በጎንደር ከተማ ታግታ የነበረች የሁለት አመት ህፃን መገደልን ተቃውመው አደባባይ ከወጡ ሰዎች መሀል ሶስቱ መገደላቸው ታወቀ

በጎንደር ከተማ ታግታ የነበረች የሁለት አመት ህፃን መገደልን ተቃውመው አደባባይ ከወጡ ሰዎች መሀል ሶስቱ መገደላቸው ታወቀ

(መሠረት ሚድያ)- ባሳለፍነው አርብ ነሀሴ 24 ጎንደር ከተማ ውስጥ ከታገተች በኋላ እስከ ትናንት ድረስ በየመንገዱ እና በየቤተክርስቲያኑ ገንዘብ ሲሰበሰብላት የነበረችው የሁለት አመት ህፃኗ ኖላዊት ዘገዬ በአጋቾች በጭካኔ መገደሏን ተከትሎ ለተቃውሞ ‘ፒያሳ’ በተባለው ስፍራ አደባባይ ከወጡ ሰዎች መሀል ሶስቱ በፀጥታ አካላት መገደላቸውን የአይን እማኞች ማምሻውን ለመሠረት ሚድያ ተናግረዋል።

በጎንደር ከተማ ቀበሌ 03 የታገተችው ህፃን ኖላዊት ቤተሰቦች የተጠየቀውን ገንዘብ መክፈል ስላልቻሉ ከህዝብ ሲያሰባስቡ ቆይተው በመጨረሻ ቢከፍሉም “ክፍያውን አዘገያችሁ” ያሉት አጋቾች ህፃኗን እጅግ አሰቃቂ በሆነ መንገድ ገድለው ቤተሰቦች ደጃፍ መጣላቸው ይታወሳል።

አባት የህፃኗን አስከሬን በመያዝ “ፍረዱኝ” ብሎ ዛሬ ቀትር አካባቢ አደባባይ የወጣ ሲሆን አባትየውን የተቀላቀሉ ነዋሪዎች ከፀጥታ አካላት በተተኮሰ ጥይት በርካቶች እንደተመቱ ታውቋል፣ ሶስቱ ህይወታቸው እንዳለፈ ምስክርነታቸውን ለመሠረት ሚድያ የሰጡ የአይን እማኞች ተናግረዋል።

አንድ ስሜም ሆነ የምሰራበት ጤና ተቋም ስም አይጠቀስ ያለ በከተማው የሚገኝ የህክምና ባለሙያ ስምንት ገደማ በጥይት የተመቱ ቁስለኞችን በዛሬው እለት ተቀብለው በርብርብ ማከማቸውን ጨምሮ ተናግሯል።