በአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ሥር አድባራትና ገዳማት ለመቀጠር እጅ መንሻ ብር እየተጠየቀ ነው የሚለውን መረጃ ሃገረ ስብከቱ አስተባበለ

ዋዜማ ሬዲዮ የተባለው የበይነ መረብ መገናኛ ብዙሃን ባሰራጨው ዘገባ ዙሪያ የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት የሰጠው መግለጫ ።
++++++++++++++++++++++++++++++++++
የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን በሀገር ውስጥ ካሏት አኅጉረ ስብከት መካከል በምእመናን እና በአገልጋይ ካህናት ብዛት በአንደኛ ደረጃ የሚመደብ ነው።
ሀገረ ስብከቱ በ1952 በወጣው የፍትሕብሔር ሕግ አንቀጽ 398 እና 399 መሠረት ሕጋዊ ሰውነት ያለው የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን አስተዳደራዊ መዋቅር ነው።
በጥቅምት 2015 ዓ.ም የቅዱስ ሲኖዶስ ምልዐተ ጉባኤ ያጸደቀው ሕገ ቤተ ክርስቲያን አንቀጽ 57 “የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት እንደማንኛውም ሀገረ ስብከት በራሱ ሊቀ ጳጳስ የሚመራ ሲሆን ተጠሪነቱም ለመንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ቤተ ክህነት ሆኖ ከሌሎች የሚለይባቸው ልዩ ሁኔታዎች ስላሉ እነዚህን ሁኔታዎች ከግምት አስገብቶ በቅዱስ ሲኖዶስ በሚወጣ ደንብ ይመራል” በሚል ደንግጓል። በዚሁ የሕገ ቤተ ክርስቲያኑ ድንጋጌ መሠረት የጥቅምት 2015 ዓ.ም የቅዱስ ሲኖዶስ ምልዐተ ጉባኤ የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት የሚመራበትን መተዳደሪያ ደንብ አጽድቋል። ከዚህ ጊዜ ጀምሮ ሀገረ ስብከቱ ቅዱስ ሲኖዶስ አጽድቆ በሰጠው መተዳደሪያ ድንብ መሠረት አገልግሎቱን በመፈጸም ላይ ይገኛል።
ይህ በእንዲህ እንዳለ ነሐሴ 8 ቀን 2016 ዓ.ም “ዋዜማ ሬድዮ” የተሰኘ የበይነ መረብ መገናኛ ብዙኃን ፍጹም ሀሰት የሆነ በአጠቃላይ የቤተ ክርስቲያኗን ስም በተለይ ግን የሀገረ ስብከቱን መልካም ስም እና ዝና የሚያጎድፍ “በአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ሥር አድባራትና ገዳማት ለመቀጠር እጅ መንሻ ብር እየተጠየቀ ነው” በሚል ሀሰተኛ ዜና አሰራጭቷል። ዋዜማ ሬዲዮ ይህንን ሀሰተኛ ዜና አገልጋይ ካህናት እና ምእመናን በጠቅላላው ያስቆጣ ድርጊት ነው ምክንያቱም በጾመ ፍልሰታ ሱባኤ ውስጥ በነበሩበት ወቅት በማሰራጨቱ ለቤተ ክርስቲያናችን ያለውን ጥላቻ ንቀት ያሳያል። ሀገረ ስብከቱም በተሰራጨው ዜና ላይ የሱባኤው ወቅት እስኪጠናቀቅ ምላሽ ከመስጠት ተቆጥቦ ቆይቷል። ይህም የሆነ በወቅቱ የቤተ ክስርቲያን ዋና ትኩረት ለምእመናን ድህነት ለሀገረ ሰላም ሱባኤውን መፈጸም በመሆኑ ነው።
ዋዜማ ሬዲዮ የተሰኘው የበይነ መረብ መገናኛ ብዙሃን ያሰራጨው ዜና ፍጹም ሀሰት ስለመሆኑ፦
ዋዜማ ሬዲዮ የተባለው የበይነ መረብ መገናኛ ብዙሃን ባሰራጨው ዘገባ “ትልቅ ሀብት የሚያንቀሳቅሱና ከፍተኛ የገቢ ምንጭ ያላቸው ናቸው በሚባሉ አድባራትና ገዳማት አሥተዳዳሪ፣ ጸሐፊ፣ ሂሳብ ሹም ሆኖ ለመቀጠር ከፍተኛ ብር እጅ መንሻ (ጉቦ) እንዲከፍሉ እንደሚጠየቁ” ገልጿል። ይህ ፍጹም ሀሰተኛ መረጃ ነው።
በአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ባለፉት ሁለት ዓመታት ከአንድ ቦታ ወደ ሌላ ቦታ ከተደረገ ዝውውር እና እድገት ውጪ አንድም የአድባራት እና የገዳማት አስተዳዳሪ፣ ጸሐፊ እና ሒሳብ ሹም ቅጥር አልተፈጸመም።
በሀገረ ስብከቱ መተዳደሪያ ደንብ አንቀጽ 10(4) መሠረት በሀገረ ስብከቱ ጽ/ቤት እና በክፍለ ከተማ ቤተ ክህነት ጽ/ቤት ቅጥር እድገትና ዝውውር የሚፈጸመው በጠቅላይ ቤተ ክህነት ሲጸድቅ ብቻ ነው። ስለዚህ ሀገረ ስብከቱ በራሱ የሚፈጽመው ቅጥር የለም።
ሀገረ ስብከቱ የገዳማትና አድባራት አስተዳዳሪዎችን በቀጥታ የሚቀጥርበት አስራር የለውም። በሀገረ ስብከቱ መተዳደሪያ ደንብ አንቀጽ 25(7) መሠረት አንድ የደብር አስተዳዳሪ የሥራ መደብ ሊያገኝ የሚችለው “በሀገረ ስብከቱ ሊቀ ጳጳስ ምርጫ በጠቅላይ ቤት ክህነት አቅራቢነት በቋሚ ሲኖዶስ ሲጸድቅ እና ቅዱስ ፓትርያርኩ ደብዳቤ ሲጽፉ” ብቻ ነው። ሀገረ ስብከቱ ከዚህ አስራር ውጪ የቀጠረው የደብር አስተዳዳሪ የለም። ዋዜማ ሬድዮ ይህንን ረጅም ሰንሰለት ያለውን አስራር ከሀገረ ስብከቱ ሳያጣራ በእጅ መንሻ ሰዎች እንደሚቀጠሩ የጻፈው ዜና ሀሰተኛ ነው።
በሕገ መንግስቱ አንቀጽ 29(6) መገናኛ ብዙሃን የሰውን ክብርና መልካም ስም የመጠበቅ ግዴታ ተጥሎባቸዋል። እንዲሁም በመገናኛ ብዙሃን አዋጅ ቁጥር 1238/2012 አንቀጽ 61(9) የበይነ መረብ መገናኛ ብዙሃን የተሳሳተ መረጃ መፈጠር ማተምና ማስራጭት እንደሌለባቸው ተደንግጓል። ዋዜማ ሬዲዮ ይህንን ከእውነት የራቀ ዘገባ የሰራው በሕግ የተጣለበትን ግዴታ ጥሶ ነው።
ዋዜማ ሬዲዮ “አሁን ላይ በቤተክርስቲያኒቱ ያለው የቅጥር ሁኔታ በሕግና በስርዓት ማስታወቂያ ወጥቶ ሰዎች አመልክተውና ተወዳደረው ሳይሆን ገንዘብ የመክፈል አቅም ያላው የሚቀጠርበትና ሥራ የሚያገኙበት እንደሆነ” አድርጎ የሰራው ዜና ፍጹም ሀሰት ነው። ይህ አገላለጽ ሀገረ የስብከቱንና መላውን የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን የብልሹ አሠራር ቤት እንደሆነች አድርጎ በሀሰት የሚከስ ነው። ሚዲያው ይህንን ድምዳሜ ሲጽፍ በጥቆማ ነገሩኝ ከሚላቸው “ምንጮች” በስተቀር ቤተ ክርስቲያኒቱ ያላትን የአገልጋዮች ቅጥር እድገትና ዝውውር ሕግጋት እና አስራር ምንም ሳይመረምር ነው። ይህም ሆነ ተብሎ ሀገረ ስብከቱን በጠቅላላውም የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያንን ለመኮንን የተደረገ ሥራ ነው።
የሚዲያ ተቋሙ “ተቀጣሪን ከቀጣሪ የሚያገናኙ ደላላዎች የጉዳዩ ዋና ተዋናዮች ሲሆኑ ሥራ ፈላጊዎቹን ካሉበት ፈልገው በሀገረ ስብከት ውስጥ ከሚሰሩ ሰዎች ጋር በቀጥታ የሚያገናኟቸው ሲሆን፣ ደላሎቹም ከሚገኘው ገንዘብ ላይ ድርሻ እንዳላቸው” አድርጎ የሰራው ዘገባም ፍጹም ሀሰት ነው። ሀገረ ስብከቱ የቅጥር የእድገትና የዝውውር ጉዳዮችን በመተዳደሪያ ደንቡ መሠረት የሚፈጽም እንጂ በደላላ የሚሰራው ሥራ የለም አሰራሩም በየጊዜው በጠቅላይ ቤተ ክህነታችን ቁጥጥር ድጋፍና ክትትል የሚደረግበት ስለሆነ ለሀገረ ስብከቱ በነጻ የተሰጠ አይደለም። የሚዲያ ተቋሙ ይህንን ሳያጣራ ሀገረ ስብከቱ በደላላ ሠራተኛ እንደሚቀጥር አድርጎ የሰራው ዘገባ ፍጹም ሀሰት ነው።
ዋዜማ ሬዲዮ ሠራተኛን በእጅ መንሻና በደላላ እንደሚሰራ “ከሀገረ ስብከቱ ሊቀ ጳጳስ ጀምሮ፣የሀገረ ስብከቱ ዋና ሥራ አስኪያጅ፣ የየመምሪያው የሥራ ኃላፊዎች እንዲሁም በየደረጃው ያሉ ሰዎች የሚያውቁትና ተደጋጋሚ አቤቱታ የቀረበበት” እንደሆነ አድርጎ የሰራው ዘገባ ሐሰተኛ ነው። ሀገረ ስበከቱ የሠራተኛ ቅጥርን በእጅ መንሻ እና በደላላ ፈጽሞ አያውቅም እየፈጸመም አይደለም። ይህንን ጉዳይ በሚመለክት ለሀገረ ስብከቱ በይፋ የቀረበ አቤቱታ የለም። የሚዲያ ተቋሙ የሀገረ ስብከታችንን ሊቀ ጳጳስ ጉዳዩን እንደሚያውቁ በድፍረት ዘገባ ሲሰራ ብፁዕነታቸውን አላነጋገረም።
ዋዜማ ሬዲዮ የሀገረ ስብከቱን ዋና ሥራ አስኪያጅ ሊቀ ማዕምራን የማነ ዘመንፈስ ቅዱስ በዘገባው የተጠቀሰው ችግር መኖሩን እንዳረጋገጡለት አድርጎ የሠራው ዜናም ትክክል አይደለም። የሀገረ ስብከታችን ዋና ሥራ አስኪያጅ ለመገናኛ ብዙሃኑ የሰጡት ምላሽ በደፈናው ችግሮች ካሉ ከጠቅላይ ቤተ ክህነት ጋር በመነጋገር ለመፍታት ጥረት እየተደረገ መሆኑን እንጂ ለተሰራው ዘገባ ትክክለኛነት የሰጡት ምንም ዓይነት ቃለ መጠይቅ ሳይኖር እንደሰጡ ተደርጎ መዘገቡ ሐሰት ነው።
በሀገረ ስብከቱ መተዳደሪያ ደንብ አንቀጽ 11 መሠረት ሀገረ ስብከቱን የመምራት እንዲሁም በማንኛውም አካል ፊት የመወከል ሥልጣን የሊቀ ጳጳሱ ሆኖ ሳለ የሚዲያ ተቋሙ ደረሰኝ የሚለውን ጥቆማ ከሁሉም አስቀድሞ ሊያጠራ የሚገባው ከሀገረ ስብከታችን ሊቀ ጳጳስ ነበር። ነገር ግን ከሀገረ ስብከቱ ሊቀ ጳጳስ ምንም ዓይነት ማጣራት ሳይደረግ፣ ብልሹ አሰራሩ እንዳለ እሱን ለማቃናት ኮሚቴ እንደተቋቋመ የተሰራው ዘገባ በሀገረ ስብከቱ ያለውን እውነታ በምልዐት የሚያሳይ አይደለም።
ዋዜማ ሬዲዮ የተሰኘው የበይነ መረብ መገናኛ ብዙሃን የሠራተኛን ቅጥር ሁኔታ አስመልክቶ ሀገረ ስብከቱ ላይ ዘገባ ሲሰራ ተገቢውን ማጣራት አላደረገም። ሀገረ ስብከቱ እንደማንኛውም ተቋም ያሉበትን የአሰራር ክፍተቶች ለማሟላት በርካታ የአሰራር ማሻሻያዎችን እያደረገ እንዲሁም ተጨማሪ ማሻሻያዎችን ለማድረግ ከፈተኛ ጥረት በማድረግ ላይ ይገኛል። በአሁኑ ሰዓት ሀገረ ስብከቱ የሠራተኛ ቅጥር ዝውውር እድገት ሙሉ ለሙሉ አግዷል። ከአጥቢያ አብያተ ክርስቲያናት እስከ ዋናው የሀገረ ስብከቱ ጽ/ቤት ድረስ ያለውን የሠራተኛ ብዛት ቆጠራ በማድረግ ላይ ይገኛል። እንዲሁም ያለ አግባብ የተዛወሩ ከሥራ ውጪ ሆነናል በማለት ቅሬታ ያቀረቡ ሠራተኞች የሚለይና የመፍትሔ ሀሳብ የሚያቀርብ ኮሚቴ በማቋቋም በርካታ ሥራዎችን በመሥራት ላይ ይገኛል። ዋዜማ ሬዲዮ ዘገባውን ሲሰራ ኃላፊነት እንደሚሰማው እንደ አንድ የሚዲያ ተቋም ይህንን የሀገረ ስበከቱን ተጨባጭ የማሻሻያ ጥረት መግለጽ ሲገባው ሐሰተኛው ዜና ብቻ ላይ ትኩረት ማድረጉ ለተቋሙ ያለውን ጥላቻ ያሳያል።
በመሆኑም፦
ዋዜማ ሬዲዮ የተሰኘው የበይነ መረብ መገናኛ ብዙሃን ነሐሴ 8 ቀን 2016 ዓ.ም የሠራውን ዘገባ በመገናኛ ብዙሃን አዋጅ ቁጥር 1238/2012 አንቀጽ 50(3)(ሀ) መሠረት እርማት እንዲሰጥ እንጠይቃልን፣ እርማት የማይሰጥ ከሆነ በሕግ መሠረት አስተዳደራዊ ፍትሕን ከመገናኛ ብዙሃን ባለሥልጣን እንዲሁም ፍትሕን ከፍርድ ቤት እንደምንጠይቅ ለመግለጽ እንወዳለን።
በተሰራው የተዛባ ዘገባ የተሳሳተ ግንዛቤ የያዛችሁ መላው የሀገረ ስብከታችን አገልጋዮች እና ምእመናን እንዲሁም የቤተ ክርስቲያናችን የበላይ አመራር አካላት ከላይ የተብራራውን የሀገረ ስብከታችንን እውነታ እንድትረዱ በታላቅ አክብሮት ለመግለጽ እንወዳለን።
ነሐሴ 30 ቀን 2016 ዓ/ም
አዲስ አበባ።