በወለጋ ያለውን ችግር በእርቅ ለመፍታት አመራሮች ፈቃደኛ አልሆኑም ተባለ

በኦሮሚያ ክልል በወለጋ የተለያዩ አካባቢዎች ለረዥም ጊዜ የቆየውን የፀጥታ ችግር በእርቅ ለመፍታት የመንግሥት አመራሮች ፈቃደኛ አይደሉም ሲሉ ነዋሪዎች ለአዲስ ማለዳ ገለጹ፡፡

ለአብነትም በአንገር ጉትን ከተማ እና በዙሪያው የሚኖረው ማሕበረሰብ ችግሩን በአገር ሽማግሌዎች በእርቅ መፍታት ጥረት ቢያደርግም፣ የአካባቢው አመራሮች ለዚህ ተባባሪ ባለመሆናቸው ሊሳካ አልቻለም ነው ያሉት፡፡

ይህ ተከትሎም በምስራቅ ወለጋ አንገር ጉትን ከተማ በማንነታቸው የተነሳ ለጥቃት ተጋላጭ የሆኑ የማሕበረሰብ ክፍሎች ለደህንነታቸው በመስጋት ወደ ገጠር ቀበሌዎች ወጥተው እንደሚኖሩ ተናግረዋል፡፡

ማሕበረሰቡ የተፈጠሩ ችግሮችን በእርቅ በመፍታት እንደበፊቱ በመልካም ጉርብትና እና በሰላም መኖር ይፈልጋል፣ ነገር ግን የአመራሩ ፈቃደኛ አለመሆን ሁሌም ሰዎች እንዲፈናቀሉና እንዲገደሉ ምክንያት ሆኗል ነው ያሉት፡፡

በአንገር ጉትን ከተማ ከዚህ በፊት ማንነት ተኮር ግጭቶች እንዲባባሱ ግፊት አድርገዋል የተባሉ አመራሮች፣ በአካባቢው የተቋቋመው የኮማንድ ፖስት ግብረ ኃይል በደረሰው ጥቆማ መሰረት ከኃላፊነታቸው እንዲነሱ ቢያደርግም፣ የተተኩትም ሥር የሰደደ የማንነት ጥላቻ ስላለባቸው በተፈለገው ልክ ለውጥ ሊመጣ አልቻለም ሲሉም ነዋሪዎቹ ተናግረዋል፡፡

እንዲሁም ወቅታዊ ችግሩን ተገን በማድረግ በስርቆት እና ዝርፊያ የተሰማሩ አካላት መኖራቸው እርቅ እንዳይፈጠር ሌላኛ እንቅፋት መሆኑ ተነግሯል፡፡

በምስራቅ ወለጋ በተለይም በጊዳ አያና ወረዳ እና አጎራባች በሆኑ እንደ ሆሮ ጉድሩ አካባቢዎች ማሕበረሰቡን ከመንግሥት ጋር የሚያገናኝ ምን ዓይነት መዋቅር አለመኖሩ ተጠቅሷል፡፡

ግብር የሚገብርም የሚያስገብርም አካል የለም ያሉት ነዋሪዎቹ፣ በየመንገዱ ሰዎች ይገደላሉ፣ ይዘረፋሉ፣ ሕግ የሚባል ነገር የለም ብለዋል፡፡

“እንደ ጊዜያዊ መፍትሄ አርሶ አደሩ ወደገጠር ወጣ ብሎ ራሱን ለመጠበቅ ጥረት እያደረገ ነው ያለው፣ ይህ ግን ዘላቂ መፍትሄ ባለመሆኑ መንግሥት የዜጎቹን ሰላም የማስጠበቅ እና ሀገራዊ ደህንነትን የማስፈን ትልቅ ኃላፊነቱን ሊወጣ ይገባል።” ሲሉ ጠይቀዋል፡

አዲስ ማለዳ