የትግሉ መዳኛም መሞቻም ይሆናል! በአስቸኳይ መፍትሔ ይሻል!
ባለፈው ሳምንት አገዛዙ ፋኖን ከሕዝብ ጋር ለማጋጨት እየሰራ እንደሆነ በዝርዝር ፅፌያለሁ። አንደኛው የእገታ ጉዳይ ነው። በእገታው አገዛዙ ከፍተኛ እጅ አለበት። ነገር ግን የፋኖ አመራርም ጉዳዩን ትኩረት አልሰጠውም። እንዲያውም አገዛዙ ፋኖን ከማህበረሰቡ ጋር አጋጭቶ ትግሉን ለማኮላሸት የሚያደርገውን ጥረት የፋኖ አመራርም ሆነ አባላት በዝምታም ሆነ በተዘዋዋሪም ሆነ በቀጥታ ተሳትፎ ሳያውቁት እያገዙት ነው።
በሁሉም የአማራ ክፍል እየተባባሰ የመጣው በጎንደር እየከፋ የመጣው እገታ ጉዳይ ላይ ፋኖ የአቅሙን መፍትሔ መስጠት፣ አቋሙን ማሳወቅ፣ አሊያም ከህዝብ ጋር ሆኖ ታግሎ ከፍተኛ የፖለቲካ ድል ማግኘት ሲችል እየታማበት ነው። አደገኛ ነው!
የጎንደሩን ሁኔታ አብነት እጠቅሳለሁ።
1) የፋኖ የቅርብ ዘመድና ወዳጆች ታግተው በነፃ ተለቅቀዋል። ይህ ጎንደር ውስጥ በስም ተጠቅሶ “የፋኖ እንትና እህት፣ የፋኖ እንትና ጎረቤት” ተብሎ እየተወራበት ያለው ጉዳይ ነው። ታጋቾች የተፈቱት የፋኖ አመራሮች በቀጥታ ደውለው ነው። ይህ ማለት የፋኖ አመራሮች ለራሳቸው ዘመድ ወዳጆች ያደረጉትን ለሌላው ሕዝብም ማድረግ ይችላሉ። የፋኖ አመራሮች አስፈራርተውም ቢሆን ያስለቀቁ፣ አፋኖችን ያውቃሉ ማለት ነው። የአገዛዙን ዋና ኃይሎች አሳድደው አዲስ አበባ ያስገቡ የፋኖ አመራሮች ከጫካ ወደ ከተማ እየመጣ ንፁሃንን የሚያግት ወንበዴ ልክ ማስገባት ሊያቅታቸው አይችልም። ትኩረት ስላልሰጡት ነው። ከህዝብ ጋር የበለጠ የሚያጋምድ የፖለቲካ ድል እንደሚያስገኝ ስላልገባቸው፣ ዋና አላማ ከሚሉት የሚያናጥብ ስለመሰላቸው ይሆናል። ግን ስህተት ነው። ህዝብህን ሳትይዝ ትግል የለም። ከወንበዴ ጋር ጎን ለጎን እየተላለፉ ድል አይመጣም። አሁን ጭራሽ ትግሉ እየታማበት ነው።
2) የፋኖ አባላትም ሆኖ ደጋፊዎች በተለያዩ ሚዲያዎች እየቀረቡ ለአገዛዙ ይሰራሉ የሚሏቸውን አካላት በፎቶና በስም ጭምር ያጋለጡበት ጊዜ አለ። በርካታ ሰው ከመጥቀሳቸው የተነሳ የንፁሃን ስም ጭምር አብሮ የሚነሳበት አጋጣሚም ታይቷል። በቅርብ ደግሞ እርስ በእርስ ስም መጠፋፋቱ ጦፏል። የፋኖ አመራሮችን ስም እያነሱ በሚዲያ መተቻቸትና መወጋገዝ እየተለመደ ነው። ለአገዛዙ እየሰሩ ነው በሚል የሚጠቀሱትን ጨምር የጋራ አላማ ያላቸው የፋኖ አመራሮችን ስም ለማንሳት ያልከበዳቸው የፋኖ አመራርና አባላት ደጀናቸው የሆነውን ህዝብ የሚያግቱና የሚገድሉትን ከፍ ሲል አገዛዙ ፋኖን ከህዝብ ጋር ለማጋጨት እየተጠቀመባቸው ያሉትን ወንበዴዎች ስም ዘርዝሮ ለህዝብ ማሳወቅ፣ ከህዝብ ጋር እንደሚታገሏቸው መግለፅ ያልደፈሩበት ምክንያት አሳማኝ አይደለም። ምክንያቱም የከተማው ህዝብ “እንትና የሚባል ፋኖ ዘመዱን በነፃ አስለቅቋል” እያለ እየተናገረ ነው። በነፃ የተለቀቁ የፋኖ ቤተሰቦች ስለመኖራቸው የተረጋገጡ መረጃዎችም አሉ።
3) አማራ ከሌሎች ክልሎች ሲሳደድ “የሚደርስለት ስለሌለ” አልን። አሁን ፋኖ በቅርብ ያለበት ህዝብ የሚወደውን ከተማ ለቅቆ እየተሰደደ ነው። ከአማራ ክልል በቅርብ ጊዜያት የሚደረጉ በረራዎች አብዛኛውና ለአካባቢው ስራ የሚፈጥረው አካል ጓዙን ጠቅልሎ የሚሰደድባቸው ሆነዋል። ይህ ስደት ታግቶ ከመዘረፍ፣ ከሞት ለመዳን የሚደረግ ነው። ይህን ለማስቆም የሚችለው አገዛዙ አይደለም። አገዛዙማ ማስመረር ነው አላማው። ደስታው ነው። ፋኖ ግን የአገዛዙን ሰራዊት እየተፋለመ አራት አምስት ሆነው ንፁሃንን የሚያግቱትን በየቦታው ልክ አስገብቶ የሚሰደዱትን “አለሁላችሁ” ማለትና የራሱ ቋሚ ደጋፊዎች ማድረግ ይችል ነበር። የአገዛዙን አካሄድ ከህዝብ ጋር ሆኖ ገትቶ የተቆጣጠረውን አካባቢ ሰላም መፍጠር እንደሚችል ቢያሳይ ዓለም አቀፍ ተቀባይነቱም በናረ ነበር። ዋና ትኩረት አልሆነም።
4) ከግለሰቦች አልፎ የባለሀብት መኪኖች እየተያዙ በሚሊዮን ብር እየተከፈለባቸው ነው። ከፍተኛ የፋኖ አመራር ልቀቁ ብሎ አዞ ከስር ያሉት “የእኛ ወታደር ምን ሊበላ ነው?” ብለው አንድ ሚሊዮን ያስከፈሉት ባለሀብት አካባቢውን ለቅቆ ሄዷል። ለሽምግልና የሄዱ አባቶች ተይዘው የቡድን መሳሪያ ካልገዛችሁ አትለቀቁም ተብለዋል። እገታ በአይነት ተከፍሏል። ይህ ከመርህ ያፈነገጠ አካሄድ ከፋኖ ለቅቀው የሄዱ፣ አገዛዙ አሁን የሚጠቀምባቸው አግቶ ብር መቀበልን እንደ ስራ እንዲቆጥሩት አድርጓል።
5) በፋኖ ስም ሚዲያ ላይ እየተዋወቁ እገታ የሚፈፅሙ ፋኖ ፋኖዎች እንዳልሆኑ የሚያውቃቸው አካላት አሉ። ከፋኖ ወጥተው በዚህ ወንጀል የተሰማሩ አሉ። እገታ ሲፈፅሙ ከርመው ፋኖን የሚቀላቀሉ አሉ። ስለእነዚህ አካላት ፋኖ በይፋና የሚጠቅመውን አላደረገም። አንዳንድ አካባቢዎች ፋኖ በወንበዴዎች ላይ እርምጃ ወስዷል። ነገር ግን እንደ አላማ አልወሰደውም። ከህዝብ ጋር አልሰራበትም። የአቅሙንና የሚጠቅመውን ያህል አልሄደበትም።
6) ፋኖ የሚሊሻን ብቻ ሳይሆን የቴሌና መብራት ኃይል ዘበኛን መሳሪያ አስወርዷል። ድሮ እናቶች እሪ ሲሉ ባሉበት ጥይት ተኩሰው ወንበዴን የሚያደናግጡ ዘበኞች ጭምር አሁን መሳሪያ አልባ ናቸው። ችግሩ ይህ አይደለም። ፋኖ የራሱን ፀጥታ አላስቀመጠው። ጦርነት ባለበት ሁሉ መዞር እንጅ የራስን ፀጥታ አዋቅሮ አካባቢን ማረጋጋት የሚባል አልተሰራም። የፀጥታ መዋቅር ይፈርሳል የራስ ፀጥታ መዋቅር አይዘረጋም የቻለ የሚዘርፍበት ሁኔታ ይፈጠራል። አሁን የተረፈው የአገዛዙ ፀጥታ የሚጠብቀው ባለስልጣንን ነው። ህዝብ ጠባቂ የለውም። ጠባቂ መሆን ያለበት ፋኖ ነው። አሊያም ሚሊሻውን ከራሱ ጋር በሚሄድ መንገድ አደራጅቶ መቀጠል ነበረበት።
አሁን አስቸኳይ መፍትሄ ያስፈልጋል።
1) እገታ በአገዛዙ ዋና ሴራ፣ በፋኖ የአካሄድና የትኩረት ችግር የመጣ መሆኑን አምኖ ተቀብሎ በአስቸኳይ መገምገም። በግምገማ ሌሎች ምክንያቶችም ሊገኙ ይችላሉ። ማካተት።
2) ከህዝብ ጋር ላለመጋጨት፣ ውስጥ ውስጡን እየተወራ ያለውን መረጃ በመያዝ በአስቸኳይ ማጥራት።
3) በዚህ መሰረት እገታ፣ ግድያና ዘረፋ በህዝባችንና በትግሉ ላይ የተደቀነ ፈተና መሆኑን አምኖ ህዝብን አስተባብሮ መታገል።
4) እገታ የሚፈፅሙ አካላት በማጋለጥ፣ ፋኖ ጋር ግንኙነት ያላቸውን ተገቢውን የዲስፕሊን እርምጃ በመውሰድ፣ በፋኖ ስም እየተንቀሳቀሱ የሚያግቱትን የእሱ አካል እንዳልሆኑ በማሳየት እንደሚታገላቸው በተግባር ማሳየት።
5) በጉዳዩ ላይ ህዝብን አወያይቶ፣ የጋራ አቋሞ ይዞ ይፋ ማድረግና እነዚህ አጋቾች ላይ ግልፅ ወታደራዊ ዘመቻ መጀመር።
እንዲህ ካልሆነ ጉዳዩ እየተለባበሰ፣ አገዛዙ እየተጠቀመበት፣ ህዝብ ውስጥ ውስጡን እያወራው ትግሉን ይገድለዋል። ከአሁኑ መፍትሔ ከተሰጠው ግን አገዛዙ ለህዝብ ማድረግ የማይችለውን አድርጎ ፋኖ ትግሉንም ሕዝብንም ያድንበታል። የነገ ቋሚ ደጋፊዎቹን ያፈራበታል። ፖለቲካ ያተርፍበታል። የአማራን ትክክለኛ አላማ የሚቦረቡረውን የጎንዮሽ የወንጀል ቡድን ያጠፋበታል። ፋኖ ከተማ ገብቶ ድንቅ ጀብዱ እንደፈፀመ በየቀኑ እየተወራ የራሱ አካባቢ ጫካ ላይ ማንም ወንበዴ ሲፈነጭ ዝም ካለ አረም ሆኖ ትግሉን ይበላዋል።
ህዝብ ማለት ዝም ብሎ ጅምላ አይደለም። ከቤታ ታንቃ ጫካ ተወስዳ ቤተሰቦቿ የተጠየቁትን መክፈል ባለመቻላቸው የምትገደል ህፃን፣ የሚሰቃይ ሽማግሌ፣ መውጫ መግቢያ ያጣው ወጣት ነው ሕዝብ ማለት። ህዝብ ማለት ተሳቅቆ እየተሳደደ የሚገኘው ነው። ህዝብ ማለት እያንዳንዱ በእገታ የሚሰቃየው፣ በልመና ተሰብስቦለት የሚከፍለው ነው። ወለጋና መተከል፣ ራያና ወልቃይት ላይ ሲፈፀም የኖረ ጭካኔ አሁን ቦርቆ ባደገበት አማራ ክልል ውስጥ ቦርቆ ባደገበት የከተማ ዳር ሲፈፀም የዚህን ህልውና ከማስጠበቅ፣ ይህን ከትግል የሚያጣላ እንቅፋት ከመንቀል የሚቀድም ትግል የለም!