አራት ኃይሎች የጋራ ግንባር ፈጥረው እየፈጸሙት ያለው ሌብነት የድህነት ወገባችንን እያደቀቀው ነው ሲል ብልጽግና ተናገረ

የኢትዮጵያ ገዢ ፓርቲ ብልጽግና በአሁኑ ወቅት አገሪቱ ዘርፈ ብዙ የሌብነት ፈተና የገጠማት መሆኑን እና ይህም የአገሪቱን “የድህነት ወገብ እያደቀቀ ነው”ሲል ገለጸ።

ፓርቲው ለሁለት ቀናት ያደረገውን የሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴውን ስብሰባ ሲያጠናቅቅ አርብ መጋቢት 08/2015 ዓ.ም. ባወጣው ሰፊ መግለጫ ላይ እንዳለው፣ “ኢትዮጵያ ወደ ታላቅ ምዕራፍ በምትሻገርበት ድልድይ ላይ ነች” በማለት አምስት ዋነኛ ተግዳሮቶች እንደገጠሟት በዝርዝር አመልክቷል።

ከእነዚህም ውስጥ ሌብነት አንዱ መሆኑን በመጥቀስ፣ በዚህ በኩል “አራት ኃይሎች የጋራ ግንባር ፈጥረው እየፈጸሙት ያለው ሌብነት የድህነት ወገባችንን እያደቀቀው መሆኑን” የብልጽግና የሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ ገልጿል።ፓርቲው በአገሪቱ ውስጥ በሌብነት ተግባር ላይ ተሰማርተዋል ያላቸው በመንግሥት ውስጥ የሚገኙ፣ በባለሀብቱ አካባቢ ያሉ፣ በብሔር ዙሪያ የተሰባሰቡ እና በሚዲያው ዘርፍ ያሉ ሌቦች ናቸው ብሏል።እነዚህም የመንግሥት መዋቅር እና ሥልጣንን፣ ገንዘብን፣ የብሔር ሽፋንን እንዲሁም በሚዲያ በኩል ደግሞ የሌቦችን ገጽታ ይገነባሉ በማለት ድርጊቶቹ ይፈጸማሉ ያለበትን ሂደት እና ሁኔታ አመልክቷል።“ሌቦቹ ሲያዙም ብሔራቸውን እየጠቀሱ ሕዝብ የተነካ ያስመስላሉ” በማለት ያለው መግለጫው፣ ለዚህም የፓርቲው አመራሮች፣ አባላት እና ደጋፊዎች እጃቸውን አስቀድመው ንጹህ በማድረግ ሌብነቱን እንዲዋጉ የሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴው ጥሪ አቅርቧል።

በፌደራል እና በክልሎች ውስጥ በተለያዩ መስኮች የሙስና ችግር እየተንሰራፋ መሆኑን ከሕዝቡ እና በተለያዩ የመገናኛ ብዙኃን ሲዘገብ ቆይቷል።

መንግሥት ከጥቂት ወራት በፊት በተቋማቱ ውስጥ አለ ያለውን የሙስና ችግር ለመከላከል እና ተጠያቂነትን ለማስፍን በሚል በከፍተኛ የመንግሥት ባለሥልጣናት የሚመራ የፀረ ሙስና አካል ማቋቋሙ ይታወሳል።

በዚህም ከፍተኛ የመንግሥት ኃላፊዎችን ጨምሮ በመቶዎች የሚቆጠሩ በሙስና ውስጥ እጃቸው አለ ተብለው የተጠረጠሩ ሰዎች በቁጥጥር ስር ውለው ጉዳያቸው በፍርድ ቤት መያዙ ተዘግቧል።

አገሪቱ በወሳኝ ምዕራፍ ላይ መሆኗን የጠቀሰው ገዢው ፓርቲ ከሌብነት በተጨማሪ ገጥመዋል ያላቸውን ሌሎች አራት ተግዳሮቶችን በዝርዝር አስቀምጧል።

ከእነዚህም መካከል የውቅቱ ዋነኛ ችግር የሆነውን የኑሮ ውድነትንም አንስቷል። በአገሪቱ ከኑሮ ውድነቱ ጋር የሥራ አጥነት መጠን መጨመሩን ጠቅሶ፣ ይህንን ችግር በጊዜያዊነት እና በዘላቂነት ለመፍታት እርምጃዎች እየተወሰዱ ነው ብሏል።

በተጨማሪም የኢትዮጵያ ችግር ብቻ አይደለም ያለውን የኑሮ ውድነት ችግርን “በብቃት ለመሻገር መንግሥት መራር ውሳኔ ሊወስድባቸው የሚገቡ ጉዳዮች አሉ” ያለ ሲሆን፣ እነዚህ “መራር ውሳኔዎች” ምን እንደሆኑ ያለው ነገር የለም።

በምርት እና በአቅርቦት ላይ የሚታዩ የአመራር እና የአሠራር ችግሮችን መፈታት፣ በየአካባቢው የሚቆሙ ኬላዎች “ከሕግ አግባብ ውጪ የሚያካሂዱት እገዳዎች እና ዘረፋዎች በአመራሮች እንዲሁም ሕግን በማስከበር መፈታት አለበት” ብሏል።

በተጨማሪም የሕዝቡን ችግር በማባባስ ኪሳቸውን መሙላት በሚፈልጉት ላይ እርምጃ መወሰድ፣ በአምራቾች እና በሸማቾች መካከል ያለው የአቅርቦት ሰንሰለት እንዲረዝ በሚያደርጉ ደላሎች እና ነጋዴዎች ላይ በሕግ መጠየቅ እንደሚገባ ጠቅሷል።

በአገራዊ እና በዓለም አቀፋዊ በሁኔታ ምክንያት በአሁኑ ወቅት ታይቶ በማይታወቅ ሁኔታ በመላው አገሪቱ የኑሮ ውድነት የተከሰተ ሲሆን፣ የመሠረታዊ ሸቀጦች ዋጋም በከፍተኛ ሁኔታ አሻቅቧል። በተጨማሪም የምርቶች እጥረት የዋጋ መናሩን የበለጠ አባብሶታል።

የብልጽግና ፓርቲ አገሪቱ ገጥሟታል ካላቸው ፈተናዎች መካከልም ነጻነትን በአግባቡ አለመጠቀም ባለው ነጥብ ላይ፣ በነጻነት ስም “ሕግ እያፈረሱ፣ የሌሎችን መብት እየጣሱ፣ ግጭት እና ጥላቻን እየቀሰቀሱ፣ ብሎም አገርን እያተራመሱ መንቀሳቀስ ወንጀል ነው” በማለት ይህም የህግ ተጠያቂነትን ያስከትላል ብሏል።

በተጨማሪ ደግሞ በመንግሥት እና በፓርቲ ባለሥልጣናት የአገሪቱን ኅብረ ብሔራዊ አንድነት የሚፈታተኑ ሁኔታዎች እያቆጠቆጡ መጥተዋል በማለት “የሕዝብን አንድነት ከሚንዱ፣ ጥላቻን እና ግጭትን ከሚያባብሱ ንግግሮች እና ድርጊቶች መቆጠብ አለባቸው” ሲል አስጠንቅቋል።

የብልጽግና ፓርቲ ሥራ አስፈጻሚ በመግለጫው ሌላኛው በተግዳሮትነት ካስቀመጣቸው ጉዳዮች አንዱ የሆነው፣ አገሪቱ ካለፈችበት ሂደት አንጻር “ታሪክ ካሸከመን ዕዳዎች የሚመነጭ ነው” በማለት፣ አገሪቱ የሚያኮሩ በርካታ ታሪክ እንዳላት በመጥቀስ፣ “በተቃራኒው ደግሞ በታሪካችን ውስጥ ያልፈታናቸው፣ ተጨማሪ ችግር አድርገን የጨመርናቸው እና ያልተግባባንባቸው “ዕዳዎች አሉን” ብሏል።

ይህ ሁኔታ የኢትዮጵያ ችግር ብቻ ሳይሆን አለመሆኑን በማመልከት፣ ፓርቲው እነዚህ “የታሪክ ዕዳዎቻችን” ያላቸውን ተግዳሮቶች “በምክክር፣ በይቅርታ እና በዕርቅ እናርማቸው” ሲል ጥሪ አቅርበዋል።

በፌደራል መንግሥቱ እና በክልሎች ውስጥ በበላይነት መንግሥት ከመሠረተ ሁለተኛ ዓመቱን የያዘው ብልጽግና ፓርቲ የሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ ለሁለት ቀናት በተለያዩ ወቅታዊ ጉዳዮች ላይ በመወያየት ባወጣው መግለጫ አገሪቱን እየፈተኗት ነው ካላቸው ችግሮች አንጻር የሚወሰዱ እርምጃዎችን በዝርዝር አላመለከተም።