቸው ከጥቅምት 5 ቀን 2016 እስከ ሕዳር 14 ቀን 2017 ባለው ጊዜ ውስጥ በአማራ ክልል የተለያዩ አካባቢዎች በተፈጸሙ 125 የድሮን እና የአየር ጥቃቶች 754 ሰዎች መገደላቸውን እና 223 መጎዳታቸውን መዝግቧል። “እኛ የምንመዘግባቸው የድሮን ጥቃቶች በሰላማዊ ሰዎች ላይ ብቻ ዒላማ ያደረጉ ናቸው” የሚሉት አቶ ሆነ “ተዋጊ ኃይሎች ላይ የድሮን ጥቃት ከደረሰ አንመዘግብም” ሲሉ አስረድተዋል።