“በስንዴና ገብስ ምርቱ የሚታወቀው የአርሲ ምድር ደም ሲጠጣ የሚውል የሚያድር ከሆነ ሰነባብቷል”- እናት ፓርቲ

 

እናት ፓርቲ በዛሬው ዕለት ባወጣው መግለጫ በኦሮሚያ ክልል አርሲ ዞን ሽርካ ወረዳ፣ ሶሌ ፈረንቀሳና ሶሌ ጡጃ ቀበሌ በተፈጸመ ጥቃት በአንድ ቤተሰብ ዙሪያ ያሉ ዘጠኝ ሰዎች መገደላቸውን አስታውቋል፡፡

ፓርቲው ግድያውን “የጫካው ሸኔ” መፈጸሙን ከአካባቢው ሰዎች አደረኩት ባለው ማጣራት ማወቁን ገልጿል፡፡

ባለፉት 5 ዓመታት በተለይ ማንነትና ሃይማኖት ተኮር ዘግናኝ ግድያዎች እንደሚፈጸሙ እና በስንዴና ገብስ ምርቱና በደግነቱ የሚታወቀው የአርሲ ምድር ዛሬ ዛሬ ደም ሲጠጣ የሚውል የሚያድር ከሆነ መሰነባበቱን ፓርቲው ከአካባቢው ነዋሪዎቹ ለማወቅ ችያለሁ ብሏል፡፡

እንዲሁም ከሰሞኑ በዚሁ አካባቢ 2 ሰዎች ተገድለው ሌሎች 8 ሰዎች ታግተው እንደተወሰዱ የአካባቢው ነዋሪዎች የገለጹ ሲሆን ታጋቾቹ የትና በምን ሁኔታ ላይ እንዳሉ ምንም ዓይነት መረጃ እንደሌላቸውም መናገራቸውን አመላክቷል፡፡

በተጨማሪም ‘መከላከያ ነን’ ያሉ ሀይሎች ከነዋሪው በግዳጅ መሣሪያ እየወሰዱ እንደነበር የገለጹት ነዋሪዎች ይህም በተለይ በአካባቢው ለሚንቀሳቀሰው ታጣቂ ኃይል እጅግ ምቹ ሁኔታ እንደፈጠረለትና በቀላሉ መንደር ውስጥ ገብቶ ገድሎና ዘርፎ እንደሚወጣ ከሞላ ጎደል አካባቢውን ወደማስተዳደር እየሄደ መሆኑን በመግለጫው አስታውቋል፡፡

ጥቃቱ በተፈጸመበት አካባቢም በግምት 3 ኪ.ሜ ርቀት ላይ የመከላከያ ሠራዊት ካምፕ እንዳለው የተገለጸ ሲሆን ጥቃት የተሰነዘረባቸውን ነዋሪዎች ለመታደግ ምንም ዓይነት እንቅስቃሴ እንዳላደረገና ለማትረፍ ጥረት እንዳልነበረ እናት ፓርቲ ገልጻል፡፡