የመንግሥት የጸጥታ አካላት አባሎች የሚፈጸሙ እገታዎች ተባብሰው ቀጥለዋል – ኢሰመኮ

የሕግ አለመከበር እና የመንግሥት መዋቅር መላላት ስርአት አልበኝነትን አንግሷል-ኢሰመኮ

በአገሪቱ የህግና ስርአት አለመከበርና የመንግስት አገርን አረጋግቶ የመምራት ሂደት አለመቻል ስርአት አልበኝነትን እያነገሰ ነው ሲል የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን አስታውቋል፡፡

ኮሚሽኑ ይህን ያለው በአማራና በኦሮሚያ ክልሎች ያለውን የሰብአዊ መብቶች ጥሰት በሚመለከት ክትትል እና ምርመራ አድርጎ ውጤቱን ባሳወቀበት ወቅት ነው፡፡

በአማራና ኦሮሚያ ክልሎች ከተራዘሙ የትጥቅ ግጭቶች ጋር ተያይዞ በአንዳንድ አካባቢዎች በተፈጠረው የሕግ ማስከበር እና የመንግሥት መዋቅር መላላት ሳቢያ በሰላማዊ ሰዎች ላይ በታጣቂ ኃይሎች፣ ለዘረፋ በተደራጁ ቡድኖች እንዲሁም በአንዳንድ የመንግሥት የጸጥታ አካላት አባሎች የሚፈጸሙ እገታዎች ተባብሰው ቀጥለዋል ብሏል፡፡

አጋቾች ሰላማዊ ሰዎችን በአብዛኛው በጉዞ ላይ እያሉ አንዳንዴም ከመኖሪያ ቤታቸው ወይም ከሥራ ቦታቸው አግተው ወዳልታወቀ ቦታ በመውሰድ ከፍተኛ የማስለቀቂያ ገንዘብ ክፍያ  እንደሚጠይቁ ኢሰመኮ አመላክቷል፡፡

እገታው በአብዛኛው እንደ ገቢ ማስገኛ የተወሰደ መሆኑን፤ አልፎ አልፎም እንደ በቀል፣ ለፖለቲካ ዓላማ ወይም የታገተ ሌላ ሰውን ለማስለቀቅ በሚል በአጸፋ መልኩ የሚፈጸም መሆኑን ባደረገው ምርመራ አስታውቋል፡፡

በዚህም የታገቱ ሰዎችን ለማስለቀቅ ገንዘብ እንደሚጠየቅ እና መክፈል ያልቻሉ ታጋቾች የድብደባ ግድያ እንዲሁም ጾታዊ ጥቃት እንደሚደርስባቸው ተጠቁሟል፡፡

በዓለም አቀፉ የሲቪል እና ፖለቲካ መብቶች ቃልኪዳን እንዲሁም ሌሎች አግባብነት ያላቸው ዓለም አቀፍና አህጉራዊ ማዕቀፎች መሠረት በጦርነት ዐውድ ውስጥ የሚፈጸም እገታ በዓለም አቀፍ የሰብአዊነት እንዲሁም የወንጀል ሕግ መሠረት የጦር ወንጀልን ሊያቋቁም የሚችል በመሆኑ፣ መንግሥት ብቻ ሳይሆን የታጠቁ ቡድኖችም ድርጊቱን ከመፈጸም የመታቀብ ዓለም አቀፍ ግዴታ እንዳለባቸው ኮሚሽኑ አስታውሷል፡፡

በመሆኑም የፌዴራል እንዲሁም የክልል መንግሥታት ለችግሩ ተገቢውን ትኩረት በመስጠት በተለይም በተደጋጋሚ እገታ በሚፈጸምባቸው አካባቢዎች እገታን ለመከላከል ውጤታማ የጥበቃና ቁጥጥር ሥራዎችን ከማከናወን በተጨማሪ የታጋቾችን ደኅንነት በጠበቀ መልኩ የማስለቀቅ ሥራዎችን እንዲያጠናክሩ አሳስቧል፡፡

ehrc.org/?p=29639