ህወሓትን በድጋሚ ለማስመዝገብ ማመልከቻ እንደማይገባ የፓርቲው ሊቀመንበር አስታወቁ

ህዝባዊ ወያነ ሓርነት ትግራይ(ህ.ወ.ሓ.ት) ሊቀ መንበር ዶክተር ደብረ ጽዮን ገብረ ሚካኤል፣ የድጋሚ ምዝገባ ለማድረግ፣ ለብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ማመልከቻ እንደማያስገባ አስታወቁ። “50 ዕድሜ ያለውን ሰው እንደ ዐዲስ አኹን ጀምር እንደማለት ነው” ያሉት ሊቀመንበሩ “ረዥም ዕድሜ ያለው ፓርቲ በሌላ መንገድ ራሱ ካልፈረሰ ይቀጥላል” ብለዋል።ፓርቲያቸውም ኾነ ጊዜያዊ አስተዳደሩ፣ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ የሰጠውን የህጋዊነት የስረዛ ውሳኔ ተቃውሞ መግለጫ ማውጣቱን ጠቅሰው፣ ጉዳዩን ለአፍሪካ ኅብረትም ማሳወቃቸውን ተናግረዋል።

ሊቀ መንበሩ፣ ዛሬ ለጋዜጠኞች በሰጡትና አንድ ሰዓት በፈጀው ጋዜጣዊ መግለጫቸው ላይ፣ ልዩ ልዩ ጉዳዮችን ያነሡ ሲኾን፣ ፓርቲያቸው፣ ሁሉንም ዓይነት ለውጥ ለማምጣት እየሠራ እንደሚገኝ አስታውቀዋል።

ዶ/ር ደብረ ጽዮን፣ ተፈናቃዮች ወደ ቀዬአቸው አለመመለሳቸውን፣ ከጦርነቱ በፊት የክልሉ የአስተዳደር ወሰን የነበሩ አካባቢዎች በጊዜያዊ አስተዳደሩ መተዳደር አለመጀመራቸውንና በጦርነቱ ወቅት ተፈጽመዋል ያሏቸውን በደሎች የሚያጣራ አካል ሥራ አለመጀመሩን፣ እንደ ጉድለት አንሥተዋል፡፡ ኾኖም፣ የሰላም ስምምነቱ ሰላም ለማምጣት በሚያስችል ኹኔታ ላይ እንደሚገኝ ጠቁመዋል።

በጦርነቱ ምክንያት፣ ህወሓት ጠቅላላ ጉባኤ ሳያካሒድ መቅረቱን ያወሱት ዶ/ር ደብረ ጽዮን፣ “አሁን ጉባኤ በማካሔድ አጠቃላይ ማስተካከያ እናደርጋለን፤ ከዚያም ጋራ የአመራር ለውጡ ተያይዞ ይመጣል፤” ብለዋል።