ጋዜጠኛ ተመስገን ደሳለኝ በጸጥታ ሀይሎች በቁጥጥር ሥር ዋለ

ጋዜጠኛ ተመስገን ደሳለኝ በጸጥታ ሀይሎች በቁጥጥር ሥር ዋለ

ጋዜጠኛ ተመስገን ደሳለኝ ዛሬ ጠዋት 12:30 ላይ ሲቪል የለበሱ የጸጥታ ሀይሎች ወደ ቤቱ በመሄድ “ለጥያቄ እንፈልግሃለን” ብለው እንደወሰዱት ተሰምቷል።

ቤተሰቦቹ ለዋዜማ እንደገለጹት፤ የጸጥታ ሀይሎቹ ተመስገንን ወዴት እንደወሰዱት እና ለምን እንደሚፈልጉት የታወቀ ነገር የለም።

ከዚህ ቀደም ጋዜጠኛ ተመስገን “በሕቡዕ የተደራጀ ቡድን በመመስረት በተለያዩ የአገሪቱ አካባቢዎች ብጥብጥ እንዲፈጠር እና የሰው ሕይወት እንዲያልፍ በማድረግ” በሚል ክስ፤ በኋላም የመከላከያን ምስጢር በማውጣት የሰራዊቱን ሥም አጥፍተሃል በሚል ክስ ተከሶ ለወራት በቂሊንጦ ማረሚያ ቤት ሆኖ የፍርድ ሂደቱን ሲከታተል መቆየቱ ይታወሳል።

በዚህም የፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ 1ኛ የጸረ ሽብርና ሕገ መንግሥታዊ ችሎት፤ ጥቅምት 21/2015 ኹሉንም ክሶች ውድቅ በማድረግ “የሀሰት መረጃ ማሰራጨት” በሚል ክስ ብቻ ከውጪ ሆኖ ማስረጃዎችን በማቅረብ እንዲከራከር በመወሰን፤ በ30 ሺሕ ብር ዋስ እንዲፈታ ወስኖ የነበረ ሲሆን፤ በየካቲት 29/2015 የመጨረሻ ፍርድ ለመስጠት ቀጠሮ የሰጠው ከፍተኛው ፍርድ ቤቱ፤ ጋዜጠኛ ተመስገን ደሳለኝ ከቀረበበት ክስ በነፃ እንዲሰናበት ወስኗል።

ያም ሆኖ በድጋሚ ቅዳሜ ግንቦት 12/2015 ምሽት ላይ በአዲስ አበባ ጃንሜዳ አካባቢ ከሚገኘው መኖሪያ ቤቱ ለ“ጥያቄ ትፈለጋለህ” ተብሎ በጸጥታ ኃይሎች የተወሰደው ጋዜጠኛ ተመስገን፤ በአዲስ አበባ ሜክሲኮ አደባባይ አካባቢ ወደሚገኘው የፌደራል ፖሊስ ወንጀል ምርመራ ቢሮ ተወስዶ ለኹለት ሰዓት ገደማ የቆየ ሲሆን ምሽት አምስት ሰዓት ገደማ መለቀቁም ይታወሳል።

ጋዜጠኛ ተመስገን ዛሬ ጠዋት ሲቪል የለበሱ የጸጥታ ሀይሎች የተወሰደው፤ ከዚህ ቀደም በፍርድ ቤት ነጻ ከተባለበት ክስ ጋር በተያያዘ ይግባኝ ተጠይቆበት ይሁን ወይንም ሌላ አዲስ ክስ ተመስርቶበት እስካሁን የታወቀ ነገር የለም።