የጠቅላይ ሚኒስትሩ የውይይት መድረኮች አንድምታ

ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) ከአዲስ አበባ ከተውጣጡ ነዋሪዎች ጋር ባደረጉት ስብሰባ የ1997 ዓ.ም. ምርጫ ወቅት አጋጣሚ ያሉትን በምሳሌነት አንስተው ነበር፡፡ በ1997 ዓ.ም. ምርጫ ሰሞን ተቃዋሚዎች ኢሕአዴግን የማጥላላት ዘመቻ በሰፊው መክፈታቸውን በማስታወስ በየቤተ ክርስቲያኑ፣ በየዕድሩ፣ በየትራንስፖርቱ፣ በየቦታው ኢሕአዴግ ዘረኛ ነው፣ ኢሕአዴግ እንዲህ ነው፣ እንዲያ ነው… ወዘተ እያሉ፣ በወሬ ስሙን ማስጠፋት እንደ ምርጫ መፎካከሪያ ስትራቴጂ መጠቀማቸውን ገልጸው ነበር፡፡

የጠቅላይ ሚኒስትሩ የውይይት መድረኮች አንድምታ | Ethiopian Reporter | ሪፖርተር

ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) ከከፍተኛ ግብር ከፋዮች ጋር ባደረጉት የውይይት መድረክ የተካፈሉ ተወያዮች

ያኔ እንደ አሁኑ የመገናኛ ብዙኃን ባለመስፋፋታቸው ተቃዋሚዎቹ የከፈቱት በወሬ የኢሕአዴግን ስም የማጠልሸት ዘመቻ በመላ አገሪቱ ተዳርሶ የሚፈልጉትን ውጤት ማምጣት ባያስችልም፣ በአዲስ አበባ ከተማ ግን እንደተሳካላቸው ተናግረዋል፡፡ ይህን መነሻ በማድረግ ልክ እንደ 1997 ዓ.ም. ብልፅግናን በወሬ ማሸነፍ አይቻልም ሲሉ የተናገሩት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ ‹‹እከሌ ይህን አልሠራህም ቢለኝ እኔ አለኝ ብዬ የማሳየው የሠራሁት ብዙ ሥራ አለና በወሬ ማጠልሸት አይቻልም፤›› ነበር ያሉት፡፡

በዚሁ የውይይት መድረክ ስለፖለቲካ ፓርቲዎች ተፎካካሪነትና ስለፓርቲያቸው ብልፅግና ትኩረት የሚስቡ ነጥቦችን ሲያሰሙ ተደምጠዋል፡፡ ‹‹የብልፅግና ፈተና የቀነጨሩ ፓርቲዎች ናቸው፡፡ ኦነግ፣ ኢሕአፓ፣ መኢሶን ምናምን 50 ዓመት አስቆጥረዋል፡፡ ነገር ግን ከሞቱ ቆይተዋል፣ እነሱ አሁንም አለን ይላሉ፡፡ ብልፅግና 14.5 ሚሊዮን አባል ይዞ በአፍሪካ ትልቁ ፓርቲ ቢሆንም በውስጡ ገና ብዙ አሰስ ገሰስ አለ፡፡ ብዙ ሌባ፣ ቀጣፊ፣ አጭበርባሪና የማይሠራ አለ፤›› በማለት እሱን የማጥራት ሥራ እንደሚከናወን ተናግረዋል፡፡

ዓብይ (ዶ/ር) በዚህ የውይይት መድረክ ያነሷቸው እነዚህ ነጥቦች ግን ጥያቄ የሚያስነሱ መሆናቸውን የሚናገሩ አሉ፡፡ በ1997 ዓ.ም. ምርጫ ወቅት ተቃዋሚዎች ሰብሰብ ብለው ራሳቸውን አጠናክረው መቅረባቸው ብቻ ሳይሆን፣ ከኢሕአዴግ የተሻሉ የፖሊሲ አማራጮች ይዘው መምጣታቸው ለተሻለ ተፎካካሪነት እንዳበቃቸው በርካቶች ይገልጻሉ፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትሩ በወቅቱ ሚዲያዎች ባይስፋፉም ቢሉም በነበሩት ሚዲያዎችና በተፈጠሩት መድረኮች ተቃዋሚዎች በክርክር ሕዝብ በማሳመን ከኢሕአዴግ ተሽለው መቅረባቸውንም የሚያስታውሱ አሉ፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትሩ እንዳሉት በምርጫ 97 ተቃዋሚዎች በወሬና ስም ማጥፋት ሳይሆን በምርጫ ፉክክሩ የተሻሉ ሆነው መቅረባቸው ለተሻለ ውጤት አብቅቷቸዋል ሲሉ ታዛቢዎች ይናገራሉ፡፡

በሌላ በኩል አንጋፋ የፖለቲካ ድርጅቶች ‹‹እያደገ ያለው›› ተብሎ ለተገለጸው ብልፅግና ፓርቲ ችግር ናቸው ተብለው መፈረጃቸው አሳማኝ አይደለም የሚሉ ጥቂት አይደሉም፡፡ በአዘቦት ቀርቶ በምርጫ ሰሞንም ቢሆን ጠንካራ የፖሊሲና የአማራጭ ሐሳቦች ፉክክር በኢትዮጵያ መታየቱ እንደቀዘቀዘ በመጥቀስ፣ በፀጥታ የተኙና መግለጫ ሲያወጡም ብዙ የማይደመጡ ተፎካካሪ ፓርቲዎች የብልፅግና ችግር ተብለው መገለጻቸውን አንዳንዶች ተቃውመውታል፡፡ ብልፅግና የቀነጨሩ ከሚላቸው ተፎካካሪ ድርጅቶች ይልቅ በራሱ ውስጥ ያለውን ንቅዘት እንዲፈትሽ ያሳሰቡም አልጠፉም፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ (ዶ/ር) ከሰሞኑ በተከታታይ ከተለያዩ የኅብረተሰብ ተወካዮች ጋር ያደረጓቸው ውይይቶች ከፖለቲካ ጋር በተገናኘ ብቻ ሳይሆን፣ በተለያዩ መንገዶች ትኩረት ሳቢ አጋጣሚዎች የታዩባቸው ነበሩ፡፡ በርካቶች እነዚህን ከአንድ ሰዓት ተኩል ባልበለጡ ቪዲዮዎች በአርትኦት ተከሽነው በመንግሥት መገናኛ ብዙኃን የቀረቡ የውይይት መድረኮች ተዓማኒነት ጥያቄ ውስጥ ሲከቷቸው ቢታዩም፣ ትኩረት ሳቢ ሐሳቦች ሲንሸራሸሩባቸው ነበር፡፡

ውይይቶቹ ልክ በኢሕአዴግ ዘመን ሲደረግ እንደቆየው በጥንቃቄ ተመልምለው የመጡ፣ በማኅበረሰብ ወኪልነት ስም ካድሬነት የተጠናወታቸው ሰዎች የተካፈሉባቸው ናቸው ሲሉ የተቹ አሉ፡፡ መንግሥት የራሱን ደጋፊዎች ሰብስቦ አድናቆትና ውዳሴ ከንቱ ለመስማት ያደረጋቸው መርሐ ግብሮች እንጂ የማኅበረሰቡ ችግር በተገቢው ሁኔታ የተነሳባቸው ሀቀኛ የውይይት መድረኮች አይደሉም ሲሉ አንዳንዶች ይተቻሉ፡፡ መንግሥት ከተለያዩ ቦታዎች የሰበሰባቸውን ተወያዮች የሚላቸውን ሰዎች በአማላይ የቤተ መንግሥትና የሙዚየም ፕሮጀክቶች ግንባታዎች ጉብኝት ትኩረታቸውን በመበተን፣ የሕዝብ ጥያቄ ሳያነሱ የውይይት መድረኮቹ እንዲበተኑ አድርጓል የሚሉም አሉ፡፡

ይሁን እንጂ መንግሥትና በደጋፊዎቹ በኩል በዚህ ዙሪያ የሚደመጠው ተቃራኒ ሐሳብ ነው፡፡ እነዚህ የውይይት መድረኮች መመቻቸታቸው በራሱ በመንግሥትና በሕዝብ መካከል መቀራረብ የሚፈጥሩ ናቸው ይላሉ፡፡ የሕዝቡን አሳሳቢ ጥያቄዎች ለመፍታት ዕድል ተመቻችቷል የሚሉት እነዚህ ወገኖች የትግራይ ክልል ተወካዮች ያነሱት የጡረተኞችን ተቆራጭ የተመለከተው ጥያቄ፣ ከዚያው ከቤተ መንግሥት ሳይወጡ መመለሱን እንደ ምሳሌ ያነሳሉ፡፡ መንግሥት በጠቅላይ ሚኒስትር ደረጃ የሕዝብን ብሶትና ችግር ለማድመጥ የውይይት መድረክ ማዘጋጀቱን በራሱ ትልቅና ከዚህ ቀደም ያልታየ በማለት በአድናቆት ያሞገሱ በርካቶች ናቸው፡፡

ከአማራ ክልል ተወካዮች ጋር ተደረገ በተባለው ውይይት የተጀመረው ይህ የውይይት መድረክ ከኦሮሚያ፣ ከኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን፣ ከአዲስ አበባ ከተማ፣ ከወንጌላዊያን አብያተ ክርስቲያናት፣ ከኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት፣ ከደቡብ ኢትዮጵያ፣ ከደቡብ ምዕራብ፣ ከሲዳማና ከማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልሎች ተወካዮች፣ እንዲሁም ከሶማሌ፣ ከአፋር፣ ከሐረሪ፣ ከጋምቤላ፣ ከቤኒሻንጉል ጉሙዝና ከድሬዳዋ ተወካዮች ጋር የተደረጉ ውይይቶች የተስተናገደበት ነው፡፡

ይሁን እንጂ ከትግራይ ክልል ተወካዮች እንዲሁም ከታማኝ ግብር ከፋዮች ጋር የተደረጉት ውይይቶች ከሁሉም ከፍ ያለ ትኩረትን የሳቡ እንደ ነበር በርካቶች ይገልጻሉ፡፡ በእስካሁን ሒደት ከዘጠኝ ያላነሱ የውይይት መድረክ ቪዲዮዎች ናቸው በመንግሥት መገናኛ ብዙኃን ሲሠራጩ የታየው፡፡ እነዚህ የውይይት መድረኮች መንግሥት እንደገለጸው የማኅበረሰቡ ችግሮች በሀቀኝነት የተስተናገደባቸው ናቸው ወይ የሚለው ጥያቄ በጉልህ ይነሳል፡፡

በሌላ በኩል ደግሞ መድረኮቹ በራሳቸው የግልጽነትና ተዓማኒነት ጥያቄ ይነሳባቸዋል፡፡ ወደ ሥልጣን ሲመጣ የካቢኔ ውይይቶችን ጭምር በቀጥታ በሚዲያ ለሕዝብ ስለማሠራጨት ቃል ሲገባ የተደመጠው የዓብይ (ዶ/ር) አስተዳደር፣ እነዚህን የውይይት መድረኮች ኤዲት ባልተደረጉ የቀጥታ ሥርጭቶች ለሕዝብ ለማሠራጨት ለምን መድፈር አቃተው ሲሉ ይጠይቃሉ፡፡ የውይይት መድረኮቹ በተሠራጩባቸው ቪዲዮዎች የተነሱ ጥያቄዎች ብቻ ናቸው ወይ የውይይቶቹ ማጠንጠኛ ሲሉ የሚጠይቁም አሉ፡፡

እነዚህ የውይይት መድረኮች ላይ የተነሱ ሐሳቦችና ጥያቄዎች መድረኮቹንም ሆነ የማኅበረሰቡን ፍላጎትና የአገሪቱን ተጨባጭ ሁኔታ የሚመጥኑ ናቸው ወይ የሚል ጥያቄም ይሰማል፡፡ በሌላ በኩል በየመድረኮቹ ለተነሱ ጥያቄዎችና ሐሳቦችም ቢሆን ተገቢ ምላሾችና ማብራሪያዎች ተሰጥተውባቸዋል ወይ የሚል ጥያቄም እየተነሳ ይገኛል፡፡

እነዚህን የውይይት መድረኮች በጥንቃቄና ታስቦባቸው የተዘጋጁ የፖለቲካ ነጥብ  ማስቆጠሪያ መርሐ ግብሮች ናቸው ብለው የፈረጇቸውና ችግር ለማድመጥ ካለው ቅንነትና ፍላጎት የተካሄዱ ውጤታማ የውይይት መድረኮች ናቸው የሚሉ እንዳሉት ሁሉ፣ በተቃራኒው ደግሞ ረብ የለሽ  የካድሬ መርሐ ግብሮች አድርገው ያጣጣሏቸውም ነበሩ፡፡

ያም ቢሆን ግን የውይይት መድረኮቹ በአንድ ወይም በብዙ መንገዶች ተመሳሳይ የሆኑ ሐሳቦች በተደጋጋሚ የተነሳባቸው ነበሩ ማለት ይቻላል፡፡ በሁሉም የውይይት መድረኮች ላይ የሰላም ጥያቄ ተደጋግሞ ተነስቷል፡፡ በሁሉም ውይይቶች ላይ የኑሮ ውድነት አሳሳቢነት ተደጋግሞ ተስተጋብቷል፡፡ በሁሉም ውይይቶች ላይ የመሠረተ ልማት አቅርቦት ጉዳይ በተደጋጋሚ ተነስቷል፡፡

በሁሉም ውይይቶች ላይ ጠቅላይ ሚኒስትሩ በአዲስ አበባ አካባቢ አሠሯቸው ለሚባሉ የሙዚየምና ቤተ መንግሥት ግንባታዎች ከተወያዮች ምሥጋና መጉረፉ መድረኮቹን ያመሳስላቸዋል፡፡ ልክ እንደተነሱ ጥያቄዎችና አስተያየቶች ሁሉ በመድረኮች የተሰጡ ምላሾችና ማብራሪያዎችም ቢሆኑ ተመሳሳይነት የታየባቸው ነበሩ፡፡ የሰላምና ፀጥታ ጉዳይን በተመለከተ የተሰጠው ሕዝቡ ራሱ ነው ሰላሙን ማስጠበቅ ያለበት የሚል ይዘት ያለው ምላሽ በየመድረኮቹ ተደጋግሞ ሲነሳ ተደምጧል፡፡ በመሠረተ ልማትም ሆነ በሌሎች መስኮች ባለፉት አምስት ዓመታት የተሠራው ሥራ ከቀደሙ ዓመታት ከነበረው ሁኔታ አንፃር የተሻለ ዕድገትና አፈጻጸም የታየበት እንደሆነ፣ መንግሥት በሁሉም መድረኮች ደጋግሞ ሲያስገነዝብ የታየ ጉዳይ መሆኑም ይወሳል፡፡

ከለውጡ ወዲህ የተሻለ ነፃነት በአገሪቱ መስፈኑን መንግሥት ደጋግሞ ገልጿል፡፡ ለሃይማኖት ተቋማት መጠናከርም ሆነ በሰላምና በነፃነት መንቀሳቀስ ከለውጡ ወዲህ የተሻሉ ድጋፎችን መንግሥት ስለማድረጉ ደጋግሞ በውይይቶቹ ከማንሳት በተጨማሪ ሲመሠገንበትም ታይቷል፡፡

መንግሥት በእነዚህ ውይይቶች ከወንኳቸው ወይም አሳካኋቸው ለሚላቸው ነገሮች ኅብረተሰቡ ተገቢውን አድናቆትና ዋጋ እንዲሰጣቸው መፈለጉም በሁሉም መድረኮች ደጋግሞ ሲጠቀምባቸው ከታዩ አገላለጾች መታዘብ ይቻላል፡፡ ‹‹ጉድለቶች አሉ ነገር ግን ጉድለቶቻችንን በጋራ እየሞላን እንሄዳለን እንጂ የተሠራውን ሥራ እንዳልተሠራ አድርጎ ማስቀመጥ አይቻልም፤›› የሚል ይዘት ያለው የጠቅላይ ሚኒስትሩ ገለጻ፣ መንግሥት አልሠራም ተብሎ እንዳይበየን ካላቸው ሥጋት ያነሱት ነው የሚሉ አልጠፉም፡፡

በሌላ በኩል እነዚህ መድረኮች መንግሥት በጠላትነት የሚፈርጃቸውና ወዳጅ የሚላቸው ኃይሎች እነማን እንደሆኑ ከብዙ በጥቂቱ ያመላከቱ ነበሩ በሚል እየተገለጸ ነው፡፡ የፌስቡክና የዩቲዩብ አርበኞች ዋነኞቹ ሰላም አደፍራሾች ሲባሉ በተደጋጋሚ ተደምጧል፡፡ ውጭ አገር ተቀምጠውና ልጆቻቸውን ውጭ እያስተማሩ የደሃን ልጅ እሳት ውስጥ ለመማገድ የሚፈልጉ ኃይሎች በሚል የተፈረጁ ጠላቶች በተደጋጋሚ ሲነሱ ነበር፡፡ በሌላ በኩል ‹‹የኢትዮጵያን ብልፅግና ለማደናቀፍ የተነሱ›› እንዲሁም ‹‹አገር ለማፍረስ የሚያሴሩ›› በሚል የተፈረጁም ነበሩ፡፡

እነዚህ የውይይት መድረኮች አገር ከሚመራ ጠቅላይ ሚኒስትር ጋር የተለያዩ የኅብረተሰብ ክፍሎችን ይወክላሉ የተባሉ ሰዎች የተነጋገሩበት እንደ መሆናቸው መጠን፣ በብዙ መንገዶች ሕዝብን ያስመረሩ አሳሳቢ ጉዳዮች ይነሱባቸዋል ተብሎ ተጠብቆ ነበር፡፡

ልክ እንደ የሰላም ጉዳይ ሁሉ ሙስናና ምዝበራ እንዲሁም የአስተዳደር በደልና የመልካም አስተዳደር ጉድለት ችግሮች በአሳሳቢነት በስብሰባዎቹ ላይ ተነስተው ነበር፡፡ የሥራ አጥነትና የኑሮ መሠረት የማጣት ጉዳይም እንዲሁ  በአሳሳቢነት ተነስቶ ነበር፡፡ ይሁን እንጂ ልክ ለሰላሙ ጉዳይ እንደተሰጠው ሁሉ ለእነዚህ አሳሳቢ ጉዳዮችም አጥጋቢ ምላሽ መሰጠቱን በርካቶች በጥርጣሬ ነው የታዘቡት፡፡

መንግሥት በተለይ በሙስናና ምዝበራ ጉዳይ ላይ ያለውን አቋም ያነሳበት አጋጣሚ በብዙዎች ዘንድ ሥጋት የጫረና ያልተጠበቀ ሆኖ ይጠቀሳል፡፡ ለባለሥልጣናትና ለመንግሥት አስፈጻሚዎች ተገልጋዩ ኅብረተሰብ ጉቦና ምልጃ መስጠትን አለማምዷል የሚል ወቀሳ መንግሥት ሲያንፀባርቅ መታየቱ ያልተጠበቀ ነበር፡፡ መንግሥት በተለይ በአዲስ አበባና በዙሪያዋ የሚሠራቸው የውበትና የመናፈሻ ልማት ሥራዎች በቅሬታ ምንጭነት እንዲነሱበት ያለመፈለግ ሁኔታ በእነዚህ ውይይቶች ተደጋግሞ መነሳቱ ይወሳል፡፡ ‹‹ታዩታላችሁ በጥቂት ጊዜያት የአዲስ አበባንና የኢትዮጵያ ገጽታ እንቀይራለን፤›› የሚለው የጠቅላይ ሚኒስትሩ ተደጋጋሚ ገለጻ፣ ግንባታዎችን እያፈረሱ መልሶ የመገንባት ጉዳይ በበጎ እንዲታይ መንግሥታቸው መፈለጉን አመላካች መሆኑ በብዙዎች ዘንድ መነጋገሪያ ነበር፡፡

በሌላ በኩል ተከባብሮና ብዝኃነትን አቻችሎ ከመኖር ውጪ ሌላ አማራጭ የሌለባት ኢትዮጵያ ስለመፈጠሯ ተደጋግሞ በመንግሥት ተነስቷል፡፡ ‹‹የማረጋግጥላችሁ በአማፂነትና በሽፍትነት ሥልጣን መያዝ በኢትዮጵያ ከእንግዲህ ዕድል የለም፤›› ሲሉ የተናገሩት ጠቅላይ ሚኒስተሩ፣ የሥልጣን መወጣጫው መንገድ ሰላማዊ ፖለቲካ ስለመሆኑ አስታውቀዋል፡፡

ጫት ትውልድ ገዳይና ከእምነት ጋር መገናኘት ያሳሰቡት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ ከጫት ንግድ የተያያዙ ችግሮች እንዲፈቱ ይደረጋል ብለዋል፡፡ ከኢኮኖሚ ቀውሱ በተለይም ከኑሮ ውድነቱ ጋር ለተያያዙ ጥያቄዎች አርሶ አደሮች ምርት እንደሚደብቁ ተነግሯል፡፡ በሌላ በኩል የዶላር እጥረት ችግር በችግርነት ሊነሳ የማይገባው ተብሎ መቅረቡ፣ እንዲሁም ከዕርቅና ከሰላም መስፈን ጋር ለተያያዙ ጥያቄዎች ‹‹እናንተም በራሳችኑ የበኩላችሁን ሞክሩ›› የሚል ምላሽ መሰጠቱ ከመድረኩ ሊገኝ የሚችለውን ውጤት አሳንሶታል የሚል ሐሳብ እያሰጠ ይገኛል፡፡

እንደ የወልቃይትና የራያ ዓይነት ከሁለት ክልሎች አልፎ አገርን ለጦርነት ሊዳርጉ የሚችሉ የአጨቃጫቂ ቦታዎች ጉዳይ በእነዚህ ውይይቶች ተነስቶ ነበር፡፡ ‹‹ወደ አገሬ ስመለስ የሚገጥመኝን ባላውቅም እናገራለሁ›› በሚል አሳሳቢ የሰላም ጉዳይን ካነሱ አንድ የአማራ ክልል ተወካይ ጀምሮ፣ በርካቶች በተለያዩ መድረኮች አንገብጋቢ የሚባሉ የሰላም ጉዳዮችን ሲያነሱ ታይተዋል፡፡ ይሁን እንጂ ለእነዚህም ሆነ ለሌሎች አንገብጋቢ ጉዳዮች አጥጋቢ መልስ አልተሰጠም የሚለው ጉዳይ እያከራከረ ነው፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ በተለይ ከ2002 ምርጫ ወዲህ በተከታታይ ከተለያዩ የኅብረተሰብ ክፍሎች ወኪሎች ጋር ውይይት ማድረጋቸው፣ ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ (ዶ/ር) ከሰሞኑ በተከታታይ ከተለያዩ የኅብረተሰብ ክፍል ወኪሎች ጋር እያደረጉ ካሉት ውይይት ጋር በተነፃፃሪነት እየተነሳ ነው፡፡ አቶ መለስ አንዴ የወጣት ፎረሞችን፣ የሴቶች ፎረሞችን፣ ኮከብ አርሶ አደሮችን፣ ባለሀብቶችንና አርቲስቶችን ጭምር በሚሊኒየም አዳራሽ እየጠሩ በሚያናግሩበት በዚያ ወቅት አንዳንድ ወገኖች ግን ሁሉንም አካታች ሀቀኛ ውይይት እንዲደረግ ሲጠይቁ ነበር፡፡

ከሰሞኑ የተለያዩ የውይይት መድረኮች ሥርጭት መደጋገምን ተከትሎም ቢሆን መንግሥት ከዚህ ወጥቶ ሀቀኛ የውይይት መድረኮች እንዲያመቻች ጥያቄዎች እየቀረቡ ነው፡፡