በፀጥታ ኃይሎች የንግድ ቤታቸው የፈረሰባቸው በርካታ አካል ጉዳተኞች ለልመና ጎዳና ልንወጣ ነው አሉ

በፀጥታ ኃይሎች የንግድ ቤታቸው የፈረሰባቸው በርካታ አካል ጉዳተኞች ለልመና ጎዳና ልንወጣ ነው አሉ

 (አዲስ ማለዳ) በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር፣ አዲስ ከተማ ክፍለ ከተማ ወረዳ 08 ልዩ ሥሙ ከረሚላ ፋብሪካ ተብሎ በሚጠራው ቦታ ከ2001 ጀምሮ ቋሚ ቦታ እስከሚሰጠን በጊዜያዊነት ሥንሰራ ነበር ያሉ በርካታ የአካል ጉዳተኞች፤ የሥራ ቦታችን በመንግሥት የጸጥታ ኃይሎች በለሊት በመፍረሱ እና ዕቃችንም በመወሰዱ ከፍተኛ ችግር ላይ ወድቀናል ሲሉ ለአዲስ ማለዳ ገለጹ፡፡

ለዚህ ችግር የተጋለጡት የአካል ጉዳተኞች ቁጥራቸው ከ180 የማያንሱ መሆኑን ገልጸው፤ የሥራ ቦታቸው የፈረሰው እና ዕቃቸውም የተወሰደው ባሳለፍነው ሐሙስ ግንቦት 10/2015 ሌሊት ዘጠኝ ሰዓት መሆኑን አስረድተዋል፡፡

የንግድ ቤቶቹን ያፈረሱት የአዲስ አበባ ፖሊስ አባላት እና የደንብ ሠራተኞ በጋራ መሆናቸውን የገለጹት አካል ጉዳተኞች፣ ሊያፈርሱብን እንደሆነ ቀድሞ መረጃ ደርሶን ለአስራ አምስት ቀን ስንጠብቅ ነበር፣ በኋላ ግን ትተውታል ብለን በተዘናጋንበት ነው ድንገት መጥተው ያፈረሱብንም ብለዋል፡፡

አካል ጉዳተኞቹ ራሳቸውን እና ቤተሰቦቻቸውን የሚያስተዳድሩት በዚህ የንግድ ቦታ በሚያገኙት ገቢ እንደነበር ገልጸው፣ ‹‹አሁን ግን ወደ ለልመና ወደ ጎዳና ከመውጣት ውጭ ሌላ መፍትሄ የለም፡፡›› ሲሉ ተደምጠዋል፡፡

መፍትሄ እንዲሰጣቸው ‹‹የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ምክትል ከንቲባ ጃንጥራር ዓባይ ቢሯቸው ሄደን ብንጠይቃቸውም እኔ ሥራ እድል ፈጠራ እንጂ ስለእናንተ አይመለከተኝም ብለው ወደ ከንቲቫ ጽህፈት ቤት ላኩን›› ሲሉ ገልጸዋል፡፡

‹‹ሆኖም ከንቲ ጽህፈት ቤት ሄደን ስንጠይቅ ደግሞ ክፍለ ከተማ ሂዱ ተብለን ወደዚያው ሄደን ስንጠይቅ ደግሞ በአመጽ የሚፈታ ችግር የለም አርፋችሁ ተቀመጡ፡፡›› የሚል ምላሽ ነው የተሰጠን ብለዋል፡፡

አክለውም ‹‹ቦታውን የያዙት አካል ጉዳተኞች ብዙዎች ከአንድ ብሔር የተሰባሰቡ ናቸው በሚል ነው ይህ የተደረገው›› የሚል መረጃም ከዚያው ከክፍለ ከተማው ሠራተኞች ይደርሰናል ካሉ በኋላ፣ ‹‹አካል ጉዳተኞች በመሆናችን የተሻለ እግዛ ሊደረግልን ሲገባ፣ በመንግሥት አካላት ይህን መሰል አስከፊ በደል የተፈጸመ በጣም አዝነናል›› ሲሉ ተደምጠዋል፡፡

እንዲሁም ጥያቄያችንን ለማቅረብ ወደ ተለያዩ አካላት ስንሄድ የሚሰማን አካል ካለመኖሩም በላይ ከጀርባችሁ የፖለቲካ አጀንዳ አለ በማለት ጭምር ማዋከብ እና እስር እየደረሰብን ነውም ብለዋል፡፡

አካል ጉዳተኞቹ መንግስት ቋሚ የሥራ ቦታ እንዲሰጣቸውና ድጋፍ እዲያደርግላቸው መጠየቃቸውን ተከትሎ ቋሚ ቦታ እስከሚያገኙ ድረስ በተሰጣቸው ጊዜያዊ ቦታ ላይ እየሰሩ በማህበር ተደራጅተው ለዓመታት ሲጠብቁ እንደነበርም ነው የጠቆሙት፡፡

ቅሬታ አቅራቢዎቹ ለሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር ቅሬታ አቅርበው ምላሽ አለማግኘታቸውን የገለጹ ሲሆን፤ አዲስ ማለዳም የአካል ጉዳተኞች ጉዳይ በዋናነት ከሚመለከተው ከዚሁ ተቋም ማብራሪያ ለማድግኘት ተደጋጋሚ ጥረት ብታደርግም የሚመለከታቸው የሥራ ኃላፊዎች አሁን አይመቸንም በማለታቸው ሳይሳካ ቀርቷል፡፡