አፓርታይድና ዘረኘነት በድሬዳዋ፣ ሃረር፣ አዳማ/ናዝሬትማ ጂማና በርካታ ቦታዎች #ግርማካሳ

 
በድሬዳዋ 40:40:20 በሚል የድሬዳዋን ከተማ የኦሮሞና የሶማሌ ፖለቲከኞች ናቸው እየተፈራረቁ የሚያስተዳድሩት። አርባ ለኦሮሞ፣ አርባ ለሶማሌ ተመድቦ ሌላው ማህበረሰብ 20% ድርሻ ብቻ ነው ያለው። ከዚህም ዘረኛ አሰራር የተነሳ ህዝቡ፣ በተለይም ኦሮሞና ሶማሌ ያልሆነው ማሀብረሰብ ላለፉት ሃያ ሰባት አመታት ከፍተኛ በደልና መድልዎ ሲደርስበት ነበር። የዚህ ሕዝብ ብሶት ገንፍሎ ላለፉት በርካታ ቀናት ድሬዳዋ ከተማ ከፍተኛ ሕዝባዊ ተቃዉሞን እያስተናገደች ነው።
 
ከድሬዳዋ በባሰ ሁኔታ በሌሎች ማህበረሰባት ላይ በደል፣ ግፍና ልዩነት የሚፈጸምባቸው ሌሎች ከተሞችና አካባቢዎች ጥቁት አይደሉም።
 
ከድሬዳዋ አቅራቢያ ያለችዋን ታሪካዊቷን የሃረር ከተማ መውሰድ እንችላለን።በዚያ 8% ነዋሪው አደሬ ነው። 30% አማራ፣ 56% ኦሮሞ። ኦሮሞና አደሬ ያልሆኑት 36% ናቸው። ግን የከተማዋና የሃረሬ ክልል መስተዳደር የተያዘው 50% በኦሮሞ ፣ 50% በአድሬ ነው። ሌሎች አማራዎችን ጨምሮ 36% ነዋሪዎች ምንም መብት የላቸው። ዜሮ። ስለዚህ በሃረር፣ ከድሬዳዋ በባሰ 50፡50 ዘረኛ አሰራር ነው ያለው ማለት ይችላል። አምሳ ለኦሮሞ፣ አምሳ ለአደሬ።፣ ዜሮ ለሌሎች።
 
ወደ አዳማ/ናዝሬት ስንሄድ ደግሞ ሌላ የባሰ ሁኔታ ነው የምናየው። ኦሮምኛ ተናጋሪዎች ወደ ሃያ በመቶዎች ቢሆንም የከተማዋ ባለቤት ኦሮሞው ብቻ ስለሆነ፣ ሌሎች በከተማዋ አስተዳደር ውስጥ እጣ ፋንታ የላቸውም። እርሱ፣ ወላጆቹ፣ ቅድመ አያቶቹ ናዝሬት ከተወለደ የናዝሬት ልጅ ይልቅ፣ በቅርቡ በአዳማ ነዋሪ የሆነ፣ ከያቤሎና ደምቢዶሎ፣ ፣ ከኮፈሌና ከሞያሌ፣ ከጊምቢና ከደምቢ የመጡ፣ የበለጠ መብት አላቸው። ኦሮሞ ስለሆኑ ብቻ።
 
የአዳማ ህዝብ አብዛኛው አማርኛ ተናጋሪ ቢሆንም መሰረታዊ የዜግነት መብቱ ተረግጦ በሚናገረው ቁንቋ የመንግስት አገልግሎት እንኳን ተነፍጓል። በአዳማ ስለዚህ 100: 0 አሰራር ነው ያለው። መቶ ለኦሮሞ፣ ዜሮ ለተቀረው ማህበረሰብ።
 
አዳማ ብቻ አይደለም። ጂማ ከተማንም ብንወስዱ ተመሳሳይ ሁኔታ ነው ያለው። አብዛኛው እዚያ የሚኖረው ማሀበረሰብ ሕብረ ብሄራዊ የሆነ ማህበረሰብ ነው። ግን ታሪካዊቷ ጂማ በኦሮሞ ክልል ውስጥ በመጠቃለሏ መስተዳድሩን ሙሉ ለሙሉ የያዙት ኦሮሞዎች ብቻ ናቸው። የኦሮሞ ብቻ ፖለቲካም ከተማዋ ማደግ ወደ ነበረባት ደረጃ እንዳታድግ አድርጓታል። በጂማ አብዛኛው ነዋሪ አማርኛ ተናጋሪ ሆኖ በቀበሌዎችን በከተማዋ አስተዳደር ግን አሁን ፎርሞች በኦሮምኛ ያውም በዚያ በላቲ ካልተጻፈ ምንም አይነት አገልግሎት ማግኘት አይቻልም።
 
ስለ አዳማ አንድ ወዳጄ ያካፈለኝን ላካፍላችሁ። ” አንድ የገጠመኝ ላጋራክ” አለኝ አስተያየቱን ሲጀመር።
 
ሲቀጥልም ” አስር ከሚሆኑ ኔዘረላንድ ዜጎች (ነጮች) ጋር ናዝሬት ከንቲባ ቢሮ ሄደን ነበር ፡፡ ጥቁር እኔ ብቻ ነበርኩ፡፡ በዕለቱ ከንቲባው ስላልነበረ ከጽ/ቤት ኃላፊ ጋር ተነጋግረንና ቀጠሮ አስይዘን ለመመለስ ወስነንና ወደ ቢሮው ገባን ፡፡ ከዚያም እኔ በአማርኛ ሳናግረው፤ እርሱ በኦሮሚኛ ይመልሳልኝ ጀመር ፡፡ እኔም ሆንኩ ነጮቹ ኦሮሚኛ እንደማንልችል በአማርኛ ነገርኩት፡፡ የተባለውን ለነጮችም ተረጎምኩላቸው ፡፡ በመጨረሻም በአማርኛ “በኦሮሚኛ ካልሆነ ውጡና ሂዱ ” አለ፡፡ ” ያው አማርኛ ትችል የለ ፤ ለምን አታናግረንም ፧” አልኩት?። ” ይህ ኦሮሚያ ነው ፣ ስብሰባ በኦሮሚኛ ነው” አለኝ፡፡ የተባለውን ለነጮቹ ነገርኳቸውና ወጥተን ለመሄድ እየተነሳን እያለ፣ “የት ነው የምትኖረው ?” አለኝ፣ አሁንም በአማርኛ፡፡ “አዲስ አበባ” አልኩት፡፡ “እዚህ ሆነህ ነው እንዴ ኦሮሚኛ አላውቅም የምትለው? ለማነኛውም ለሌላ ጊዜ ተምረህ ና ” ብሎ አሰናበተኝ፨
 
ድሬዳዋ፣ ሃረር፣ ናዝሬትንና ጂማ ጠቀስኩ እንጂ ሌሎች አካባቢዎች ብትሄዱ ተመሳሳይ ዘር ተኪር የሕዝብ መብት ረገጣዎች እናያለን። አጋሮ፣ ባሌ ጎባ፣ አሰላ፣ ሻሸመኔ፣ ደብረዘይት፣ ዝዋይ፣ መቂ፣ እንዳለ በአዲስ አበባ ዙሪያ ባሉ እያደጉ በመጡ ከተሞች፣ በደራ ፣ በቅምብቢት፣ በአቢቹ ..በመሳሰሉ ወረዳዎች ሌሎች ማህበረሰባት ላይ ግፍና በደል፣ አድልዎችና ልዩነት አሁንም ድረስ አለ። እንደውም አንዳንድ አካባቢዎች የዘር ልዩነቱ ብሷል።
 
ባይገርማችሁ በኦሮሞዎች ላይ ራሱ ልዩነት እየተደረገም ነው። ወደ አርሲ ብትሄዱ ከሸዋ የመጡ ኦሮሞዎች፣ ወይንም ከኦሮሞ ውጭ ከሌላ ጋር የተጋቡ ኦሮሞዎች እንደ “ኦሮሞ” አይታዩም። በሌሎች ኦሮምዎች የሚገፉበት ሁኔታ ነው ያለው።
 
የዶ/ር አብይ አስተዳደር በዋናነት በተለይም በኦሮሞ ክልል የሚኖሩ በአስር ሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ማህበርሰባት መብትና ደህንነት በሕግ እንዲጠበቅ ማድረጉ ላይ ትኩረት መስጠት ያለበት ይመስለኛል። ስልጣን ከያዘ አመት ሊሞላው ነው።
 
በድሬዳዋና በደራ ህዝብ ድምጹን አሰምቷል። ነገ ጂማ አሰላ፣ አዳማ በመሳሰሉትም፣ የመብትና የእኩልነት ጥይቄ ነውና ሕዝብ ድምጹን ማሰማቱ አይቀርም። ነገሮች ወደ አላስፈላጊ ደረጃ ከመድረሳቸው በፊት አሁኑኑ ቅድሚያ ለፍትህ ፣ ቅድሚያ ለእኩልነት ይሰጥ። መድልዎች፣ ዘረኘኘት የአንድ ጎሳ የበላየነት ይቁም። ዜጎች በዘራቸው ወይንም ጎጣቸው ሳይሆን በችሎታቸው፣ በስራቸው ይመዘኑ !!! የዘር ቀመር ይቁም!!!!
 
ለዚህም ብቸኛና አስተማማኙ መፍትሄ ይኈን የጎሳ ፌዴራሊዝም አፍርሶ ሁሉንም እኩል የሚያያዩ በብቃት ላይ ያተኮሩ፣ ለአስተዳደር አመች የሆኑ፣ ህዝብን የማያጉላሉ፣ ከዘርና ከጎሳ ነጻ የሆኑ የፌዴራል መስተዳደሮች መዘርጋት ነው